Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአገር ውስጥ ምርቶች ብቻ የሚቀርቡበት መድረክ

የአገር ውስጥ ምርቶች ብቻ የሚቀርቡበት መድረክ

ቀን:

መንግሥት ለኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ድህነትን ለመቅረፍ ቅዶ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ማቋቋም ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም ከ100,000 በላይ ኢንተርፕራይዞች በአገር አቀፍ ደረጃ ተቋቁመዋል፡፡ ሆኖም በዘርፉ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ስኬቶች ቢመዘገቡም፣ የተለያዩ ችግሮች መታየታቸው አልቀረም፡፡ ከእነዚህ አንዱ የገበያ ትስስር ነው፡፡

 በፌዴራልና በክልል ደረጃ የተቋቋሙ ኢንተርፕራይዞችም ከሚገጥሟቸው እክሎች አንዱ የሆነውን ገበያና የገበያ ትስስር ችግር ለመቅረፍ በተለያዩ ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች ሲሳተፉ ይስተዋላሉ፡፡

ኢንተርፕራይዞቹ በመጠን፣ በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ ምርትና አገልግሎት በማስተዋወቅና በመሸጥ፣ አትራፊ እንዲሆኑም መንግሥት ከሚያመቻቻቸው የገበያ ድጋፎች አንዱ ኤግዚቢሽንና ባዛር ነው፡፡

ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮችም የፈጠራ ሥራዎችን በማበረታታትና በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችንና ፈተናዎችን በራሳቸው በኢንተርፕራይዝ ባለቤቶች እንዲፈቱም ዕድል ይፈጥራሉ፡፡

ክልሎችና ከተሞችም በየአካባቢያቸው ኤግዚቢሽንና ባዛሮችን በየወቅቱ በማመቻቻቸት፣ ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁና እየሸጡም ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም ልምድ እንዲለዋወጡ ይሠራሉ፡፡

ክልሎችና ከተሞች በራሳቸው ከሚያዘጋጇቸው በተጨማሪም፣ አገር አቀፍ የኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር በየዓመቱ ይካሄዳል፡፡

የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን የኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር የሚመራ ሲሆን፣ ለ2012 በጀት ዓመትም አንደኛውን ዙር የሞዴል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይች አገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር እያካሄደ ይገኛል፡፡   

ከታኅሣሥ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለሰባት ተከታታይ ቀናት ጀሞ ቁጥር አንድ አካባቢ እየተካሄደ ያለውን የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ቡድን መሪ ወ/ሮ አቦዘነች ነጋሽ እንዳሉት፣ በኤግዚቢሽኑ የሚቀርቡት የአገር ውስጥ ምርቶች ብቻ ናቸው፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ከ100,000 በላይ ኢንተርፕራይዞች በኤግዚቢሽኑ የሚሳተፉት 180 ያህል ሲሆኑ፣ እነዚህም ሞዴል ሆነው የተቀመጠውን መሥፈርት ያሟሉና ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች መርጠው የላኳቸው ናቸው፡፡

በ2012 በጀት ዓመት በአገር አቀፍ አንደኛው ዙር የሞዴል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር ከሁሉም ክልሎችና ከተሞች ከተውጣጡት 180 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በተጨማሪ አሥር አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ይሳተፋሉ፡፡ ከተሳታፊዎች ውስጥ 50 በመቶ ሴቶች፣ ሦስት በመቶ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም አሥር ተቋማት ተሳትፈዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ነጋዴ ሴቶች ማኅበርና ከኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበራት በልዩ ልዩ ምርቶችና አገልግሎቶች ከእያንዳንዳቸው ሦስት፣ ከሴቶች ኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ፕሮግራም አምስት፣ ከፋሽን ዲዛይን ማኅበር አምስት፣ ከሴቶች ራስ አገዝ ድርጅት አምስት፣ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ሦስት፣ እንዲሁም ኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ማዕከል አምስትና ከአጋር አካላት የተመለመሉ 29 ኢንተርፕራይዞችም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ 15 ኢንተርፕራይዞች በሴቶች እንዲሁም ሁለት ኢንተርፕራይዞች በአካል ጉዳተኞች ባለቤትነት የተያዙና የሚመሩ ናቸው፡፡

ባህላዊና ዘመናዊ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርት ውጤቶች፣ ባህላዊና ዘመናዊ የቆዳ አልባሳትና የቆዳ ምርት ውጤቶች፣ ባህላዊና የዕደ ጥበባትና ቅርፃ ቅርፅ ሥራዎችና ውጤቶች፣ የብረታ ብረት፣ የእንጨት ሥራና የኢንጂነሪንግ ሥራዎችና ውጤቶች፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች፣ የከተማ ግብርና፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና የፈጠራ ሥራዎች በባዛሩ ቀርበዋል፡፡   

ኢንተርፕራይዞቹ የሚገጥማቸውን የገበያ ችግር ለመቅረፍ በመንግሥት በኩል ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች ቢዘጋጁም፣ የመሥሪያ ቦታ ከማግኘት፣ ደኅንነታቸው የተጠበቁ የምግበ ምርቶች ከማቅረብ፣ ብድር ከማግኘትና በወቅቱ ከመመለስ፣ ኢንተርፕራይዞች በራሳቸው ሳያመርቱ ከሌሎች ገዝተው የማቅረብ፣ የኤግዚቢሽን ማሳያ ቦታዎች ችግሮችና ሌሎችም ይስተዋላሉ፡፡

የኮሙዩኒኬሽን ቡድን መሪዋ አቦዘነች እንደሚሉት፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በምርት፣ በዓይነትና በጥራት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየተሠራ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የማምረት ዘርፍ ብዙም ያደገ አለመሆኑ ተግዳሮት ነው፡፡ ሆኖም በጥቃቅን ደረጃ የማምረት ሥራ ከተጀመረ ወዲህ ሥራን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ልምዶች ተገኝተዋል፡፡

አንድ አምራች በማምረት ዘርፍ ሲገባ ኢንተርፕራዙ በዓይነት፣ በጥራትና በብዛት ተወዳዳሪ መሆን ቢጠበቅበትም ከጥራት ጋር በተያያዘ ሰፊ ችግሮች ይታያሉ፡፡ በቆዳና በቆዳ ውጤቶች፣ በአልባሳትና በአግሮ ፕሮሰሲንግ የጥራት ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡

የምርት ጥራት ችግርን ለመቅረፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የማምረቻ መሣሪያዎች እንዲቀርቡ፣ ጥራታቸውና ደኅንነታቸው የተጠበቀ የማምረቻ ቦታዎች እንዲኖሩ፣ በተለይ ምግብና ምግብ ነክ በሆኑ ሥራዎች የተሰማሩት መንግሥት በሚያዘጋጃቸው ሼዶች እንዲያመርቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ሆኖም ካለው ሀብት አንፃር ይህ ሁሉም ቦታ እንደማይፈጸም ቡድን መሪዋ ተናግረዋል፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊት ትልቅ ችግር የነበረው ምርቶችን ከእጅ ንክኪ ነፃ በሆኑ ማሽኖች የማምረት ሒደት፣ በየክልሉ የካፒታል ፋይናንሲንግ ተቋማት በማቋቋም ማሽኖችን በሊዝ እንዲገዙና ለሚፈልጉ ኢንተርፕራይዞች በብድር እንዲሰጡ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ አዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደርን ጨምሮ በትግራይ፣ በአማራ፣ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ ከምግብ ጥራት ጋር ተያይዞ የደረጃና የጥራት ሰርተፊኬት የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ ከሚነሱ ዋና ዋና ችግሮች አንዱ የመሥሪያ ቦታ እጦት ነው፡፡ ኢንተርፕራይዞች የመሥሪያና የመሸጫ ቦታ እንዲያገኙ፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በጀት በመያዝ በየዓመቱ ሼዶች ቢገነቡም፣ ለኢንተርፕራይዞች ማስተላለፍ ላይ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡

ለሼዶች መብራትና ውኃ ባለመግባታቸው ሳይተላለፉም ለብዙ ጊዜያት መቆየት፣ ሲተላለፉም ፍትሐዊ አለመሆንና ከፍተኛ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ከሚታዩ ችግሮች እንደሚጠቀሱ፣ ይህንን ችግር ለመፍታትም እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡

አንድ ኢንተርፕራይዝ መንግሥት በሚያመቻቸው ሼድ አምስት ዓመት ሠርቶ ለተተኪ መልቀቅ ያለበት ቢሆንም፣ ይህንንም ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አለመቻሉም ሌላው ችግር ነው፡፡

ኢንተርፕራይዞች የተሰጣቸውን ሼድ ለምን ከአምስት ዓመታት በኋላ አይለቁም? የሚለው ሲታይ፣ ማምረቻ ሼድ ውስጥ ያሉት የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፣ ካፒታል ገንብተዋል፡፡ እነዚህ በአግባቡ ሌላ ቦታ ሄደው ሥራ ሳይጀምሩ ማስወጣት፣ በዘርፉ ላይ ተስፋ መቁረጥን ያስከትላል፡፡ ስለሆነም የየከተማ አስተዳደሮች በሚያስቀምጡት የኢንቨስትመንት አማራጭ ተጠቃሚ ሆነው እንዲሸጋገሩ ግንዛቤ ላይ መሥራት እንዳለበት፣ በቀጣዮቹ ዓመታትም የማስተላለፉ ሥራ ተግባራዊ እንዲሆን እየሠራበት መሆኑን ወ/ሮ አቦዘነች ተናግረዋል፡፡

ከብድር ጋር በተያያዘ በ2012 ሩብ ዓመት 1.2 ቢሊዮን ብር ከ34,000 በላይ ኢንተርፕራይዞች ተሠራጭቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የሴቶች ተጠቃሚነት 45 በመቶ ነው፡፡

ብድር ላይ በአንዳንድ ክልሎች ያሉ ኢንተርፕራይዞች በአግባቡ ሲመልሱ፣ በአንዳንዶቹ እየተመለሰ አይደለም፡፡ በመሆኑም ሥርዓቱን የጠበቀ የብድር አሰጣጥ እንዲዘረጋ እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...