ማንኛውም ዓይነት የዘር፣ የሃይማኖት፣ የፆታ፣ የቀለምና መሰል ጉዳዮች ቅስቀሳ በጥላቻ ላይ ሲመሠረት አግላይ፣ ጠላትነትን የሚያስፋፋና ግጭት ቀስቃሽ ስለሚሆን በሕግ መከልከል እንዳለበት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነት ያለውና ስምምነት የተደረሰበት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አሉታዊ ድርጊት በሕግ ሲገደብ ግን፣ መሠረታዊ የሆኑ መብቶችንና ነፃነቶችን እንዳይገደብ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ጤናማ ማኅበረሰብ መፍጠር የሚቻለው ጎጂና አሉታዊ ድርጊቶችን በጋራ ይሁንታ በማስወገድ ነው፡፡ የጋራ ዕይታና አቋም ለመያዝ ግን ውይይትና ድርድር ያስፈልጋል፡፡ መሰንበቻውን የጥላቻና የሐሰተኛ ንግግርን ለመከላከልና ለመቆጠጠር የተዘጋጀ የሕግ ረቂቅ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕዝባዊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ረቂቅ ሕጉን በተመለከተ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ ሰዎች ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ የብዙዎች ሥጋትም ረቂቅ ሕጉ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ይገድባል የሚለው እንደሆነ በውይይቱ ወቅት ተወስቷል፡፡ አንድ ንግግር የጥላቻና የሐሰተኛ ለመሆኑ ብያኔ የሚሰጠው ማን ነው? ይህንን ሕግስ ለማፅደቅ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለ? ከሚሉት በተጨማሪ በረቂቅ ሕጉ ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችና ለትርጉም አሻሚ የሆኑ አገላለጾች ጉዳይም ተነስቷል፡፡ የሁሉም ማጠንጠኛ ግን ረቂቅ ሕጉ በአንድ በኩል የጥላቻና የሐሰት ንግግሮችን እቆጣጠራለሁ ሲል፣ ሌሎች መብቶችንና ነፃነቶችን ላለመደፍጠጡ ምን ማስተማመኛ አለ የሚለው ነው፡፡ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ፍርድ ቤት ያሉ ተቋማት ደካማ መሆን፣ ለአተረጓጎም ክፍት ከሆነው ሕግ ጋር ሲደመር የዜጎች መብትና ነፃነት ላለመደፍጠጡ ምንም ዋስትና የለም፡፡ አቅመ ቢስ ተቋማት ማንንም አያስጥሉምና፡፡ ይህ ሥጋት ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ያሳስባል፡፡
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የሕግ ትርጉም ክፍተት እንዳለበት፣ አንድ ንግግር የጥላቻ ለመሆኑ እንዴት ብያኔ እንደሚሰጥበት፣ የጥላቻ ንግግር የሚረጋገጠው እንዴት እንደሚሆን፣ የጥላቻ ንግግር ምን ማለት እንደሆነ፣ ለአንዱ ወገን የመብት ጥያቄ የሆነ ለሌላው የጥላቻ ንግግር ሊሆን ስለመቻሉ፣ የሐሳብ ልዩነቶች ለክርክር ሲቀርቡ እንዴት እንደሚመዘኑ፣ በሕገ መንግሥቱ የሠፈረውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ካስቀመጣቸው ክልከላዎች ውጪ፣ ተጨማሪ ገደብ ማምጣት የሚፈጥረው ተቃርኖ፣ ሕጋዊ መሠረት የማጣት ጉዳይና ሌሎች ሐሳቦች ቀርበውበታል፡፡ በተጨማሪም አንድ ንግግር ጥሬ ሀቅ ሆኖ ከዜና ባለፈ ወደ ፖለቲካዊ ትችትና አስተያየት ካጋደለ ተብሎ በረቂቅ ሕጉ የቀረበውም ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ የንግግር ነፃነት አካል የሆነው የፖለቲካ ትችት ወይም አስተያየት ከሌለ እንዴት ሆኖ ነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው? የፖለቲካ ትችት በሌለበት የተለያዩ ሐሳቦች ለሕዝብ በአማራጭነት እንዴት መቅረብ ይችላሉ? ዜጎች እርስ በርሳቸው የማይነጋገሩ፣ የማይከራከሩና ሐሳባቸውን በነፃነት ማቅረብ የማይችሉ ከሆነ የተሻለ ሐሳብ እንዴት ማግኘት ይቻላል? በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር እንዴት ሊከናወን ነው? እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ምላሽ ይሻሉ፡፡
እንደሚታወቀው የማኅበራዊ ትስስር ገጾች በርካታ ሐሳቦች ያለ ገደብ የሚስተናገዱባቸው ዘመን ውስጥ ነው ያለነው፡፡ መደበኛው ሚዲያም እንዲሁ በርካታ ሐሳቦችን ያስተናግዳል፡፡ የጥላቻ ንግግሮች በአብዛኛው የሚሠራጩት ማንነታቸው በማይታወቅ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች መሆኑ እየታወቀ፣ ሕጎች ሲወጡ ግን መደበኛውን ሚዲያ ዒላማ አድርገው ስለሆነ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የሚደረገው ጥረት ይመክናል፡፡ ሰዎች ሕግ አክብረው በነፃነት የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋቸው እጅግ ተፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን በሠለጠኑ አገሮች መንግሥታት የሚዲያን አራተኛ መንግሥትነት አምነው ተቀብለው ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርጉ፣ በአንፃሩ የፕሬስ ነፃነትን የፈቀዱ እየመሰሉ ሥልታዊ በሆነ መንገድ አፈና ውስጥ የሚገቡ አሉ፡፡ በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ያለው የሚዲያ ሕግ በነፃነት ስም ያደረሰውን መከራ ብዙዎች ያውቁታል፡፡ በተለይ የፀረ ሽብር ሕጉ በአገሪቱ የሚዲያ ምኅዳር ላይ የፈጸመው ታሪክ ይቅር የማይለው በደል አይረሳም፡፡ በርካታ ጋዜጠኞች የፀረ ሽብር ሕጉ ሰለባ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡ በአሁኑ ጊዜ አፋኝ የሆነውን የሚዲያ ሕግ ለመለወጥ ከፍተኛ የሆነ ሥራ ተከናውኖ፣ አዲሱ ረቂቅ ሕግ ለፓርላማ እንዲቀርብ በዝግጅት ላይ ነው፡፡ የሚዲያ አፈናን ለማስቀረት የሚጠቅም አዲስ ሕግ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት፣ የጥላቻና የሐሰተኛ ንግግር ሕጉ ሌላ አፈና ይዞ እንዳይመጣ የሚመለከታቸው አካላት መረባረብ አለባቸው፡፡ ይህ ሕግ ነፃነትን የሚገድብ ከሆነ ልፋቱ ሁሉ ‹‹ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ›› ይሆናል፡፡ በሚዲያ አፈና የደረሰው ጉዳት ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ምክንያት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በሚዲያው ላይ አፈና ሲደረግ የነበረው ቅቡልነት የሌለው ሥልጣን ለመያዝና ለማጠናከር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ለዚህም ነው የዚህ ሕግ ዓላማ ምንድነው ተብሎ የሚጠየቀው፡፡
በጥላቻና በሐሰተኛ ንግግር ረቂቅ ሕጉ ላይ በተደረገው ውይይት የተነሱ ሐሳቦች፣ ለረቂቁ በግብዓትነት እንደሚጠቅሙ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ከገዳቢ ሕግ ይልቅ ለንግግር ነፃነት ከፍ ያለ ቦታ መስጠት ይገባል፡፡ ይህ ረቂቅ ሕግ ኢትዮጵያ ተቀብላ ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ሰነድ ድንጋጌዎች በተቃራኒ፣ የተለጠጡ መሠረታዊ የሚባሉ አንቀጾችን እንደያዘ ሲነገር ደንገጥ ማለት ተገቢ ነው፡፡ የንግግርና የሚዲያ ነፃነትን የሚጋፋ ሕግ ከማፅደቅ ይልቅ፣ ምክንያታዊ የሆነ የንግግር ነፃነት እንዲኖር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀደም በበርካታ ምክንያቶች የተበላሸውን የአገሪቱን ፖለቲካዊ ግንኙነት ለማደስ፣ የተለያዩ ሐሳቦች እንዲንሸራሸሩ የሚረዳውን የንግግር ነፃነት ማሳደግ ይመረጣል፡፡ የጥላቻ መርዝ የተነሰነሰበት የአገሪቱ ፖለቲካ ፈውስ የሚያገኘው፣ የንግግር መድረኮች ሲበዙና ሐሳቦች በስፋት ሲስተናገዱ ነው፡፡ ንግግርን በንግግር የመመከት ባህል ማዳበር ሲገባ፣ የንግግር ነፃነት ላይ አፈና ሊያመጣ የሚችል ሕግ ለማውጣት መጣደፍ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊያደርግ ይችላል፡፡ ሕግ በማስከበር ስም ሕገወጥነትን የሚያስፋፋ፣ ለሐሳብ የበላይነት ሳይሆን ፀጥ እረጭ የሚያደርግና ወደ አምባገነንነት ሊመልስ የሚችል ችግር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ በጣም የተለጠጠ፣ ለትርጉም ክፍት የሆነ፣ ለችግሮች መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ የሚያባብስ፣ እንዲሁም የንግግርና የሚዲያ ነፃነትን ሊገድብ የሚችል ነው ተብሎ ሥጋት ሲገለጽ ግራና ቀኙን ማማተር ተገቢ ነው፡፡ አንድን ንግግር በጥላቻ በይኖ ለሐሳብ አፈና የሚጠቅም ሥጋት ከመደቀን፣ አላስፈላጊ ለሆኑ እሰጥ አገባዎችና ትንቅንቆች ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ ካሁን ቀደም በአገሪቱ ውስጥ ለቅራኔ፣ ለእርስ በርስ ግጭትና ውድመት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ምንድናቸው ሲባል፣ የመብቶችና የነፃነቶች መታፈን እንደነበረ ማንም አይስተውም፡፡ የተበላሸውን የፖለቲካ ግንኙነት ለማስተካከል ሕግ ከመደርደር ይልቅ፣ ለንግግር ነፃነት ትኩረት መስጠት መቅደም አለበት፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ አላስፈላጊ ችግሮች ጉዳዮች ሲያጋጥሙም፣ የመነጋገርና የመወያየት ባህል እንዲዳብር የሚረዱ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ይረዳል፡፡ የዜጎችን ሰብዓዊ ክብርና ደኅንነት ለማስጠበቅ ሕግ አስፈላጊ ቢሆንም፣ የሚወጣው ሕግ መብትና ነፃነትን እንዳይደፈጥጥ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የጥላቻና የሐሰተኛ ንግግር በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በአካል ጉዳት፣ በቀለምና በሌሎች መሰል ጉዳዮች ላይ መገለል ለመፍጠርና ጥቃት ለመፈጸም አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ይህንን ጎጂ ተፅዕኖ አላስፈላጊ በሆነ መንገድ ለመግታት ግን የንግግር ነፃነት የመስዋዕት ጠቦት መሆን የለበትም፡፡ በተለጠጠ የሕግ ትርጉምና ክፍተት ምክንያት መብትና ነፃነት ድባቅ እንዳይመታ ጥንቃቄ ማድረግ የግድ ይሆናል!