የተሸኘው ዓመት 2019 በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዐቢይ ኩነት ሆነው ካለፉት መካከል ዓመታዊ በዓላት ይጠቀሳሉ፡፡ በኬሚስትሪ ትምህርት ‹ፔሪዮዲክ ቴብል› ተብሎ የሚታወቀው የኢለመንቶች ሰንጠረዥ 150ኛ ዓመት የልደት በዓል በ2019 ተከብሯል፡፡ ሌላው የኢዮቤልዩ ዓመት የመጀመርያዋ አፖሎ 11 ጨረቃ ላይ ያረፈችበት 50ኛ ዓመት ሲታሰብ፣ የሰው ልጅ ምርምሩ እስከ ሕዋ መድረሱ የተበሰረበት ነው፡፡
በሌላ በኩል በ2019 በአርኪዮሎጂ ዘርፍም በእስራኤልና በዮርዳኖስ ወደ 2000 ዓመት ዕድሜ የሚቀርቡ አብያተ ክርስቲያናትና መንደሮች፣ ለአምልኮት የሚያስፈልጉ የድንጋይ መንበሮች፣ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ተገኝተዋል፡፡ በሰሜን እስራኤል የቢዛንታይን ዘመን ቤተ ክርስቲያን 1,400 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲገኝ በአፈታሪክ ‹‹የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን›› እንደሚባል በላይቭ ሳይንስ ተዘግቧል፡፡
በሰባተኛው ክፍል ዘመን በጥንታዊ ሂፖስ ከተማ የነበረ ቤተ ክርስቲያን በእሳት ከወደመ በኋላ ደብዛው ጠፍቶ ነበር፡፡ አርኪዮሎጂስቶች በአካባቢው ባደረጉት ቁፋሮ የሞዛይክ ሥራ አግኝተዋል፡፡ ሞዛይኩ በአንድ በኩል አምስት ኅብስትና ሁለት ዓሳን፣ በሌላው ገጹ ቅርጫትን ያሳያል፡፡ ይህም በአዲስ ኪዳን የተጻፈው የእግዚእ ኢየሱስ 5000 ሰዎችን የመገበበትን ታሪክ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡
በኢትዮጵያም በቅርቡ ከአክሱም ሰሜን ምሥራቅ 30 ማይልስ ርቀት ላይ ቤት ሰማዕቲ በተባለ ቦታ ጥንታዊ ከተማና ቤተ ክርስቲያን መገኘቱ በቁፋሮው ተረጋግጧል፡፡ ከመዳብ የተሠራና የበሬ ምስል ያለው በወርቅ የተለበጠ ቀለበት፣ በድንጋይ ላይ የተጻፈ የግዕዝ ጽሑፍና ሌሎች ቁሳቁሶችም መገኘታቸው ተዘግቧል፡፡