[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር?
- የት አለ ሪፖርቱ?
- የትኛው ሪፖርት?
- ሥራውን እርግፍ አድርገህ ትተኸዋል ልበል?
- ኧረ በፍፁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምርጫ ዓመት መሆኑን ረሳኸው እንዴ?
- እንዴታ ክቡር ሚኒስትር?
- ታዲያ የትኛው ሪፖርት እንዴት ትለኛለህ?
- እ…
- ሲሆን እኮ በየደቂቃው ነው ሪፖርት ማድረግ ያለብህ፡፡
- እሱስ ልክ ነዎት፡፡
- ይኸው ባለጋራዎቻችንም እየተጠናከሩ ነው፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ያው አንዳንድ ፓርቲዎች ልክ እንደ እኛ ራሳቸውን ለማጠናከር እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡
- የሰሞኑን ዜና ሰምተው ነው?
- እህሳ፡፡
- ለእኔ እንኳን ያደረጉት አይቅርብኝ አካሄድ ነው፡፡
- እንዴት?
- ከመቼ ጀምሮ ነው ውኃና ዘይት የሚቀላቀለው?
- እ…
- ክቡር ሚኒስትር ሩጫው ሁሉ ለአንድ ነገር ሆኗል፡፡
- ለምን?
- ነጥብ ለማስቆጠር ነዋ፡፡
- ቢሆንም ሁሉን ነገር በትኩረት መከታተል አለብን፡፡
- ስለዚህ ጉዳይ ፈፅሞ ሥጋት አይግባዎት፡፡
- ለምን አይገባኝም?
- ከመዋሀዳቸው ተጣሉ የሚል ወሬ መውጣቱ አይቀሬ ነው፡፡
- ለማንኛውም ጥንቃቄ ማድረጉ አይከፋም፡፡
- እሱማ ትክክል ነው፡፡
- ለመሆኑ የሰጠሁህን የቤት ሥራ ሠራህ?
- የመሬቱን ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሌላ ምን የቤት ሥራ አለህ?
- ይመልከቱት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድነው ይኼ?
- የመሬቶቹ ዝርዝር ነው፡፡
- እ…
- በየክፍለ ከተማው ለይቼ አዘጋጅቼያቸዋለሁ፡፡
- ሳተና ነህ እኮ አንተ፡፡
- ከዚህ በላይ ምን አለ ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሌላው ሥራ ላይም እንዲህ ንቁ ብትሆን ጥሩ ነው፡፡
- በመሬት አይቀለድም ብዬ እኮ ነው፡፡
- እሱማ ልክ ነው፡፡
- ይኸው እንዳዘዙኝ ኪስና ግንባር ቦታዎቹም ተለይተዋል፡፡
- አንተ ሥራህን ጨርሰሃል በቃ፡፡
- ስምን መላክ ያወጣዋል ማስባል አለብን፡፡
- የማንን ስም?
- የፓርቲያችንን ነዋ፡፡
- በመሬት ሽያጩ መበልፀጋችን አይቀርም ብለህ ነው?
- ምን ጥያቄ አለው ክቡር ሚኒስትር?
- በቃ ለማንኛውም እሱን ሪፖርት ስጠኝና ያን ደላላ ላግኘው፡፡
- ከዚህ በኋላ ድምፃችንን አጥፍተን እነዚህን መሬቶች ምን እንደምናደርግ ያውቃሉ?
- ምንድነው የምናደርጋቸው?
- እንቸበችባቸዋለን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ደላላ ወዳጃቸውን ደውለው ቢሮ ጠሩት]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር?
- እንቅስቃሴ እንዴት ነው?
- ሰው ፈርቷል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድነው የሚያስፈራው?
- ምርጫው መሰለኝ፡፡
- ምኑ ያስፈራል ብለህ ነው?
- ይደረጋል አይደረግም ከሚለው ጀምሮ ማን ይመጣል የሚለው ነዋ?
- መደረጉማ አይቀሬ ነው፡፡
- ማን ነው የሚመጣውስ?
- ምን ጥያቄ አለው?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እኛው ነና፡፡
- ምርጫው እንደ ድሮው ዓይነት ምርጫ ነው እንዴ?
- እንደ ድሮው ዓይነት ስትል?
- የይስሙላ ምርጫ ነዋ፡፡
- እንደ እሱ ዓይነትማ በፍፁም አይሆንም፡፡
- ያው እኛ ነን የምናሸንፈው ሲሉኝ ነዋ፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ማለቴ የምርጫ ውጤቱ አስቀድሞ ከታወቀ ብዬ ነው፡፡
- እሱማ ግልጽ ነው፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እኛ ነን የምናሸንፈው አልኩህ እኮ፡፡
- ብትሸነፉም ልታጭበረብሩ አስባችኋል እንዴ?
- አልወጣኝም፡፡
- ታዲያ ምን እያሉኝ ነው?
- ከእኛ ውጪ ማን ይመረጣል ብለህ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር አሁን እኮ ነፍስ ያላቸው ተፎካካሪዎች እየመጡ ነው፡፡
- እ…
- ይኼ ዴሞክራሲ የምትሉትን ነገር አስቡበት ስል የነበረው እኮ ለዚህ ነው፡፡
- እንዴት?
- ሰው ምርጫ ከተሰጠው ሌላ ሊመርጥ ይችላል፡፡
- እ…
- ለእኔና ለእርስዎ ዓይነቱ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ ነገር አደጋ ነው፡፡
- ማለት?
- ሰው በጣም ነዋ የሚጠላን፡፡
- ለምን?
- ያው ሲጀመር አቅም እንደሌለን ግልጽ ነው፡፡
- ሲቀጥልስ?
- ሲቀጥል ደግሞ ሌቦች እንደሆንን የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
- እና ምርጫው ቢቀር ይሻላል እያልከኝ ነው?
- እሱ እንኳን ከባድ ነገር ይመስለኛል፡፡
- ታዲያ ምን ተሻለ?
- ባይሆን የመሬቷን ፕሮጀክት ቶሎ እናስፈጽማት፡፡
- እ…
- ክፍት ቦታዎችን ከምርጫው በፊት እንቸብችባቸውና እንውሰድ፡፡
- ምንድነው የምንወስደው?
- የድርሻችንን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ባለሀብት ጋር ቢሯቸው ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- ዛሬ መደወልዎ አስገርሞኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ አስገረመህ?
- ያው በጣም ቢዚ ስለሚሆኑ ብዬ ነው፡፡
- ሕዝቤን ከማገልገል ግን ቢዚ ሆኜ አላውቅም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ለዘላለም መንገሥ አለብዎት፡፡
- የአንተ ዕርዳታ ካልተለየኝ መቼ ይቀራል ብለህ ነው?
- ሁሌም ከጎንዎ ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የፓርቲያችን ደጋፊ መሆንህን ሰምቻለሁ፡፡
- ምን ጥርጥር አለው?
- ለነገሩ አንተ የገዥው ፓርቲ ደጋፊ ነህ አሉ፡፡
- እ…
- ያው እኛም ብንሸነፍ የቀጣዩ ገዥ ፓርቲ ደጋፊ መሆንህ አይቀርም፡፡
- ኧረ በፍፁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ከዚህ ቀደም የበፊቶቹ ቀንደኛ ደጋፊ አልነበርክ እንዴ?
- ምን መሰለዎት?
- ችግር የለም አታስረዳኝ ጥቅም አሳዳጅ መሆንህን አውቃለሁ፡፡
- እኔ እንደዚያ ዓይነት ሰው አይደለሁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ዛሬ የጠራሁህ ጥቅመኛ ነህ ብዬ አስቤ ላነጋግርህ ነው እኮ፡፡
- ማለት?
- እንድንጠቃቀም አስቤ ነዋ፡፡
- ምን ችግር አለው ክቡር ሚኒስትር?
- ስለዚህ ጥቅመኛ ሰው ነህ ማለት ነው?
- እውነቱን ንገረኝ ካሉማ በእሱ የታወቅኩ ነኝ፡፡
- ለአሁኑ እኔም የምፈልገው ጥቅመኛ የሆነ ሰው ነው፡፡
- ምን ልታዘዝ ታዲያ?
- እንደ አንተ ጥቅመኛ የሆኑ ባለሀብቶችን እንድታደራጅልኝ እፈልጋለሁ፡፡
- ምን ችግር አለው ክቡር ሚኒስትር?
- እሱን ማድረግ ትችላለህ?
- በቃኝ እስኪሉ የጥቅመኛ መዓት ማደራጀት እችላለሁ፡፡
- ምርጫዬ ትክክል ነበር ማለት ነው?
- ትክክለኛ ሰው ነው ያገኙት ስልዎት?
- ስማ የቀጣዩ ምርጫ ውጤት አይታወቅም፡፡
- እኔ አውቀዋለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት?
- እናንተ ነዋ የምታሸንፉት፡፡
- አንተ ጥቅመኛ ስለሆንክ ለአንተ ብዙ ችግር አይኖረውም፡፡
- እ…
- ለማንኛውም ከተማ ውስጥ ያሉ ዓይን ዓይን ቦታዎች በእጄ ናቸው፡፡
- እሺ፡፡
- ስለዚህ ከምርጫው በፊት እነዚህን ቦታዎች ከእጄ ማውጣት እፈልጋለሁ፡፡
- ምን ልርዳዎት ታዲያ?
- የሚረከቡኝን ባለሀብቶች አደራጅልኛ?
- ደስ እያለኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስም ዝርዝራቸውን ስጠኝና ካርታው ይዘጋጅላቸው፡፡
- እኔን ጨምሮ በርካታ የተራቡ ሰዎችን አዘጋጃለሁ፡፡
- ምን የተራቡ?
- መሬት!
[ክቡር ሚኒስትሩ በሌላ ሚኒስትር እየተገመገሙ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር ሁሉን ነገር ደርሰንበታል፡፡
- ምን አደረግኩ?
- እርስዎን እንጠይቅዎት እንጂ?
- ጠይቁኛ?
- እኮ ይመልሱዋ?
- ምኑን ልመልስ?
- የመሬቱን ጉዳይ?
- እ…
- ምነው ተንተባተቡ?
- ኧረ አልተንተባተብኩም፡፡
- ይንገሩና?
- ምን ልንገራችሁ?
- መሬት በምን አግባብ እየሰጡ እንደሆነ እናውቃለን፡፡
- እንዲያለሙበት እኮ ነው የሰጠኋቸው፡፡
- እርስዎ እንዲለሙበት ማለትዎ ነው?
- እ…
- መሬት የሕዝብ ሀብት መሆኑን ረሱት እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ኧረ በፍፁም፡፡
- ከአዲሱ ፓርቲያችን አካሄድ ጋር የሚጋጭ ድርጊት በመፈጸምዎ በሕግ ይጠየቃሉ፡፡
- እ…
- ያልተገባ ድርጊት ፈጽመዋል፡፡
- ምን አጠፋሁ?
- በከፍተኛ ሁኔታ ነዋ የበለፀጉት፡፡
- ይኼ ታዲያ የፓርቲያችን ፕሮግራም አይደል እንዴ?
- ምኑን ነው የፓርቲያችን ፕሮግራም?
- ብልፅግና፡፡
- የእርስዎ ብልፅግና አይደለማ፡፡
- ታዲያ ምንድነው?
- ብልግና!