Wednesday, October 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበወሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት በማስነሳት የተጠረጠሩ 14 ግለሰቦች ተያዙ

  በወሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት በማስነሳት የተጠረጠሩ 14 ግለሰቦች ተያዙ

  ቀን:

  በወሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት በማስነሳት የተጠረሩ 14 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ፡፡ እስከ ሐሙስ ምሽት ታኅሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከል አንድ መምህር መኖሩን ለሪፖርተር የገለጹት፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አባተ ጌታሁን (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት ተቀስቅሶ በነበረው ግጭት ሕይወቱን ላጣው ተማሪ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ የተጠረጠረው ተማሪ፣ ሐሙስ ሌሊት በቁጥጥር ሥር መዋሉንም አክለዋል፡፡

  በደሴ ካምፓስ እንደሚማር የተገለጸው ይህ ተጠርጣሪ አብሮት የሚሠራ ሌላ ኃይል መኖር አለመኖሩም እየተጣራ ነው ብለዋል፡፡

  ተማሪውን ለሞት የዳረገው አደጋ የደረሰው ሐሙስ ታኅሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ጠዋት አንድ ሰዓት ተኩል ላይ ሲሆን፣ የተማሪዎች መመገቢያ ካፊቴሪያ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት ሦስት ሰዎች መቁሰላቸውን፣ ከሦስቱ አንደኛው በደረሰበት ጉዳት ረፋድ አምስት ሰዓት አካባቢ ሕይወቱ ማለፉን፣ አስከሬኑም ለምርመራ አዲስ አበባ ቅዱስ ጳውሎስ ሜዲካል የሕክምና ኮሌጅ መላኩን አባተ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ የሕክምና ዕርዳታ ተደርጎላቸው ተመልሰዋል የተባሉት ሁለቱ ተጎጂዎችም የጥበቃና የኮንስትራክሽን ሠራተኞች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

  ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻና ደሴ በተባሉ ሁለት ካምፓሶቹ ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተምራል፡፡ በአሁኑ ወቅት በደሴ ካምፓስ የመማር ማስተማሩን ሒደት የሚያደናቅፉ ክስተቶች እየተስተዋሉ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ችግሮቹ ግን ካምፓሱን የሚያዘጉ አይደሉም ብለዋል፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ተቋማት ግን መደበኛውን የትምህርት ፕሮግራም ማስቀጠል እንደከበዳቸው እየገለጹ ነው፡፡

  ከ2008 ዓ.ም. ወዲህ እየታየ ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ዩኒቨርሲቲዎች እየታመሱ መሆኑን የተናገሩት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አባተ (ዶ/ር)፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ የደሴ ካምፓሱ በተረጋጋ ሁኔታ ማስተማር አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

  ይህ በዚህ እንዳል ለሦስተኛ ጊዜ ትምህርት ያቋረጡ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መቀጠል የማይችሉ ከሆነ፣ ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚዘጋ ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ፡፡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የተለያዩ የማግባባት ሥራዎች ቢከናወኑም፣ አለመሳካታቸውንና በመሆኑም በፍጥነት ወደ ትምህርት ገበታቸው ካልተመለሱ፣ እንደ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ እንደሚዘጋ ዩኒቨርሲቲው ይፋ ያደረገው ከሰሞኑ ነው፡፡

  ጅማ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ የማይፈልጉ በግቢው የሚገኙ ተማሪዎች፣ አስፈላጊውን ፎርማሊቲ አሟልተው ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ሒደት ከሰኞ ታኅሳስ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የቀጠለ ቢሆንም፣ ተማሪዎች በተሟላ ሁኔታ ወደ ትምህርት ገበታቸው አለመመለሳቸውን በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡

  በመሆኑም ወደ ትምህርታቸው መመለስ ለማይፈልጉ ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተማሪዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚያቋርጥና ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ አስተላልፏል፡፡

  ዩኒቨርሲቲው የመማር ፍላጎት የሌላቸው ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ሲያስጠነቅቅ፣ ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ ሁለተኛው ነው፡፡ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ከሚከታተሉ ተማሪዎች ውጪ ሌሎችን እንደማያስተናግድና ለቀው እንዲወጡ ያስታወቀው ከሳምንት በፊት ነበር፡፡

  በዩኒቨርሲቲዎች የሚታዩ ቀውሶች በተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ሁከት ለመፍጠር በሚሠሩ ኃይሎች መፈጠራቸውን ያስታወቀው፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አባተ (ዶ/ር) እንዲሁ፣ ተማሪዎች ከሌሎች ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው እንደሚሠሩ ጥርጣሬ እንዳለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  በአሁኑ ጊዜ በሁለት ሰዎች መካከል የሚፈጠር የግል ግጭት ሳይቀር በዘርና በሃይማኖት መነጽር እየታየ ወደ ቡድን ፀብ እየተቀየረ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ በተማሪዎች መካከል ሰላም እንዲወርድ በተለያዩ ጊዜያት የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት ለዕርቅ መቀመጣቸውን፣ ይሁንና ፍሬያማ ሳይሆን መቅረቱን ገልጸዋል፡፡

  ‹‹በዘመዶቻችን ላይ ግፍ ደርሷል፤›› የሚሉ ተማሪዎች ከጓደኞቻቸው እየተጋጩ መሆኑን፣ በአገሪቱ የሚታዩ የተያለዩ የፖለቲካ ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት ምሬታቸውን እንደሚገልጹ፣ ‹‹የእኛ መማር ምንድነው?›› የሚሉ ተማሪዎች መበራከታቸውንም አስረድተዋል፡፡  

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img