Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየመጽሐፈ ሄኖክ መንገድ

የመጽሐፈ ሄኖክ መንገድ

ቀን:

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ትኩረት እያገኙ ከመጡት ጥንታውያን መጻሕፍት መካከል መጽሐፈ ሄኖክ ይጠቀሳል፡፡ የሄኖክ መጽሐፍ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመጻሕፍት ቀኖና ውስጥ አንዱ ሆኖ ይሠራበታል፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ በዘርዐ ክህነት፣ በሊቃውንቱም ሆነ በምዕመኑ ተገቢ ቦታ ቢኖረውም፣ በብዙኃን ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በሌሎች መገናኛዎች ስለ መጽሐፉ ብዙ እየተባለ ነው፡፡

በሌላው ዓለም የተወሰነ ቁርጭራጭ ከመገኘቱ ውጪ እንደ ግዕዝ ቋንቋ ሙሉው የመጽሐፈ ሄኖክ ቅጂ መገኘቱ ታላቅ ነገር ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በባሕር ማዶ ሊቃውንት ዘንድ ‹‹Ethiopic Enoch›› (የግዕዝ መጽሐፈ ሄኖክ) ማለታቸውን ተከትሎ አንዳንዶች ለግዕዝ ምትክ ሆኖ የቀረበውን ‹‹ኢትዮፒክ›› ኢትዮጵያ በሚለው በመተካት ‹‹የኢትዮጵያዊው ሄኖክ መጽሐፍ›› ማለታቸው አልቀረም፡፡ (በቅርቡም አንድ ተርጓሚ ‹‹The Ethiopian Book of Enoch›› [የኢትዮጵያው/ግዕዝ መጽሐፈ ሄኖክ] የሚለውን ‹‹ኢትዮጵያዊው ሄኖክ›› ሲሉ አስቀምጠውታል፡፡ )በየመጽሐፋቸው፣ በየክታባቸው፣ በየጡመራ መድረካቸው ይህንን ሲያንፀባርቁ ይስተዋላል፡፡ ይህንን አገላለጽ ከሚቃወሙት ምሁራን አንዱ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ናቸው፡፡ በቅርቡ ባሳተሙት ስለ ግዕዝ ሥነ ጽሑፍ የተሰበሰቡ ማስታወሻቸው እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡

- Advertisement -

“መጽሐፈ ሄኖክ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱን ዓለም በአድናቆት ሲናገር የሰሙ አንዳንድ ወጣቶች ራሱን ነቢዩን ሄኖክን ሳይቀር ኢትዮጵያዊ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ሄኖክም ሆነ መጽሐፈ ሄኖክ ኢትዮጵያዊነት የለባቸውም፡፡”

እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው አገላለጽ፣ ‹‹ለምንድነው እነዚህ መጻሕፍት እኛ ዘንድ ሲኖሩ ከሌላው ዘንድ የጠፉት? እያንዳንዱ አገር የራሱ ታሪካዊ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ የሃይማኖት ጭቅጭቅ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ክርስትና ከአይሁድ ሃይማኖት የተለየበት ዘመን የፈተና ዘመን ነበር፡፡ ወንጌሉ እንደሚለው ክርስቶስ ‹‹የእርሱ ወደሆኑት መጣ፣ ግን የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም›› ካልተቀበሉ ‹‹ክርስትና›› የሚባል ሌላ ሥርዓት ሊቋቋም ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ፣ ሐዋርያትና የእነሱ ተከታዮች ሊቃውንት ያንን አዲስ ሥርዓት መልክ ለማስያዝ የየራሳቸውን ሐሳብ የያዘ ጽሑፍ ያቀርቡ፣ የተለየ የኋለኞቹ ከዚያም አልፈው አንዱ የሌላውን ጽሑፍ ከእነመረጃው ምንጩ ያጠፉ ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ከመጥፋታቸው በፊት ወደ ግዕዝ ተተርጉመው እኛ ዘንድ በሰላም ይኖራሉ፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ለክርስትና ሃይማኖት ታሪክ የሚፈለጉ ዋና ምንጮች ናቸው፡፡    

‹‹የመጽሐፈ ሄኖክ መግቢያ››

መሰንበቻውን ምዕዛር የተባሉ ባለሙያ ‹‹የመጽሐፈ ሄኖክ መግቢያ›› የሚል በጥናት ላይ የተመሠረተ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ የመጽሐፉ ትኩረት ከግዕዙ መጽሐፈ ሄኖክ በተጨማሪ በስላቭ የተጻፈው ‹‹መጽሐፈ ሄኖክ›› (Slavonic Enoch)፣ ‹‹መጽሐፈ ሄኖክ ሣልስ›› (የአይሁዳውያን ትውፊት)፣ እንዲሁም በቅዱስ ቁርዓንና በትውፊት ኢድሪስ ተብሎ ስለሚታወቀው ሄኖክ መግለጫ አቅርቧል፡፡

እንደ ደራሲው ማብራሪያ ‹‹የመጽሐፈ ሄኖክ መግቢያ›› ከመጽሐፈ ሄኖክ ውቅያኖስ ውስጥ የጠብታ ያህል እንኳን የማትሆን ጥናት ስትሆን፣ በመጽሐፉ ዙሪያ አንዳንድ ጭብጦችን ለማሳየት ብቻ ግን ሙከራ ታደርጋለች፡፡ መጽሐፉ በስድስት ምዕራፎች የሚከፈል ነው፡፡ ስለ ሕይወተ ሄኖክና መጽሐፉ አጠር ያለ ዳሰሳ፣ ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ትውፊተ ሄኖክ በአገር በቀል የግዕዝ መጻሕፍት ውስጥ ያለው ሚና ምን እንደሚመስል የገድለ ቅዱስ ላሊበላንና የዜና እስክንድርን መጽሐፍ መሠረት በማድረግ ለማየት ይሞክራል፡፡ እንዲሁም የመጽሐፈ ሄኖክ ከሌላው የአይሁድ ሃይማኖትም ይሁን ከክርስትና ክበብ ለዘመናት መጥፋትና ተጠብቆ አለመኖር ምክንያት ይቃኛል፡፡

ምዕዛር፣ መጽሐፈ ሄኖክ በሌላው ዓለም ጠፍቶ ሳለ በኢትዮጵያ መገኘቱ ራሱን የቻለ አንድምታ ያለው ክስተት ነው ይሉታል፡፡ ከዚህም በላይ በሌሎች ቀደምት የግዕዝ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ መጻሕፍት ውስጥ ሄኖክና መጽሐፉ ያላቸው ሚና ሲመረመር በእርግጥም የመጽሐፉ ተጠብቆ በኢትዮጵያ የመኖሩ ክስተት የአጋጣሚ ነገር ብቻ ሳይሆን ሥርና መሠረት ያለው ባህለ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችንም እንደ አሻራ ማስቀረቱን፣ ከዘመን ቀመር ጀምሮ እስከ ነገረ ዕውቀት (ኢፒስቶሞሎጂ) እና ሌሎችም የባህለ ሃይማኖት ርዕዮቶች ውስጥ ያለው ጥልቅ ትስስር በተለይም ግምት ውስጥ ገብቶ ሊታይ የሚገባው የጥናት ትኩረት መሆኑን ምዕዛር ይገልጻሉ፡፡

የመጽሐፈ ሄኖክ ባህር ማዶ መሻገር

መጽሐፈ ሄኖክ በአሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ ሐሣሤ ምድሩ (Explorer) ጄምስ ብሩስ ሦስት የመጽሐፈ ሄኖክን የግዕዝ ቅጂዎች ወደ ምዕራቡ ዓለም በመውሰድ ህልውናውን ከማስተዋወቁ በፊት፣ ስለ መጽሐፉ ከቃል ትውፊት በዘለለ የሚታወቅ ነገር እንዳልነበረ የመጽሐፉ መግቢያ ያመለክታል፡፡

እንደ ምዕዛር አገላለጽ፣ ምዕራባውያን መጽሐፈ ሄኖክን ያገኙ አየመሰላቸው አፍልሰዋል፣ መዝብረዋል፡፡ በሃያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይም ትንግርት በሚመስል ሁኔታ በይሁዳ በረኻ ቁምራን በተባለ ዋሻ አካባቢ ከስምንት መቶ በላይ ጥቅልል መጻሕፍት ተገኙ ሲባል፣ ከግኝቶቹ መካከል ውስጥ ግንባር ቀደም የሆነው በአራማይክ የተጻፈው የመጽሐፈ ሄኖክ ቁርጥራጭ ቅጂ ጽሑፍ ይገኝበታል፡፡

ይሁን እንጂ በቁምራን የተገኘው የመጽሐፈ ሄኖክ የአራማይክ ቅጂ ሙሉው ክፍል ሊገኝ የቻለው በግእዙ የመጽሐፈ ሄኖክ ቅጂ ላይ በመሆኑ፣ የግእዙ መጽሐፈ ሄኖክ የጥናት ትኩረት መስህብ ለመሆን ችሏል፡፡

በአሁን ጊዜም መጽሐፉ በተለይም በሁለተኛው ቤተ መቅደስ የይሁዲ ጥናት ውስጥ፣ ማለትም በግሪካውያንና ሮማውያን ዘመን በአራተኛው መቶ ዓመተ ዓለም ውስጥ የነበረውን የአይሁዳውያንን የሥነ ጽሑፍ ክበብ ለመረዳት ምናልባትም ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠውና ጠቃሚ የጥናት ትኩረት ለመሆን እንደቻለ አሁን ላይ ያሉ የዘርፉ ተመራማሪዎች አስተያየታቸውን መስጠታቸውን ምዕዛር ያብራራሉ፡፡

‹‹ከዘርፉ ምሁራን መካከል በተለይ ዮሴፍ ሚሊክ (Jozef T.Milik) የተባለ ተመራማሪ እ.ኤ.አ. በ1976 ባሳተመው የቁምራን ቁርጥራጭ ጽሑፎች ውስጥ፣ መጽሐፈ ሄኖክ በሁለተኛው ቤተ መቅደስ አካባቢ የተጻፉ የአይሁድ ስብስብ የጽሑፍ ሥራዎች ውጤት እንደሆነ ግምቱን አንፀባርቋል፡፡ በመቀጠልም በመጽሐፈ ሄኖክ ውስጥ ያለው ሥነ ጽሑፋዊ ሐሳብ በይሁዲ ሁለተኛ ቤተ መቅደስ ዘመን የነበረ የልዩ ሃይማኖታዊ ንቅናቄ ዋና ማዕከል እንደሆነ ምሁራኑ የተስማሙበት ጉዳይ ለመሆን ችሏል፡፡

‹‹እንዲሁም መጽሐፈ ሄኖክ በሁለተኛው ቤተ መቅደስ ዘመን ለነበሩት አቡቀለምሲሳዊ ጽሑፎችም (Apocalyptic Literatures) ያበረከተው ሚና ከሚጠኑት መስኮች አንዱ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና መተርጉማን በተቃራኒም (ሄኖክ ራሱ እንደጻፈው ስለሚታመን) የምዕራባውያን አጥኚዎች መጽሐፈ ሄኖክ የተጻፈውም ምናልባትም ከአንድ በላይ በሆኑና በሁለተኛው ቤተ መቅደስ አካባቢ ይኖሩ በነበሩ የካህናት ቡድኖች ሳይሆን አይቀርም የሚል መላምት የሚሰነዝሩ ሲሆን፣ እነዚህ ካህናትም በእነርሱ ግምት በኢየሩሳሌም አካባቢ የነበረውን የመቅደስ ሥርዓትና ሁለንተናዊ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴን ይቃወሙ የነበሩ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...