Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ኮንትራክተሮች ባለሥልጣናትን ሌባና ሀብታም እያደረጋችሁ በከፍተኛ ደረጃ የማይታዘዙ በዝተዋል›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተዋናይ ኮንትራክተሮች ባለሥልጣናትን ሌባና ሀብታም እያደረጉ፣ በከፍተኛ ደረጃ የማይታዘዙ ሹማምንትና ባለሥልጣናት መብዛታቸውን ገለጹ፡፡ መሀል ላይ ያለውን ደላላና ሌባ አጥፍቶ መንግሥት ለሕዝብ ብቻ አገልጋይ እንዲሆን እንዲያግዙ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተዋናዮችን ጠየቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ ለሁለተኛ ጊዜ ባዘጋጀው የአገር አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ንቅናቄ መድረክ ላይ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢኮኖሚክ ኮሚንሽን የስብሰባ አዳራሽ ሐሙስ ታኅሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፣ የሌብነት ዋና ቦታ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ነው፡፡ ‹‹ሌብነት እያስቸገረ ነው፡፡ ባለሥልጣናትን ሌባና ሀብታም እያደረጋችሁ በከፍተኛ ደረጃ የማይታዘዙ ሹማምንቶች በዝተዋል፡፡ የባንክ ብድር የለም ትላላችሁ፡፡ ዕድሜ ለእናንተ ሰዎቹን አባለጋችሁ፡፡ ብር ማጭበርበርና የውሸት ሪፖርት ማቅረብ ለምደው ለመንግሥት ዕዳ ሆኑ፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ባለሥልጣናት ሥራ ስለማይወዱ ስምንት ሰዓት እንኳን መሥራት እንደማይወዱ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ዕድሜ ለእናንተ የውጭ ምንዛሪ ችግር ስለሌለባቸው በረባ ባልረባው ባንኮክ ይሄዳሉ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እባካችሁ ሌብነት እንዲቆም ወስናችሁ ሥሩ፡፡ ሌብነት ካልቆመ ለጊዜው ሥራችሁን ያቀለላችሁ ይመስላችኋል እንጂ፣ መልሶ የሚበላሸው የራሳችሁን ሥራ ነው፤›› ብለው፣ ሥራቸውን በገንዘብ ኃይል ለማሠራት የሚያደርጉት ጥረት ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚብስ አስረድተዋል፡፡

አንድ ጊዜ የለመደ ሰው በአንድ ጊዜ ስጦታ እንደማያቆምና በዚህ ደግሞ ከሚሠራው ይልቅ የሚሰርቀው በሚበዛበት አገር፣ ወደ ብልፅግና መሄድ እንደማይቻልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው አስረድተዋል፡፡ መንግሥትና አገሩን ዋሽቶ የሰረቀ ለእነሱ ዕድገት ሊሠራ እንደማይችልም አክለዋል፡፡

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ምርመራ በማድረግ በሚሠሩት ሥራ ላይ እንዲወስኑ ጠቁመው፣ ‹‹ሌቦችን እያለማመድኩ አገሬን አልጎዳም ብላችሁ ሌብነትን ከተዋችሁ፣ እኛም መምራትና መርዳት እንችላለን፡፡ በጋራም እናቅዳለን፡፡ ምክንያቱም የምናቅደው በሀብታሞች ላይ ነው፡፡ እኛን ከመስማት እናንተን መስማት ይሻላል፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት የሚከፍለው አምስት ሺሕ ብርና አሥር ሺሕ ብር ቢሆንም፣ ተቋራጩ ወይም የሴክተሩ ተዋናይ መቶ ሺሕ ብር እንደሚከፍል የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለሥልጣኑ ግን ለመንግሥት እንዳይሠራ በባለሀብቱ መያዙን፣ ለባለሀብቱ እንዳይሠራ በመንግሥት በመያዙ ሴክተሩ እንዳያድግ ከባድ ችግር ውስጥ እንደከተተው ጠቁመዋል፡፡ መሀል ላይ ያለውን ደላላና ሌባ አጥፍቶ መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ እንዲሆን ተጋግዞ መሥራት ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል፡፡ ሌቦች እስካሉ ድረስ ምንም ቢሠራ ውጤት ለማምጣት እንደማይቻልና የሌባ ስብሰብ ያለበት አገር በለፀገ ማለትም እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ ብልፅግና ቁስ ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብም ጭምር ስለሆነ፣ ሌብነትን ለመቀነስና ለመተባበር አንዱ ቁልፍ ነገር መተማመን በመሆኑ፣ ‹‹እንድናምናችሁ ካደረጋችሁን እንተጋገዛለን፤›› ብለዋል፡፡

የግለሰብ ኩባንያ የሚቀጥረው ከሠፈሩ፣ የሚገዛውም ከሚያውቀው መሆኑንና ይኼ አሠራር ሴክተሩን የትም ሊያደርሰው እንደማይችል የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ያልተደመረ አያድግም፡፡ ተደምራችሁ ትልቅ ኩባንያ ፍጠሩ፡፡ እኛም እናግዛለን፡፡ ኩባንያ ሲሆን ኢትዮጵያዊና ዘር አልባ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ ኩባንያው ኢትዮጵያ ከሆነ የትም ቦታ ማለትም ከአገር አልፎ በጂቡቲ፣ በኬንያ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኡጋንዳ፣ ወዘተ ተንቀሳቅሶ መሥራት እንደሚችልና ‹‹የእንትና ኩባንያ›› የሚለውን እንደሚያስቀርም ጠቁመዋል፡፡

በዘርፉ የሚመደበው ሀብት በጣም ብዙ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተያዘው በጀት ዓመት እንኳን 48 ቢሊዮን ብር መመደቡን አስታውሰዋል፡፡ ሀብቱ የዘርፉን ተዋናዮች አጠናክሮና አሳድጎ ወደ ሌሎች አገሮች የማይወስድ ከሆነ፣ ‹‹የእናንተ ዕድገት ብቻ መጨረሻ ላይ ችግር ይፈጥርብናል፤›› ብለዋል፡፡ ዕድገታቸው የማያቋርጥ እንዲሆን ሰብሰብ ብለው በመደመር መሥራት እንዳለባቸው አክለዋል፡፡ ይህንን ካደረጉ መንግሥትም በተገቢው መንገድ እነሱን ለማገዝ እንደሚሠራም ቃል ገብተዋል፡፡

ከውጭ ተቋራጮች ጋር በምክክር ደረጃ የተጀመረ ነገር እንዳለ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ መቶ በመቶ በኢትዮጵያውያን የሚሠሩና በግልጽ ጨረታ በውጭ ተቋራጮች የሚሠሩ ጉዳታቸው እየተጠና መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በጀቱ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት በሚሆንበት ጊዜ፣ የውጭዎቹ ከኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር በጋራ (Joint Venture) መሥራት እንደሚኖርባቸው እንደ ቅድመ ሁኔታ እንደሚወሰድ አስረድተዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በአጠቃላይ በአገር ዕድገትና ኢኮኖሚ ጉዞ ውስጥ ከፍተኛ ጫና እያመጣ መሆኑን ተናግረው፣ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ከሚያበድረው መቶ ብር ውስጥ ሰባት ብር ብቻ ጥቅም ላይ እንደሚውልና የተደራሽነት መጠን (Disbursement Ratio) ዝቅተኛ መሆኑን እየገለጹ እንደሚገኙ በምሳሌ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ለሦስት ዓመታት የያዛችሁትን የመንገድ ግንባታ ለስድስት ዓመታት ስለምታዘገዩና የተፈቀደውን ብድር በአግባቡ ሥራ ላይ መዋል ስላልተቻለ፣ ተጨማሪ ብድር ማግኘት አልተቻለም፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የተደራሽነት መጠን ከ30 እስከ 40 በመቶ ቢሆን እስከ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ለመልቀቅ እንደሚቻል መገለጹንም አክለዋል፡፡ ከዓለም ባንክ ብድር ሲገኝ አብዛኛው ለመንገድ፣ ለኢንዱስትሪ ፓርክና ከኮንስትራክሽን ጋር ለሚያያዝ ሥራ እንደሚውል ተናግረው፣ ‹‹በእርግጥ በግንባታ ላይ ያላችሁ ግሽበት (ኢንፍሌሽን) እንደሚያስቸግራችሁ እናውቃለን፡፡ ከውጭ የሚመጡ ግብዓቶችን በሚተኩ ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥታችሁ ከሠራችሁ ለእናንተም የተለየ ድጋፍ ይደረግላችኋል፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በመድረኩ ተገኝተውና መልዕክት አስተላልፈው ከሄዱ በኋላ፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያስጠናቸው የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ ሚኒስቴሩ ያዘጋጀውን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሴክተር የአሥር ዓመታት (ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም.) መሪ ዕቅድ ረቂቅ ቀርቧል፡፡

የአሥር ዓመታት ዕቅዱ የተዘጋጀው ኢትዮጵያን በ2022 ‹‹አፍሪካዊ የብልፅግና ተምሳሌት›› ለማድረግ የተያዘውን አገራዊ ራዕይ ለማሳካትና የዘርፉን ተልዕኮ ለማስፈጸም መሆኑን በመድረኩ ተነግሯል፡፡

የከተማ ልማት በርካታ ዘርፎች ያሉት እንቅስቃሴ ማለትም በኢንዱስትሪ፣ በገበያ፣ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በመሠረተ ልማት አገልግሎቶችን እንደሚያከናውን ረቂቁ ይገልጻል፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከግብርና ቀጥሎ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበትና የአገሪቱን የኢንዱስትሪ ሁለንተናዊ ዕድገት የሚወስን ስትራቴጂካዊ ዘርፍ መሆኑንም ያብራራል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ አሥር ዓመታት ሕዝቡን በማኅበራዊና በኢኮኖሚ ልማት ሙሉ ተሳታፊና ተጠቃሚ በሚያደርጉ ዋና ዋና ሥራዎች ላይ በማተኮር ሰፊ ርብርብ እንደሚደረግም ያብራራል፡፡

የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት፣ አካታችና ዘላቂነት ያለው የከተማ ፕላንና ልማት፣ አዋጭነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው የመሬት አቅርቦትና ማኔጅመንት፣ ኅብረተሰቡንና የግል ዘርፉን ያሳተፈ የቤት ልማትና አቅርቦት በጥራት፣ በተመጣጣኝ ወጪ፣ በወቅቱና በተወዳዳሪነት የሚሠራ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ፣ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት አሠራርና የማስፈጸም አቅም በመገንባት የአስተዳደር መርሆዎችን ለማሳካት እንደሚሠራ በረቂቁ በዝርዝር ቀርቧል፡፡

 በቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ተዋናዮች የግንዛቤ ችግር እንዳለባቸው፣ ዘርፉም ከግብዓት አቅርቦት እስከ የውጭ ምንዛሪ ድረስ ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንዳሉበት ተገልጿል፡፡ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የዘርፉ ተዋናዮችና ባለድርሻ አካላት ለሁለት ቀናት በቆየው የንቅናቄ መድረክ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒትሯን ወ/ሮ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶችም በውይይቱ ተሳትፈዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች