Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመድረክ ብሔራዊ ድርድር በአስቸኳይ እንዲጀመር ጠየቀ

መድረክ ብሔራዊ ድርድር በአስቸኳይ እንዲጀመር ጠየቀ

ቀን:

በአገሪቱ የተከሰቱት ዘርፈ ብዙ ችግሮች በሙሉ ዕልባት ሊያገኙ የሚችሉት ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በቀጥታ ወይም በተወካዮቻቸው አማካይነት ድርድርና ውይይት በማድረግ በሚፈጥሩት ብሔራዊ መግባባት ብቻ መሆኑን ተገንዝቦ ምንም ጊዜ ሳያባክን ራሱን ለድርድር እንዲያዘጋጅ፣ ብሔራዊ ድርድርና ውይይት በአስቸኳይ እንዲጀመር የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) መንግሥትን አሳሰበ፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ እየተከናወነ ያለው ለውጥ መሠረታዊ እንዲሆንና የአገሪቷንና የሕዝቦቿን ሁለንተናዊ ችግር በሚፈታ አኳኃን ይካሄድ ዘንድ፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ተቋቁሞ ችግር ፈቺ ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት እንዲካሄድና ብሔራዊ መግባባት እንዲመጣ በተደጋጋሚ ሐሳብ ማቅረቡን አስታውሷል፡፡

ነገር ግን፣ ‹‹በገዥው ፓርቲ ፈቃደኛ አለመሆንና በአንዳንድ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ግንዛቤ ባለመወሰዱ ምክንያት ሕዝቦች አድማሳቸውን በሚያሰፉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ምክንያት ፍዳቸውን እያዩ ይገኛል፤›› በማለት፣ ዳግም ለብሔራዊ ዕርቅና መግባባት ጥሪውን አቅርቧል፡፡

መድረክ ይህን ማሳሰቢያ አዘል ጥሪ ያቀረበው ዓርብ ታኅሳስ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሆን፣ ከብሔራዊ ዕርቅና መግባባት ባለፈም፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ስለተከሰቱ ግጭቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ እንዲሁም በቤተ እምነቶች ላይ እየደረሰ ስላለው ውድመት አስመልክቶም አቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም መሠረት መንግሥት የዜጎችን ሕይወት ያጠፉ፣ ዜጎችን ያፈናቀሉና ቤተ እምነቶች ላይ ጉዳት ያደረሱ ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን ለፍርድ እንዲያቀርብና ውጤቱንም ለሕዝቡ ይፋ እንዲያደርግ፣ እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን የገደሉ፣ ያስገደሉ፣ እንዲሁም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ የሥራ ኃላፊዎች፣ ግለሰቦችና ቡድኖች ለፍርድ እንዲቀርቡ መንግሥትን ጠይቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ሕዝቡን ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ ለሟች ቤተሰቦች ተገቢ ካሳ እንዲከፍልና ኃላፊነቱንም በይፋ እንዲወስድ መድረክ ጠይቋል፡፡

በማኅበራዊ የትስስር ገጾችና በሕግ አግባብ ያልተደራጁ ቡድኖችን ሥርዓት እንዲያሲዝ፣ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ላይ እያደረሱ ያሉትን አፍራሽ ተፅዕኖዎች በማስቆም ሕጋዊነትና ተጠያቂነት ባለው መንገድ ተደራጅተው ለአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መንግሥትን ጠይቋል፡፡ 

ሕዝቡን በሚከፋፍሉና በሚያጋጩ ባለሥልጣናቱም ሆነ ሌሎች ፖለቲከኞችና ቡድኖች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግና በሕዝቦች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በሰላማዊና ባህላዊ ውይይቶችና የዕርቅ ሥርዓቶች በየአካባቢያቸው የሚፈቱበት መንገድ እንዲፈጠር መድረክ መንግሥትን አጥብቆ ጠይቋል፡፡

በአገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮች በሙሉ እልባት የሚያገኙት ሁሉም ዜጎች በቀጥታ ወይም በተወካዮቻቸው በኩል ውይይትና ድርድር በማድረግ በሚፈጥሩት ብሔራዊ መግባባት ብቻ መሆኑን በመገንዘብ፣ መንግሥት ጊዜ ሳያባክን ራሱን ለድርድር አዘጋጅቶ ብሔራዊ ድርድርና ውይይት እንዲጀመር አሳስቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...