Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ የሚመራ የኢንቨስትመንት ችግሮችን የሚፈታ የቅንጅት መድረክ ተመሠረተ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በመሳብ ሒደት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችልና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ግርማ ብሩ (አምባሳደር) የሚመራ የቅንጅት መድረክ ተመሠረተ፡፡ የቅንጅት መድረኩ የተመሠረተው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ሐሙስ ታኅሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደ ስብሰባ ነው፡፡

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገዱ፣ ‹‹በአገራችን በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለውን አጠቃላይ አገራዊ ለውጥ ተከትሎ በርካታ የውጭ ባለሀብቶች ኢንቨስት ለማድረግ በስፋት እየመጡ ነው፤›› ብለዋል። ይሁን እንጂ ባለሀብቶችን በአግባቡ ተቀብሎ በማስተናገድና ወደ ሥራ በማስገባት በኩል ክፍተቶች መኖራቸውን አስረድተዋል።

በመሆኑም የሚታዩ ችግሮችን በአግባቡ በመፍታት የተሻለ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እንዲቻል ችግሮችን በቅርብ እየተከታተለ የሚፈታ መድረክ ማዘጋጀት በማስፈለጉ የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን አባላት፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ቦርድ አካላትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ያካተተ ውይይት ለማካሄድ መድረኩ መጠራቱን አቶ ገዱ አብራርተዋል።

በስብሰባው ላይ የተገኙት በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ግርማ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጓት ምክንያቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በርካታ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ መሆኑን ገልጸዋል። ‹‹የውጭ ባለሀብቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንደ አገር የመፈጸም አቅማችንን በማሳደግ መፍታት ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አቶ ግርማ አሳስበዋል።

በማያያዝም የውጭ ባለሀብቱ የሚያጋጥመውን ችግር በቅደመ ተከተል በማስቀመጥና እንደ ችግሩ ዓይነት፣ በቅርብ እየተከታተለ የሚፈታ ቋሚ መድረክ ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል። የውጭ ባለሀብቶችን ወደ ኢንቨስትመንት ከማስገባት አንፃር ከምልመላ ጀምሮ፣ በቅድመ ኢንቨስትመንት እንዲሁም ከኢንቨስትመንት በኋላ በርካታ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

ባለሀብቶቹ ወደ ኢንቨስትመንት ከገቡ በኋላ ከፀጥታና ከደኅንነት፣ ከመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ከታክስ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ ከመሬት አቅርቦት፣ ከውጭ ባለሙያዎች ፈቃድ አሰጣጥ፣ አላስፈላጊ ቢሮክራሲና ሌሎች ከሎጂስቲክስ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንደሚያጋጥማቸው ተገልጿል። ችግሩን በቋሚነት በቅርብ ለመከታተል እንዲቻል ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሴክተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ያካተተ የቅንጅት መድረክ ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑም መግባባት ላይ ተደርሷል።

በዚሁ መሠረት በአቶ ግርማ የሚመራ የቅንጅት መድረክ የተቋቋመ ሲሆን፣ የመድረኩ ቀጣይ ስብሰባም በጥር ወር 2012 ዓ.ም. መጨረሻ እንዲካሄድ ተወስኗል።

በስብሰባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ አቶ ግርማ ብሩ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፣ የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ኃይለ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም ሌሎች የመንግሥታዊ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች