ዛሬ ታኅሣሥ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የጎርጎርዮሳዊውን የዘመን አቆጣጠር የሚከተሉ አገሮች የ2020 ዓመታቸውን ጀምረዋል፡፡ ትናንት የተጠናቀቀው 2019 ዓመት የማይዘነጉ ክስተቶች ተስተናግደውበታል፡፡ የዓለምን ሕዝብ አጀብ ካሰኙት መካከል አንኳሮቹ እንደሚከተሉት ናቸው፡፡
የዶናልድ ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ መግባት
የተለያዩ አወዛጋቢ ንግግሮችን በማድረግ የሚታወቁት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሰሜን ኮሪያ ያቀኑት በተጠናቀቀው 2019 ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ ሄደው ከፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን ጋር እንደሚነጋገሩ ደጋግመው ሲገልፁ፣ በርካቶች ቀልድ መስሏቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ፕሬዚዳንት ትራምፕ እንዳሉትም ከሰሜን ኮርያ ፕሬዚዳንት ጋር በሰሜንና ደቡብ ኮርያ ድንበር ላይ ተገናኝተው ከመምከር ባሻገር የሰሜን ኮሪያ ግዛትን በመርገጥ ዓለምን አስደምመዋል፡፡ ተቋርጦ የነበረው የኑክሌር ውይይትም ተጀምሯል፡፡ ውይይቱ ፍሬያማ መሆኑ አጠያያቂ ቢሆንም፣ ተቋርጦ የነበረውን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ማስቀጠሉ ተችሏል፡፡ ተቀራርቦ ማውራት መቻላቸው እንደ ትልቅ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕም በሥልጣን ላይ ሳሉ ሰሜን ኮሪያን የጎበኙ የመጀመርያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡
የዶናልድ ትራምፕ ክስ
የዶናልድ ትራምፕ ክስ ጉዳይም በዓመቱ ውስጥ ከተሰሙ ዓበይት ነገሮች ዋነኛው ነው፡፡ ሥልጣናቸውን ያላግባብ ተጠቅመዋል፣ የምክር ቤቱን ሥራ አደናቅፈዋል በሚል ሁለት ክሶች የቀረበባቸው ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ሴኔት ፊት ቀርበው ክሳቸውን እንዲከላከሉ የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ ወስኗል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ሴኔት ፊት ቀርበው ክሳቸውን እንዲከላከሉ ሲደረግ፣ ከአንድሪው ጆንሰንና ቢል ክሊንተን ቀጥሎ በታሪክ ሦስተኛው ፕሬዚዳንት ይሆናሉ፡፡ አንድሪው ጆንሰን የቀረበባቸውን ክስ ተከትሎ በፈቃዳቸው ሥልጣን ሲለቁ፣ ቢን ክሊንተን ደግሞ ሴኔት ቀርበው ክሳቸውን ተከራክረው በማሸነፍ ሥልጣን ላይ ቆይተዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሥልጣን ላይ የመቆየታቸው ነገር ሴኔቱ በሚሰጠው ውሳኔ የሚመሠረት ይሆናል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ
የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ አንገብጋቢ የወቅቱ አጀንዳ ነው፡፡ በጉዳዩ የተለየ አቋም የሚያራምዱ ፖለቲከኞች የአየር ንብረት ለውጥ በሚነገርለት መጠን አስጨናቂ አይደለም ይላሉ፡፡ ነገር ግን የአየር ንብረት ለውጥ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሳሳቢ መሆኑን የሚያሳዩ የተለያዩ ክስተቶች ባለፈው 2019 ታይተዋል፡፡ ዓመቱ የአየር ለውጥ ተፅዕኖ ምልክቶች የታዩበት ብቻም ሳይሆን፣ የከባቢ አየር አለኝታ የሆኑ ደኖች የወደሙበትም ነበር፡፡ በብራዚል የሚገኘው ጥቅጥቁ አማዞን ደን ከባድ ቃጠሎ የደረሰበት በተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ ዓመት ነበር፡፡ የደረሰው ቃጠሎ ሰፊ ቦታን የሸፈነ በመሆኑ የዓለምን ትኩረት ሳበ እንጂ በየዓመቱ ሲቃጠል መኖሩም ተነግሯል፡፡ በደረቃማው ወቅት በተለይም በሐምሌና ጥቅምት ወራት መካከል አማዞን ይነዳል፡፡ በተለያዩ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ለምሳሌ በመብረቅ ምክንያትም ደኑ በየጊዜው ይቃጠላል፡፡ በ2019 የደረሰው አስደንጋጩ ቃጠሎ ግን በደኑ ውስጥ የሚኖሩ አርሶ አደሮች እርሻቸውን ለማስፋፋት ሲሉ በጫሩት እሳት ሳይደርስ እንዳልቀረ ተነግሯል፡፡ በቃጠሎው 7,747 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ደን ጠፍቷል፡፡ የአብዛኞቹን ትኩረት ከሳበው የአማዞን ደን ቃጠሎ የበለጠ አደጋም በአፍሪካ በሚገኙ ደኖች ላይ ተከስቷል፡፡ በአማዞን ደን የደረሰውን እጥፍ ያህል ቃጠሎ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደርሷል፡፡ በአንጎላም ቀላል የማይባል የደን ቃጠሎ ተመዝግቧል፡፡ በኢትዮጵያ ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የደረሰው ቃጠሎም አይዘነጋም፡፡ በአውስትራሊያ በደረሰው ቃጠሎም አራት ሚሊዮን ሄክታር የሚሸፍን ጫካ ሲጠፋ፣ ከ900 የሚበልጡ ቤቶችም ነደዋል፡፡ የሰዎች ሕይወትም ጠፍቷል፡፡ አውስትራሊያን ጭጋግ ያለበሰው አማዞንን ያመነመነው፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ያስጨነቀው የደን ቃጠሎ ወደ ከባቢ አየር የለቀቀው የካርበን መጠን፣ ድርብ ጉዳት ሆኖ ይታያል፡፡
ቦሪስ ጆንሰን
እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት አባልነቷ እንድትወጣ የተጀመረውን ዘመቻ ተከትሎ በመጀመርያ ዴቪድ ካሜሩን ሥልጣናቸውን ሲለቁ፣ በእግራቸው የተተኩት ቴሬሣ ሜይም ብሪኤግዚትን ዕውን ማድረግ ሳይችሉ መንበራቸውን ለቦሪስ ጆንሰን አስረክበዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመሪነት ቦታውን የያዙት የእንግሊዝ ወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ቦሪስ ጆንሰን፣ በየትኛውም መንገድ ብሪኤግዚትን ተግባራዊ ለማድረግ ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ቦሪስ ከዲፕሎማት አባትና ከአርቲስት እናታቸው የተወለዱት እ.ኤ.አ. በ1964 ነበር፡፡ ቦሪስ ጋዜጠኛ ሆነው ሠርተው ያውቃሉ፡፡ ደራሲም ሆነው መጻሕፍት አሳትመዋል፡፡ የለንደን ከተማ ከንቲባ ሆነው አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2016 እስከ 2019 የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነውም ሠርተዋል፡፡
ሆንግ ኮንግ
ከብሪታኒያ አስተዳደር ወደ ቻይና ከተመለሰች 21 ዓመታትን ያስቆጠረችው ሆንግ ኮንግም ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ጠንካራ ተቃውሞ ያስተናገደችበት ነበር፡፡ አንድ መንግሥት ሁለት አስተዳደር በሚል የፖለቲካ አወቃቀር የምትተዳደረው ሆንግ ኮንግ ራስ ገዝ መሆኗ ይነገራል፡፡ የምትተዳደረውም በየአምስት ዓመቱ በሚመረጡ ሥራ አስፈጻሚዎች ነው፡፡ የሆንግ ኮንግ ራስ ገዝነት ለይስሙላ እንጂ ከቻይና ተፅዕኖ ነፃ አለመሆኗን ግን ዜጎቿ ያምናሉ፡፡ ሥራ አስፈጻሚዎቿ ቃለ መሀላ የሚፈጽሙትም በቻይና ይሁንታ ነው፡፡ በከተማዋ ወንጀል የሚፈጽሙ የግዛቲቱ ተጠርጣሪዎች በቤጂንግ እንዲዳኙ የሚፈቅደው ደንብ መርቀቁ ደግሞ ሆንግ ኮንግ ከቻይና ነፃ አይደለችም የሚለውን ትርክት ይበልጥ ያጠናከረና ተወላጆቹም ቁጣቸው ገንፍሎ በ2019 ተቃውሟቸውን ይዘው አደባባይ እንዲወጡ አድርጓል፡፡ ተቃዋሚዎች የተለያዩ የሕዝብ መገልገያ ቦታዎችን በመያዝ ሥራን አስተጓጉለዋል፡፡ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያውን በወረሩበት ወቅት ከ300 የሚበልጡ በረራዎችን አሰናክለዋል፡፡ በአንድ ዩኒቨርሲቲ መሽገውም ከፖሊሶች ጋር ተፋጠዋል፡፡ ፖሊሶችን በድንጋይ፣ በቀስትና በሌሎች መሣሪያዎች አዋክበዋል፡፡ እስካሁን በሺዎች የሚቆጠሩ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የሱዳን አመፅ
በተጠናቀቀው ዓመት በአመፅ ከተናጡ አገሮች መካከል ሱዳን በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች፡፡ በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን የምግብ ዋጋ ንረትን፣ የነዳጅ እጥረትን ምክንያት አድርጎ እ.ኤ.አ. በ2018 ማብቂያ ላይ የተቀሰቀሰው የዜጎች ተቃውሞ በሥልጣን ላይ ወደነበሩት ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር የዞረው ብዙም ሳይቆይ ነበር፡፡ ተቃውሞው ወደ አልበሽር ከዞረባቸው ምክንያቶች አንዱ ሥርዓቱ የዜጎች ስቃይ የበዛበት ጭፍጨፋዎች ያጀቡት ነው የሚል ነበር፡፡ በ2003 እና 2004 መካከል 15,000 ሱዳናውያን በሥርዓቱ በሚታገዙ ሚሊሺያዎች ተገድለዋል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩም ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ሚሊሺያዎቹ በዳርፉር የሚገኙ ሴቶችን ደፍረዋል፡፡ መንግሥት በዜጎቹ ላይ ኬሚካል መሣሪያ ተጠቅሟልም ይባላል፡፡ የሱዳን ዜጎችም በተለያዩ ጊዜያት የነበሩትን መሰል ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እያስታወሱ ትግላቸውን አቀጣጠሉ፡፡ ሰላማዊው ተቃውሞ ወደ አመፅ ተለውጦ በርካቶች ሞተዋል፡፡ ቅን አልነበሩም የተባሉት አልበሽርም ተነስተው ዘብጥያ ወረዱ፡፡ በምትካቸው ወታደራዊው ሥርዓት ከተተካ በኋላ የወታደሩና የሲቪል የጋራ መማክርት ተመሥርቶ አዲስ የሲቪል ጠቅላይ ሚኒስትር ከተሾመ በኋላ ሱዳናውያኑ ማመፃቸውን አቆሙ፡፡ ሱዳንም ሰላም ሆነች፡፡