Monday, February 26, 2024

ግልጽነት የሚሹት የፀጥታ ተቋማት ማሻሻያ ሥራዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አንድ ዓመት ከመንፈቅ በላይ ያስቆጠረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የአስተዳደር ዘመን በርካታ የማሻሻያ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን፣ የማስተካከያና የማሻሻያ ዕርምጃ የሚጠብቁ በርካታ ዘርፎችም እንዲሁ ተራቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን የመጡ ሰሞን በከፍተኛ ርብርብ የማሻሻል ሥራ እንደሚከናወንባቸው ከተናገሩዋቸው ዘርፎች መካከል፣ በተለይ የፍትሕ ዝርፉ ቅድሚያውን የወሰደ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በሒደቱም የሲቪል ማኅበራትና ከምርጫ ቦርድ አስተዳደር ጋር የተያያዙ አዋጆች ተሻሽለው ወደ ሥራ መግባታቸው የሚታወቅ ነው፡፡

በዚህ ዘርፍ እንደሚሻሻሉ ቃል የተገባላቸው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅና ላለፉት በርካታ ዓመታት ዜጎችን ለእስር ሲዳርግ የነበረው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ፣ በተገባው ቃል መሠረት ማሻሻያቸው ተጠናቅቆ ሥራ ላይ አለመዋላቸው አሁንም ጥያቄ ይነሳበታል፡፡

ከዚሁ የፍትሕ ዘርፍ እኩል አትኩሮት የተቸረው የፀጥታ ተቋማት ማሻሻያ ሥራም እየተከናወነ መሆኑ ሲገለጽ ሰንብቷል፡፡ ከእነዚህ ማሻሻያዎች መካከል በተለይ የደኅንነት ተቋማትን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ለማድረግ ሲባል የተቋሙ አባላት፣ ወይ ፖለቲካውን ወይም የደኅንነት ሙያውን መምረጥ የግድ እንደሚላቸው መወሰኑ አይዘነጋም፡፡

ምንም እንኳን የደኅንነት ተቋማትን የማሻሻልና የማስተካከል ዕርምጃዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ቢገለጽም፣ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ ተቋማቱ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት አመራሮችና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ቢጎበኘም፣ እየተከናወነ ያለው የማሻሻያ ሥራ እንዴት እየተከናወነና ማን እያከናወነው እንደሆነ የሚያሳዩ ግልጽ መረጃዎች ለሕዝቡ እየደረሱ አይደለም በማለት፣ የተለያዩ የስሞታ አስተያየቶችን የሚያሰሙ በርካታ የዘርፉ ምሁራንና የፖለቲካ ልሂቃን አልታጡም፡፡

ዓርብ ታኅሳስ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ተቋም፣ ‹‹የፀጥታ ተቋማት በፖለቲካ ሽግግር ውስጥ›› በሚል ርዕስ በርካታ የዘርፉ ምሁራን፣ የቀድሞና የአሁን የዘርፉ ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም ሌሎች ተሳታፊዎች የተካፈሉበት የግማሽ ቀን ውይይት አካሂዶ ነበር፡፡

ይህ የተቋሙ የውይይት መድረክ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የዋለልኝ መኮንን ጽሑፍ 50ኛ ዓመትን አስመልክቶ ተመሳሳይ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በቀጣይም በየወሩ አገራዊ ፋይዳቸው የጎሉ የውይይት መድረኮችን በቋሚነት እንደሚዘጋጅ በወቅቱ ተገልጿል፡፡

ባለፈው ዓርብ የተካሄደው የፀጥታ ተቋማትን የተመለከተው የውይይት መድረክ ዘርፉን በተግባርም ሆነ በጥናትና ምርምርም በሚገባ የሚያውቁት ተሳታፊዎች የተገኙበት ሲሆን፣ ውይይቱም በዋነኛነት በለውጥ ሒደት ውስጥ ለውጡ ሳይንገራገጭ እንዲቀጥል የፀጥታ ተቋማት ሚና ምን መሆን አለበት የሚሉ የምክረ ሐሳቦች የጎሉበትና የተሰነዘሩበት ነበር፡፡

በዚህ የውይይት መድርክ ላይ ከመንግሥት ወገን እየተካሄደ ስላለው የፀጥታ ተቋማት የለውጥ ሒደትን አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጻ ያደረጉና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ የቀድሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ሌተና ጄኔራል ገብረ ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ ደግሞ ካካበተ ልምዳቸውና ከንባባቸው የተቀዱ ለውጡ ከፀጥታ አንፃር እንዴት መመራት ይኖርበታል በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዮናስ ኦዳዬ (ዶ/ር) ደግሞ የፀጥታና የደኅንነት ጉዳዮችን የተመለከቱ ሀልዮታዊ ምልከታቸውን አካፍለዋል፡፡

የሦስቱን ባለሙያዎች ገለጻና ማብራሪያ ተከትሎ ደግሞ በውይይቱ የተሳተፉ ታዳሚዎች፣ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ የፖሊሲ ግብዓቶችና አስተያየቶች ለግሰዋል፡፡

በዚህም መሠረት የመጀመርያውን ገለጻ ያደረጉት ዮናስ ኦዳዬ (ዶ/ር) የፀጥታ ተቋማት በፖለቲካ ሽግግር ውስጥ የሚለውን ጉዳይ በዝርዝር የተመለከቱት በሀልዮት (Theory) ደረጃ በመመርኮዝ ሲሆን፣ ከዚህ አንፃር በዘርፉ የተጻፉ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችንና ድርሳናትን በማጣቀስ የፀጥታ ተቋማት በሽግግር ወቅት ሊገጥማቸው የሚችለውን ፈተና፣ ፀጥታ የሚለው ሐሳብ ራሱ የሚቆምባቸው ምሰሶዎችና የፀጥታ ተቋማት ሲሻሻሉ ሊከተሉት ስለሚገባው መርህ አብራርተዋል፡፡

የፀጥታ ሥጋት ጽንሰ ሐሳብ የሚቆምባቸውን ሦስት መሠረታዊ ምሰሶዎችን በተመለከተ፣ አንደኛው የሥጋቱ ተጠቂ ማን ነው የሚለው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የፀጥታ ሥጋት አለ ሲባል የሥጋቱ ተጠቂ የሚሆነው መንግሥት ነው? ሕዝቡ ነው? ወይስ አገዛዙ? የሚለውን ለይቶ ማወቁ ተቋማቱን ለማሻሻልም ሆነ ተገቢውንና ሕጋዊውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡

ሌሎቹ ሁለት ምሰሶዎች ደግሞ የሥጋቱ ምንጭ ምንድነው? የሚለውንና ከሥጋቱ መውጫ መንገድ ምንድነው? የሚለው መለየት መሆኑን በመግለጽ፣ ከተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች አንፃር የፀጥታ ሥጋት ምሰሶዎችን አቅርበዋል፡፡

የፀጥታ ዘርፉ ሲሻሻል ሊከተለው የሚገባውን መርህ በተመለከተ ደግሞ በዋነኛነት ሕዝብን ማዕከል ያደረገና ሲቪሎች ሊቆጣጠሩት የሚችሉት መሆን እንደሚኖርበት ገልጸው፣ በተጨማሪም ተቋማቱን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ቁጥጥር የሚደረግበት፣ ከጊዜው ጋር አብሮ የሚራመድ፣ ቅቡልነት ያለውና በግልጽነት የሚመራ መሆን እንደሚኖርበትም አውስተዋል፡፡

እነዚህ ሁሉ መርሆዎችና ምሰሶዎች አስፈላጊ የሚሆኑበት ምክንያት ደግሞ፣ የፀጥታ ተቋማት ማሻሻያ ሥራዎች ዋነኛ ዓላማና ግብ ልማትን ለማፋጠንና ዕድገትን ለማምጣት የሚሠራ ሥራ ከመሆኑ አንፃር መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ስለሆነም የአንድ አገር አጠቃላይ ደኅንነትና ፀጥታ የበርካታ ተቋማት ትስስርና ደኅንነት ከመሆኑ አንፃር የየዘርፉን ተዋናዮች በመለየትና በማሳተፍ የማሻሻያ ሥራዎች በግልጽነት ማከናወን ማለት፣ የአገርን ልማትና ዕድገት ማረጋገጥ ሊሆን እንደሚችል ታሳቢ መደረግ እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡

የእሳቸውን ወደ ሀልዮት ያዘነበለ ማብራሪያ ተከትሎ ሐሳባቸውን ያቀረቡት የቀድሞ ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ሌተና ጄኔራል ገብረ ፃድቃን ደግሞ፣ ለፀጥታ ተቋማት ማሻሻያ የሚደረገው ለምንድነው? የደኅንነት ተቋማት የሚባሉት ማን ናቸው?  በሚባሉት ጉዳዮች ላይ የተፈተነ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

የፀጥታ ተቋማት በፖለቲካ ሽግግር ወቅት ከማንኛውም ተቋም በላይ ራሳቸውን ማሻሻል እንደሚጠበቅባቸው አሳስበው፣ የዚህም ዋነኛ ምክንያት ዘርፉ በባህሪው ለሥልጣን ቅርብ በመሆኑ እንደሆነ አውስተዋል፡፡

‹‹የመጀመርያው ጉዳይ በፖለቲካ ሽግግር ወቅት የደኅንነት ተቋማቱ መሻሻል አለባቸው፡፡ ምክንያቱም የደኅንነት ተቋማት ከማንኛውም ተቋም በላይ ወደ ፖለቲካ ሥልጣን በጣም በጣም የቀረቡ ናቸው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ አስተሳሰቦች አስተዳደሩ ሲለወጥ እነሱም መለወጥ አለባቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት የሚቋቋሙት አንድን የፖለቲካ ዓላማ በደኅንነት ሥራ ተግባር ላይ ለማዋል ነው፡፡ ስለዚህ ከሒደቱ ጋር መስማማት አለባቸው፤›› ብለው፣ በሽግግር ወቅት ዘርፉን ማሻሻል ለነገ የማይባል ሥራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የእሳቸው ገለጻ ከልምዳቸው፣ ከትምህርትና ከንባብ የተቀዳ መሆኑን በማስረዳት ትኩረታቸው ከፍ ባሉ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳን ከልምዳቸው በመነሳት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ቢሰጡም፣ አሁን እየተካሄደ ስላለው የዘርፉ ማሻሻያና ለውጥ ግን ከተባራሪ ወሬዎች በዘለለ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው በመግለጽ በጉዳዩ ላይ ግልጽነት ሊኖር እንደሚገባ ምክር ለግሰዋል፡፡

የተለያዩ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ሐሳብ ያቀረቡት ዮናስ (ዶ/ር) ቀደም ብለው እንደገለጹት፣ የፀጥታ ተቋማት ማሻሻያዎች ግልጽነት ዋነኛ መርህ ከመሆናቸው አንፃር ከመድረኩ ታድመው የነበሩ ተሳታፊዎችም ተመሳሳይ ሐሳቦችን አንፀባርቀዋል፡፡

‹‹መንግሥት የለውጥ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ወሬውን ነው እንጂ የምሰማው ምን ዓይነት ለውጥ እያደረገ እንዳለ የማውቀው መረጃ የለኝም፤›› በማለት፣ በሒደቱ መረጃ የማግኘት ክፍተት እንዳለ በመጥቀስ አሳታፊ የሆነ አሠራር ቢዘረጋ መልካም መሆኑን ሌተና ጄኔራሉ አሳስበዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም አብዛኛውን ጊዜ በደኅንነት ተቋማት ላይ ንግግር ሲኖር ቀድሞ ወደ አዕምሮ የሚመጣው መከላከያ፣ ፖሊስ፣ እንዲሁም ደኅንነት እንደሆነ በማስታወስ፣ የማሻሻያ ሥራዎችም በዚህ ዙሪያ ሊያጠነጥኑ እንደሚችሉ ግምት እንደሚወሰድ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን የሲቪል ሠራተኞችም ቢሆኑ የማሻሻያ ሥራው አንድ አካል መሆን እንደሚገባቸው፣ ‹‹ዘርፉን ለመምራት የተቀመጡ ወይም የተሾሙ ግለሰቦች አብረው መለወጥ አለባቸው፤›› በማለት፣ ሁሉን አቀፍ የማሻሻያ ሥራዎች ማከናወን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በፖለቲካ ሽግግር ውስጥ የሚገኝ አንድ የፀጥታ ተቋም ማሻሻያዎችን ይሠራል ሲባል ሊያሟላቸው የሚገባውን ነጥቦች አነስተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የማሻሻያ ሥራ ስኬት መለኪያ አስተዳደራዊ ውጤታማነት፣ ሀብት ቆጣቢ መሆን፣ ቅቡልነት ማግኘት፣ እንዲሁም ተጠያቂነት ማስፈን የሚሉት እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን የደኅንነት ፖሊሲዎች ሲዘጋጁ ግልጽ መሆን እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተው፣ ሐደቱም ሁሉንም የሚያሳትፍ መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

የአገር ደኅንነት ሲባል ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ከመሆኑና ከዚህ ቀደም ከነበረው ባህላዊ ብያኔ ውጪ፣ ማለትም የአገርን ዳር ድንበር ማስከበር ከሚለው ከፍ የሚልና የግለሰቦችን ደኅንነት የሚጠብቅ ከመሆኑ አንፃር ግልጽነትና አሳታፊነት የሚለውን አስተያየት ብዙዎች የተጋሩት መሆኑን ከሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡

እየተካሄደ ያለውን የፀጥታ ተቋማት ማሻሻያ መነሻ ምክንያቶችን ያቀረቡት አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፣ ማሻሻያው ያስፈለገው ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በመኖሩ ያነሰ ሙያዊ ብቃት፣ የተፍረከረከ መዋቅር መኖር፣ የጠበበ የብሔራዊ ደኅንነት ብያኔ፣ ተጠያቂነት አለመኖርና ተቋማዊ ትስስር ወይም ቅንጅት አለመኖር የሚሉት ችግሮች በመለየታቸው እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በተለይ ተቋማዊ ግንኙነት ወይም ቅንጅት አለ ከተባለ ሥርዓታዊ ሳይሆን፣ ጓዳዊ እንደነበር በመጥቀስ በዚህ ምክንያት ባለሙያዎቹና ተቋማቱ ወይ ይተባበራሉ ወይም ይፎካከራሉ በማለት ከዚህ ቀደም የነበረውን አሠራር አውስተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ተቋማቱን በአስተሳሰብም ሆነ በአደረጃጀት እንዲሻሻሉ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በመግለጽ፣ ነገር ግን ፖሊሲ ከማውጣት በፊት ተቋማቱ ከዚህ ቀደም ከነበሩበት የከፋ ችግር ለማላቀቅ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሠራ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ከማሻሻያ ሥራዎቹ ጎን ለጎንም የደኅንነት ፖሊሲውን ለማሻሻልም የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ለግማሽ ቀን በተካሄደው ‹‹የፀጥታ ተቋማት በፖለቲካ ሽግግር ውስጥ›› በሚለው መርሐ ግብር ላይ የተለያዩ ሐሳቦች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ በአብዛኛው ግን ከዚህ ቀደም የነበሩ ስህተቶችን ላለመድገም የመንግሥት ግልጽነት አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቁሙ ድምፆች ጎልተው ነበር፡፡ እየተካሄደ ያለውን ዘርፉን የማሻሻል ሥራ አስመልክቶ የሚመለከተው አካል መረጃዎችን ይሰጣል የሚል ተስፋን የሰነቁ በርካቶች ናቸው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -