ብዙዎች ከችግሮቻቸው ተነስተው መፍትሔ ለማግኘት ይጥራሉ፡፡ በሕመም ምክንያት የሚሰቃዩ ቤተሰቦቻቸውን በማየት እነርሱን የሚረዳና ከሕመማቸው የሚያገግሙበት መንገድ የሚፈልጉ ጥቂት አይደሉም፡፡ ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ የቅርብ ጓደኛ ስለሕመሙ ግንዛቤ ለመፍጠርና ሕክምና የሚገኝበትን መንገድ ለማመቻቸት፣ ማኅበር ሲመሰርቱ፣ አልፎም የሕክምና ተቋም በመክፈት ለሕመሞች መፍትሔ ለመሻት ሲሞክሩም ይስተዋላሉ፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መካከል የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ባለሙያው አቶ ሰሎሞን ተሾመ ይገኙበታል፡፡ እሳቸው ቤተሰቦቻቸውን ካጡበት በሽታ ሌሎችን ለመታደግ ዳማከሴ ፌዚዮቴራፒ ሪሀብ ማዕከል አቋቁመዋል፡፡ ስለሚሰጡት የሕክምና አገልግሎትና ተያያዥ ጉዳዮች ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ዳማከሴ ምን ዓይነት አገልግሎቶችን ይሰጣል?
አቶ ሰሎሞን፡- ከነርቭና ከጡንቻ ጋር ለተያያዙ ችግሮች፣ የአንጎል ጥቃት (ስትሮክ)፣ የጀርባ አጥንት መጨፍለቅ፣ የጅማት መጨማደድና የጡንቻ መዛል ከቀዶ ሕክምና በኋላ የሚደረጉ የአካል እንክብካቤዎች፣ ከስፖርት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን፣ ከእጅና እግር መቆረጥና ከአጥንት መሰንጠቅ ጋር ያሉ ችግሮችና ለሌሎችም የጤና እክሎች አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በተለይም ከፍተኛ ስቃይ ያለው ሕመም (ማኔጅመንትን) ጨምሮ ከአሥር በላይ የሕክምና አገልግሎት እንሰጣለን፡፡
ሪፖርተር፡- የቤት ለቤት ሕክምና አላችሁ፡፡ በምን መልኩ ነው የምታከናውኑት? የየትኞቹ የሕመም ዓይነቶች ነው ሕክምናውን የምትሰጡት?
አቶ ሰሎሞን፡- በቤት ለቤት አገልግሎት ከአሥር በላይ ለሚሆኑ ሕመሞች ሕክምና እንሰጣለን፡፡ ከቀዶ ሕክምና በኋላ የሚደረግ እንክብካቤ፣ ከሳምባ፣ ከልብና ከአተነፋፈስ ጋር የተያያዘ እንክብካቤ፣ የቁስል ቁጥጥር እንክብካቤ፣ የደም ግፊት ቁጥጥርና እንክብካቤን ጨምሮ ሕሙማን ከበሽታቸው እንዲያገግሙ የሚደረግበት መንገድ አለ፡፡ ሕመምተኞችን ከማስታመም ባሻገር የምክርና የመድኃኒት አወሳሰድና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች በቤት ለቤት ሕክምና እንሰጣለን፡፡
ሪፖርተር፡- ተቋሙ በአንድ ጊዜ ምን ያህል ሕመምተኞቹን ያስተናግዳል?
አቶ ሰሎሞን፡- በአንድ ጊዜ ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ ሕመምተኞችን ሊያስተናግድ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ወደ ተቋማችን የሚመጡ ሕምተኞቹ ሕሙማን አብዛኛዎቹ ዕድሜያቸው ገፋ ያለ ሲሆን፣ እነሱ ቶሎ እንዲያገግሙና ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲኖራቸው የምግብ ሥርዓትንም እናስተምራለን፡፡
ሪፖርተር፡- እንደዚህ ዓይነት የሕክምና አገልግሎት ውድ ነው፡፡ ብዙዎችም ፈርተው ወደ ሕክምናው አይወጡም፡፡ የእናንተ የሕክምና ተቋም በዋጋ ረገድ ምን ያህል ተቀባይነት አለው?
አቶ ሰሎሞን፡- ዳማከሴ የፊዝዮቴራፒና ሪሀብ ማዕከል የተነሳበት ዓለማ አጥንትን ጨምሮ በተለያዩ ሕመሞች ለሚሰቃዩ ሰዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በባለሙያዎች የታገዘ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ በዋጋ ረገድ ከሌሎች የፊዚዮቴራፒና ሪሀብ ማዕከል ጋር ሲነፃፀር እጅግ ያነሰ ነው፡፡ ይህም ያዋጣል ወይም ያከስራል ማለት ሳይሆን፣ በጣም የተጋነነ ትርፍን ሳይሆን ሕሙማን አገግመው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ዋና ሥራው ስለሆነ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ተቋሙን ለመክፈት ያነሳሳዎት ምንድነው?
አቶ ሰሎሞን፡- ተቋሙ በመጀመርያ የተከፈተው በቁጭት ነው፡፡ በእኔም ቤተሰብ የደረሰ ችግር በመኖሩ፣ የኔ ቤተሰቦች ያላገኙትን ሕክምና ሌሎች እንዲያገኙና የተሻለ ነገር ለማቅረብ ነው፡፡ በመሆኑም የተጋነነ ዋጋ ጨምረን አገልግሎቱ እንዳይዳረስ ማድረግ አንፈልግም፡፡ የሚያስፈልገው ሕሙማኑን ከስቃይ መታደግ ነው፡፡ ትልቁ ኃላፊነታችንም ይኸው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አንድ ሕመምተኛ (ታካሚ) በምን ያህል ጊዜ ነው ከሕመሙ የሚያገግመው?
አቶ ሰሎሞን፡- በዳማከሴ ፌዚዮቴራፒ ሪሀብ ማዕከል የገቡ ሕሙማን እንደ ሕመማቸው ዓይነት ይለያያል፡፡ ሥር የሰደደ ከሆነ ረዥም ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ በጊዜ ወደ ሕክምና ተቋም ከመጡ የመዳን ዕድል ሊኖራቸው ይችላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የሕመሙን ስቃይ ለመቀነስና ቢያንስ ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ድረስ በሕይወት እንዲቆዩ ለማድረግ የሚጣርበት ሁኔታ አለ፡፡ ሕሙማን ስቃያቸው እንዲቀንስላቸው ነው የምንሠራው፡፡
ሪፖርተር፡- የሠለጠነ ባለሙያ ስብጥራችሁ ምን ይመስላል?
አቶ ሰሎሞን፡- ማዕከሉን በተለያዩ የሕክምና መርጃ መሣሪያዎች እያሟላን እንገኛለን፡፡ በማዕከሉ ውስጥ ሁሉም ሠራተኞች በዘርፉ የሠለጠኑ ናቸው፡፡ ይህም ተገልጋዮች ሳይንገላቱ የምናስተናግድበትን ሁኔታ አመቻችቶልናል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከስድስት በላይ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥረናል፡፡ ተቋሙ አያደገና እየሰፋ ሲመጣ የሥራ ዕድሉም እንደዛው እየሰፋ ነው የሚመጣው፡፡ ከፊዚዮቴራፒ በተጨማሪ ስፒች ቴራፒ (የንግግር) ሕመምተኞችን በሥነ ልቦና በማነፅ፣ ስለሕመሙ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ተስፋ እንዳይቆርጡ የተለያዩ ምክሮችን እንሰጣለን፡፡ ማዕከሉን ከመክፈታችን ተመሰሳይ ማዕከሎችን የማየት ዕድል በማግኘታችን የሌሎችን ክፍተት እኛ ለመሙላት እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በማዕከሉ አቅም የሌላቸው ሕሙማንን ታግዛላችሁ?
አቶ ሰሎሞን፡- ‹‹የወደቁትን አንሱ›› የአረጋውያን መርጃ ማዕከል ብዙ አረጋውያን የሚገኙበት ማዕከል ነው፡፡ ሁሉንም መርዳት ባንችልም የተወሰኑትን ወደ ማዕከላችን በማምጣት ስቃያቸው እንዲቀንስላቸው እያደረግንላቸው እንገኛለን፡፡ በዚህም ገንዘብ ባናገኝበትም፣ የሥነ ልቦና እርካታ እያገኘንበት ነው፡፡ በመሆኑም የተቸገሩትን እናግዛለን፡፡
ሪፖርተር፡- በማዕከሉ ምን የተለየ አገልግሎት ይሰጣል?
አቶ ሰሎሞን፡- በተቋሙ በሕክምና ብቻ ሳይሆን የአመጋገብ ሥርዓትንም ለሕሙማን እናሳያለን፡፡ ሕሙማን ከሕመማቸው ቢሻላቸውም መልሰው እንዳይታመሙ የአመጋገብ ሥርዓታቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ ስለሆነም እዚህ ላይ እንሠራለን፡፡
ሪፖርተር፡- የማስፋፊያ ሥራ አለ?
አቶ ሰሎሞን፡- የማስፋፊያ ሥራውን ይኼኛው ሲጠነክር የምናደርገው ይሆናል፡፡ ማስፋፊያችንም ከ100 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለን እናምናለን፡፡