የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የሚያቅዷቸው መካከለኛና ከፍተኛ ፕሮጀክቶች አዋጭነት በገለልተኛ አካል ሳይመረመር፣ በጀት እንዳይፈቀድላቸውና ወደ ትግበራ እንዳገይቡ አስገዳጅ ክልከላ የሚጥል ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተላከ፡፡
ምክር ቤቱ ከቀናት በኋላ የመጀመሪያ ውይይት ያደርግበታል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ረቂቅ አዋጅ፣ የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በብድርም ሆነ ከመንግሥት ካዝና በሚገኝ በጀት ሊያከናውኗቸው የሚፈልጓቸው ማናቸውም ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት ሳይካሄድላቸው ወደ ትግበራ እንዳይገቡ ይከለክላል፡፡ ነገር ግን መካከለኛና ከፍተኛ ፕሮጀክቶች ደግሞ የፕሮጀክት ሐሳብ አፍላቂ የሆነው ፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ ተቋም ከሚያደርገው የአዋጭነት ጥናት በተጨማሪ፣ ኃላፊነት በሚሰጠው ገለልተኛ አካል አዋጭነታቸው እንዲጠና የሚያደርግ አስገዳጅ ድንጋጌን ይዟል፡፡
የፕሮጀክት ሐሳብ አፍላቂና ፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ከሚያደርጉት የአዋጭነት ጥናት በተጨማሪ በገለልተኛ ወገን የአዋጭነት ጥናት ግምገማ ማድረግን አስፈላጊ ያደረገው፣ የፕሮጀክት አፍላቂ ተቋማት የፕሮጀክቱን ወጪ የመቀነስና የፕሮጀክቱን ጠቀሜታ የማጋነን አዝማሚያ ስለሚታይባቸው ነው፡፡ እንዲሁም ፕሮጀክቱን አስመልክቶ የሚቀርቡትን መረጃዎች ተዓማኒነት በገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ እንደሆነ፣ የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡
የፌዴራል መንግሥት የፕሮጀክት አስተዳደርና አመራር ሥርዓት ዘርግቶ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ቢደረጉ ኖሮ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ በዚህ ምክንያት የባከነውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ማዳን ይቻል እንደነበር መንግሥት ባካሄደው የኢንቨስትመንት ግምገማ ጥናት ማረጋገጡን የረቂቁ አባሪ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡ ባለፉት የዕቅድ ዓመታት በመንግሥት በጀትና በመንግሥት ዋስትና በተገኘ የውጭና በአገር ውስጥ ብድር የተከናወኑና በመከናወን ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው መርሐ ግብር፣ የጥራት ደረጃና በጀት መሠረት አለመከናወናቸውን ማብራሪያው ይገልጻል፡፡
በዚህም የተነሳ በአገሪቱ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት እንዲከሰት ምክንያት መሆናቸውና ይህም ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ማስከተሉ፣ በጥናት መረጋገጡን ማብራሪያው ያመለክታል፡፡ በረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ መሠረት ሁሉም ፕሮጀክቶች ወደ ትግበራ ከመግባቸው አስቀድሞ የሚያልፉበትን ዑደት ረቂቅ አዋጁ አስቀመጧል፡፡
በዚህም መሠረት ለእያንዳንዱ ፕሮጀክት ሐሳብ ማመንጨትና የመጀመሪያ ደረጃ መረጣ ወይም ምልመላ በፕሮጀክቱ አመንጪ እንደሚከናወን፣ ይህንን ተከትሎም የቅደመ አዋጭነትና አዋጭነት ጥናት በአመንጪው ተቋም መካሄድ እንደሚኖርበት፣ በኋላም በፕሮጀክቱ ባለቤት ተቆጣጣሪና በገለልተኛ ወገን የአዋጭነት ግምገማ እንደሚካሄድ፣ በመጨረሻም የፕሮጀክት ቅደም ተከተል ማስያዝና በጀት መፍቀድ መሆናቸውን ረቂቁ ያመለክታል፡፡
ሆኖም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና በልማት አጋሮች ፋይናንስ የተጠኑ ፕሮጀክቶች ዝርዝር መሥፈርቶቹን ማለፍ ሳይጠበቅባቸው፣ በቀጥታ ወደ ገለልተኛ የአዋጭነት ጥናት ግምገማ ሊያልፉ እንደሚችሉ ይፈቅዳል፡፡ በመንግሥትና የግል አጋርነት እንዲከናወኑ የሚፈለጉ ፕሮጀክቶችም የተዘረዘሩትን ደረጃዎች ማለፍና በገለልተኛ ወገን የአዋጭነት ግምገማ እንደሚደረግባቸው ያመለክታል፡፡ ገለልተኛ የአዋጭነት ግምገማውን የማድረግ ኃላፊነት የሚሰጠው ለፕላንና ልማት ኮሚሽን እንደሆነም በረቂቁ ተመልክቷል፡፡ በመከላከያ ሚኒስቴር፣ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሚፈጸሙ ፕሮጀክቶችና የአደጋ መከላከልን የተመለከቱ ፕሮጀክቶች ላይ ረቂቅ አዋጁ ተፈጻሚ እንደማይሆን ተገልጿል፡፡