Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልገና እና ‹‹ቤዛ ኲሉ››

ገና እና ‹‹ቤዛ ኲሉ››

ቀን:

በሔኖክ ያሬድ

ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችና በመላው ዓለም የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን (ገና) የሚያከብሩት ታኅሣሥ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ ዓምና ጳጉሜን 6 ስለነበረች ዘንድሮ ገናን ከታኅሣሥ 29 ወደ 28 አምጥቷታል፡፡

በዓለም ዙርያ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን በዓሉን ታኅሣሥ 28 ሲያከብሩ ዕለቱን በሚከተሉት የጁሊያን አቈጣጠር መሠረት ‹‹ዲሴምበር 25›› (በጎርጎርዮሳዊ ቀመር ጃንዋሪ 7) ብለው ነው፡፡ የግብፅ ኦርቶዶክስም እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ‹‹ኪያክ 28›› ቀን ብለው፣ ኤርትራም ‹‹ሐሳበ ግእዝ›› በምትለው አቆጣጠሯ ታኅሣሥ 28 ብላ በዓሉን ያከብሩታል፡፡

16ኛው ምዕት ዓመት ከጁሊያን ካላንደር ተከልሶ የተዘጋጀውን የግሪጎሪያን ካላንደር የሚከተሉት ምዕራባውያን ደግሞ እነርሱ ዲሴምበር 25 ባሉት 13 ቀናት በፊት ታኅሣሥ 15 ቀን አክብረውታል፡፡ በዓሉ አንድ ሆኖ የቀኑ ልዩነት የተፈጠረው መሬት ፀሐይን ለመዞር የሚፈጅባት ጊዜ በምሥራቆች 365 ቀን 6 ሰዓት ነው በማለታቸው ምዕራቦች ደግሞ 365 ቀን 5 ሰዓት 48 ደቂቃ 46 ሰከንድ ነው በሚል ልዩነት በመፈጠሩ ነው፡፡ 

ገና እና ‹‹ቤዛ ኲሉ››

በዓለ ልደት መቼ መከበር ጀመረ?

የልደት በዓልን አከባበር አስመልክቶ በተለያዩ ሊቃውንት የተጻፉ መረጃዎች እንዳሉ “በዓላት ምን? ለምን? እንዴት?” በሚለው መጽሐፋቸው ያተተቱት መምህር ብርሃን አድማሱ፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ዕለት የሚታወቀው በትውፊት ነው ይላሉ፡፡ “በመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖችና እስከ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ የልደት በዓል የሚከበረው ከጥምቀት በዓል ጋር በአንድነት በታኅሣሥ 29 ነበር፡፡ ከአራተኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ግን ከአርመን ቤተ ክርስቲያን በቀር በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ተለያይቶ ይከበር ጀመር፡፡”

ከአንደኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ክርስትና የተሰበከባት ኢትዮጵያ፣ እንደ ቀደምቱ ክርስቲያኖች በዓሉን ስታከብር ኖራለች፡፡ በተለይም መንበረ ጵጵስናን በአክሱም ከመሠረተችበት አራተኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ሥርዓትም አበጅታለች፡፡ በተከታታይ አዝማናት በዘጠኙ ቅዱሳንና በቅዱስ ያሬድ እስከነ ድርሰቶቹ ዜማዎቹ የልደቱን ክብር ከማጉላት ባሻገር ትውልደ ትውልድን ተሻግሮ ለዚህ ወቅት እንዲበቃ አድርጎታል፡፡

ክብረ በዓሉ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በሚገኙባቸው የዓለም ክፍሎች በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሲከበር ኖሯል፤ እየተከበረም ነው፡፡  

በታኅሣሥ 29 ሰዓተ ሌሊት ማለትም በ28 ማታ በቤተ ክርስቲያን ከሚኖረው አከባበር በተጨማሪ፣ ከሌሎች በተለየ መንገድ ልደቱ በቅዱስ ላሊበላ ከተማ በ29 ንጋት ላይ በውቅር አብያተ ክርስትያናቱ አማካይ ስፍራ በማሜ ጋራ “ቤዛ ኵሉ” በሚል መጠርያ ትርዒታዊ ሥነ በዓል አለው፡፡

የቤዛ ኵሉ ሥነ በዓል መቼ ተጀመረ?

ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ በ12ኛው ክፍለ ዘመን ከታነፁበት ዘመን አንስቶ በዓሉ በንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ ዘመን እየተከበረ ቢቀጥልም ንጋት ላይ በማሜ ጋራ ቤዛ ኵሉ (የዓለም ቤዛ) በሚል ማክበር የተጀመረው በአፄ ሰርፀ ድንግል ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባዘጋጀው የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ሰነድ ላይ እንደተገለጸው፣ ንጉሡ ሰርፀ ድንግል ሽልማት ይዘው ወደ ላሊበላ አድባራት ይመጣሉ ሲባል በወቅቱ የነበሩ አለቃ ኮከብ ዘላሊበላ የተባሉ የደብሩ ኃላፊ የቤተ ክርስቲያናቱን ቀሳውስት በማሜ ጋራው ላይና ታች አሠልጥነውና አሠልፈው እየተቀባበሉ ወረብ እንዲወርቡ አደረጉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በየዓመቱ ይህ ተግባር መከናወን እንደቀጠለና እዚህ ዘመን እንደደረሰ ይወሳሉ፡፡

ልደትን በተለይ በላሊበላ ለማክበር ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ምዕመናን ቁጥር በርካታ ነው፡፡ ከቅርብ አጎራባች ከተሞችና ገጠሮች ከሚመጡት አንዳንዶቹ ከሥፍራው የሚገኙት በእግር ተጉዘው ነው፡፡ በእግር የሚመጡበት ዋና ምክንያትም በአብዛኛው በረከት ለማግኘት እንደሆነ ይገለጻል፡፡

ተምሳሌታዊው ትርዒት

በበማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ሰነድ እንደተጠቆመው፣ የልደት በዓል ከመድረሱ በፊት በሚኖሩት ሦስት እሑዶች በኢትዮጵያ ሥርዓተ አምልኮ መሠረት እሑድ እሑድ ነቢያት የክርስቶስን መወለድ በተመለከተ የተነበዩትን ትንቢት የተመለከቱ ማህሌቶች ይቆማሉ፡፡ በመጀመርያ እሑድ ‹‹ስብከት›› የተባለው ቀለም ማለትም “ወልዶ መድኅነ ንሰብክ” የጌታችንን ልደት እናውጃለን (ነቢያት ስለክርስቶስ መወለድ ሰበኩ) የሚለው በያሬዳዊ ዜማ ይዜማል (ይወርባል) ይሸበሽባል፡፡ በሁለተኛው እሑድ እነዳዊት ስለክርስቶስ በተነበዩትና “ብርሃን” የተባለው ቀለም ማለትም ‹‹ብርሃን የሆነው ክርስቶስ ወደ ዓለም መጣ›› የሚለው ቀለም ይዜማል፡፡ በሦስተኛው እሑድ ኖላዊ (እረኛ) የተሰኘው ቀለም ማለትም ‹‹ኖላዊ ዘመጽአ ውስተ ዓለም ወልዱ ወቃለ ለእግዚአብሔር›› የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ወደዚህ ዓለም መጣ ለእኛ እረኛ ሊሆን›› የሚለው ቃል ይዜማል፡፡ በእነዚህ ቀናት የሚደረጉ ቅዳሴዎችም እነዚህኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎች የሚመለከቱ ይሆናሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ‹‹ዛሬ ስብከት ነው››፣ ‹‹ዛሬ ብርሃን ነው››፣ ‹‹ዛሬ ኖላዊ ነው›› እያሉ ሦስቱን እሑዶች የሚጠሯቸው፡፡

በየዐውደ ምሕረቱ የበዓሉ ድባብ መስፈን የሚጀምረው ከሳምንት ጀምሮ ቢሆንም ታኅሣሥ 26 ሌሊት፣ ታኅሣሥ 27 እና 28 ቀንና ሌሊት፣ እንዲሁም ታኅሣሥ 29 ጧት የቤዛ ኵሉ በዓል በሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት በዋነኛነት የሚከበርባቸው ቀናት ናቸው፡፡ ይኼም የሆነበት ዋና ምክንያት እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስን የተመለከቱ በዓላት በታኅሣሥ 27 (መድኃኔ ዓለም)፣ በታኅሣሥ 28 (አማኑኤል)፣ በታኅሣሥ 29 (የልደት በዓል) በተከታታይ ስለመከበሩ በታኅሣሥ 26 ማታ በቤተ መድኃኔ ዓለም ዋዜማ ከቀኑ ሦስት ሰዓት ጀምሮ እስከ 6፡30 ቅዳሴ እስኪገባ የዋዜማው ማህሌት ከሌላው ጊዜ በተለየ ሞቅ ባለ ሁኔታ ይቆማል፡፡

በዋዜማው ሌሊት በሚቆመው ማኅሌትም ከ300 በላይ የሚሆኑ ከሁሉም አካባቢዎችና ከአሥራ አንዱ አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ሊቃውንት በቤተ ማርያም ይሳተፋሉ፡፡ በማኅሌቱም እኒሁ ሊቃውንት በአራት ማዕዘን ክብ ሠርተው ይቆማሉ፡፡ ከመካከላቸውም 24 የሚሆኑ ጥንግ ድርብ (ካባ) የለበሱ ሊቃውንት ይመረጣሉ፡፡

‹‹ክርስቶስ መጽዐ ኅቤነ ውስተ ማኅፀን ድንግል ኅደረ (ክርስቶስ ወደ ዓለም መጥቶ በድንግል ማኅፀን አደረ)›› የተሰኘውን ወረብ ሲወርቡ በቤተ ማርያም ማሜ ጋራው ላይና ታች ያለው ሕዝብ በሙሉ ጧፍ ያበራል፡፡ እልል ይባላል፣ ሆታና ጭብጨባው ይድምቃል፡፡ ተምሳሌቱም በጨለማ ይኖር የነበረው ሕዝብ በክርስቶስ መምጣት ብርሃን አገኘ ለማለት ነው፡፡ አካባቢው በምዕመናኑ ነጭ አልባሳት በጧፍ ብርሃን ቅንጅት ደምቆና እጀግ ተውቦ ያድራል፡፡

ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በ11ዱ አብያተ ክርስቲያናት ያሉ ካህናትና ዲያቆናት በልብስ ተክህኖ ደምቀውና አሸብርቀው ሥዕል፣ መስቀል፣ ጥላና አፍሮ አይገባ መስቀል ይዘው ከየቤተ መቅደሳቸው በቤተ ማርያም በተለያዩ አቅጣጫዎች ባሉ በሮች ይገባሉ፡፡ ሁሉም በአንድ ላይ ሆነው ማሜ ጋራው ላይ ይወጣሉ፡፡

እነዚህ ለሁለት ተከፍለው ከላይና ከታች ተሠልፈው ቦታቸውን ከያዙ በኋላ ‹‹ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ›› የሚባለውን ወረብ መወረብ ይጀምራሉ፡፡ በዚህም የጌታን ውልደት በአቋቋምና በረገዳ በምሳሌ ያሳያሉ፡፡ እስከ አራት ሰዓት በሚፈጅ ክንውንም ሁሉም በእኩል እንቅስቃሴ ጸናጽላቸውን ወደላይ፣ ወደታች፣ ወደ ጎን እያደረጉ በአንድ ቋንቋና በአራቱም አቅጣጫ እየዞሩ ከላይ ያሉት ሦስት ጊዜ ‹‹ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ›› የዓለም ሁሉ ቤዛ ዛሬ ተወለደ ብለው ካዜሙ በኋላ  ይሰግዱና ታች ላሉት ያቀብላሉ፤ ታች ያሉትም ልክ እንደላይኞቹ ሦስት ጊዜ ይሄንኑ ቃል በዜማ ይሉና ሰግደው ለላይኞቹ ያቀብላሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ዕልልታውና ጭብጨባው ይደምቃል፡፡ ጥሩምባው ይነፋል፣ ርችት ይተኮሳል፡፡ ከበሮ መቺዎችም በቀሳውስቱ የፀናፅል አጣጣል ልክ ያሸበሽባሉ፣ ምታቸውም እንደዝማሬው ሥልት አብሮ ይፈጥናል፡፡

ከዚህ ሒደት በኋላ በዝማሬው ወቅት ከላይ ያሉት ካህናት ተምሳሌትነታቸው የመላዕክት ነው፡፡ ይህም ጌታ ሲወለድ በሰማይ መላዕክት አመስግነውታልና ነው፡፡ ከታች ያሉት ደግሞ የምድራውያን ኖሎትና ሰብአ ሰገል (የእረኞች) ምሳሌ ናቸው፡፡ ይህም ጌታ በተወለደበት ወቅት መላዕክት ለእረኞች ‹‹እነሆ በቤተልሔም ጌታ ተወልዶላችኋልና ሂዱና እዩ›› ብለው ሲያበስሯቸው እረኞች መዘመራቸውን ለማመልከት ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ሥርዓት ሰውና መላዕክት እግዚአብሔርን በአንድነት ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ›› በሰማይ ለእግዚአብሔር በምድር ለሰው ልጅ ሰላም ይሁን›› እያሉ የሚያዜሙበትና የሚያመሰግኑበት በዓል እንደሆነ የቤተ ክርስቲያናቱ ቀሳውስት ይናገራሉ፡፡

የቤዛ ኩሉ ሥነ ሥርዓት እንዳበቃ የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን ወደ ታች ወርደው መዘመር ይጀምራሉ፡፡ ምእመናንም በመሰባሰብ ክብ ሠርተው ዕልል እያሉና እያጨበጨቡ የሚከተሉትን የታቦት ዘፈን ይዘፍናሉ፡፡

ተው ማረኝና ላውራ ዝና

ቅዱስ ላሊበላ

ኧኸ. . .

አባቴ ነህና

ኧኸ. . .

ይምርሃነ ክርስቶስ

ኧኸ. . .

የሕይወቴ ፋና

ኧኸ. . .

በማሜ ጋራ ከሚኖረው አከባበር በተጨማሪ ምእመናንም በቆይታቸውም ዕለቱ የቅዱስ ላሊበላ የተወለደበት በመሆኑ እርሱንና ሥራውን ከበሮ እየመቱ እልል እያሉና እያጨበጨቡ ከሚያወድሱት መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፡፡

‹‹ቅዱስ ላሊበላ የላስታው ደብር

ውስጡ አረንጓዴ ነው ባህር

ከቶ እንዴት አድርጎ አነጸው

ከቶ እንደምን አድርጎ ሠራው

የመጥረቢያው እንኳን እጀታ የለው፡፡

ዓይኔ ዓለም አየ እግሬ ደርሶ

ዓይኔ ዓለም አየ እግሬ ደርሶ

የድንጋይ ወጋግራ የድንጋይ ምሰሶ፡፡”

ምዕመናኑ የሥነ በዓሉ ፍጻሜ ላይ ሲሰነባበቱ እንዲሁ አይደለም፡፡ የማሳረጊያ ዝማሬ አላቸው፡፡

“ከርሞ እንገናኝ ላመት

እናንተም ሳትሞቱ እኛም ሳንሞት

እንዲሁ እንዳለን ከእናታችን ቤት

ከርሞ እንገናኝ ላመት

ከመካከላችን ማንም ሰው ሳይሞት

ከርሞ እንገናኝ ላመት፡፡”

ከበዓሉ ውሎና ከድግሱ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚደረገው ወጣቶች ዱላቸውን አሽለምልመው፣ አለባበሳቸውን አሳምረው፣ ቁምጣ ሱሪ (ሶራ) ለብሰው የገና ጨዋታ በቡድን ሆነው ይጫወታሉ፡፡ ይህ ጨዋታም ወንዶች ከእንጨት የተሠራች ትንሽ ድቡልቡል ኳስ በቆልማማ ዱላ እየመሩ አንዱ ቡድን በአንዱ ቡድን ድንበር አልፎ ኳሷን በማስገባት የሚጫወቱት ጨዋታ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...