Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበስፖርቱ የተደበላለቀው ሕግ ደንብና መመርያ

በስፖርቱ የተደበላለቀው ሕግ ደንብና መመርያ

ቀን:

የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶላቸው በኅብረተሰቡ የሚዘወተሩ ስፖርቶች የመኖራቸውን ያህል ተቋማቱ የሚመሩበት ሕግ፣ ደንብና መመርያ ሊቀመጥላቸው እንደሚገባ ይታመናል፡፡ የሦስቱ ማዕቀፎች ተሟልቶ አለመቀመጥ በኢትዮጵያ ውጤታማ ተብሎ ለሚወደሰው አትሌቲክስና ለሌሎችም ስፖርቶች ውድቀት ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድና ችግሩ በእጅጉ ከሚያሳስባቸው ወገኖች መካከል ነዋሪነታቸውን በጀርመን ያደረጉት ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር) አንዱ ናቸው፡፡

ለጁዶና ጁጂትሱ ስፖርት ከፍተኛ ፍቅር እንዳላቸው የሚናገሩት ዶ/ር ፀጋዬ፣ በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ የጁጂትሱ ፌዴሬሽን የሥነ ምግባር ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ስፖርቱን ጨምሮ ሁለንተናዊ ለውጥና ዕድገት ይመጣ ዘንድ በዕውቀታቸው በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ለመሥራትና ለማገዝ ዝግጁ ስለመሆናቸው ተናግረው፣ በኢትዮጵያ በቆዩባቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ ከጀርመን ተሞክሮ በመነሳት በተለይ ስፖርቱን በሚመለከት የተቀመጡ ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎች ላይ ክፍተቶች መመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡

የዕውቀት ሽግግር አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው የሚናገሩት ዶ/ር ፀጋዬ፣ ስፖርቱን በሚመለከት በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው አንቀጽ ውስጥ ጥቅል ካልሆነ በዝርዝር የተቀመጠ ነገር የለም ይላሉ፡፡ መንግሥት ለስፖርት ተቋማት በሚበጅተው በጀት ልክ የሚኖረውን ድርሻና ሚና ሕጉ በቅጡ እንደማያብራራ በማሳያነት ያቀርባሉ፡፡ ሕግ አንድ ተቋም (ዘርፍ) የሚገዛበት አስገዳጅ ጥቅል መመርያ ሲሆን፣ ደንብ አዋጁ ያስቀመጣቸውን ነገሮች በዝርዝር የሚያስረዳ እንደሆነ፣ መመርያ ደግሞ በደንቡ ተዘርዝረው የተቀመጡትን የአዋጅ ድንጋጌዎች ማስፈጸሚያ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፣ በዚህ ደረጃ ስፖርቱን በሚመለከት የወጡት ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎች ላይ ግልጽ ክፍተት መኖሩን ይናገራሉ፡፡

በሚኖሩበት ጀርመን መንግሥቱ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ከሚያፈስባቸው ዘርፎች ስፖርት አንዱ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ፀጋዬ፣ አሁን ባለው ሁለቱን አገሮች ማወዳደር ባይቻልም ኢትዮጵያ በሁሉም ስፖርቶች የመንግሥት ሚና፣ የተቋማትና የማኅበራት፣ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ዘርፉን ማስተዳደርም ሆነ መምራት የሚችሉበት ሥርዓት መፍጠር ከተቻለ ስፖርቱን ወደሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ ብዙም ከባድ እንደማይሆን ያምናሉ፡፡

በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ኃላፊዎች ባመቻቹት መድረክ በአገሪቱ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸውን በማስቀመጥ ሁለንተናዊ ለውጥና ዕድገት ማምጣት በሚቻልባቸው ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና በሰጡባቸው መድረኮች ቀደም ሲል የዘረዘሯቸው ችግሮች ከተሳታፊዎቹ በግልጽ ሲቀርቡ እንደነበር ዶ/ር ፀጋዬ አስታውሰዋል፡፡

ጀርመኖች ለስፖርት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጡ የሚናገሩት ዶ/ር ፀጋዬ፣ በአገሪቱ ወደ 98 የሚጠጉ ማኅበራት ሲኖሩ፣ ከዚህ ውስጥ እግር ኳስ ከታች ጀምሮ እስከ 27,000 የሚጠጉ አደረጃጀቶች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ስፖርት በጀርመን ኢኮኖሚ ውስጥ 2.2 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ አወቃቀሩም ከታች ወደ ላይ የጀርመን ኦሊምፒክ ስፖርት ፌዴሬሽን የሚል ስያሜ የያዘ ስለመሆኑ ጭምር ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ስፖርት በዚህ መልክ እንኳ ባይሆን ያልተደበላለቀ ግልጽ የተጠሪነት ድርሻና ወሰን ሊበጅለት እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

በጀርመን የስፖርቱ የበላይ ጠባቂዎች ከአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ስፖርቱን የሚደጉሙ አካላት ሲሆኑ፣ እነዚህ አካላት ደግሞ ማኅበራቱን የበጀት አጠቃቀም የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት የመቆጣጠር ሙሉ ኃላፊነት የሚኖራቸው ናቸው፡፡ በዚህ አግባብ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ስንመለከት ማኅበራት መንግሥትን የሚፈልጉት በጀት እንዲሰጥ ሆኖ ቁጥጥርና ክትትልን በሚመለከት ግን ‹‹ጣልቃ ገብነት›› በሚል መንግሥት ድርሻ እንዳይኖረው የሚያደርግ አሠራር እንዳለ መታዘባቸውን፣ መንግሥት በሰጠው ፋይናንስ ቁጥጥር ላድርግ ሲል እንደ ጣልቃ ገብነት መታየቱ የሚያስገርም ስለመሆኑ ጭምር ይናገራሉ፡፡

ይህ ማለት ግን ጀርመን ውስጥ መንግሥት የማይቆጣጠራቸው የስፖርት ተቋማት የሉም ማለት እንዳልሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ፀጋዬ፣ ‹‹በራሳቸው ገቢ የሚተዳደሩ ተቋማት ከሆኑ ብቻ ነው፤›› ብለው፣ የፋይናንስ አጠቃቀም ግልጽነትን ለማስፈን ሲባል መንግሥት ጣልቃ የሚገባበት የአሠራር ሥርዓት እንደሚኖር ሳይገልጹ ግን አላለፉም፡፡

በጀርመን ስፖርት ጤናማና አምራች ትውልድ ለማፍራት ከሚሰጠው ጥቅም በተጨማሪ በዕድሜ የገፉ ዜጎች ጤናቸውን ለመጠበቅ አዘውትረው የሚጠቀሙበት ዘርፍ መሆኑ ለአገሪቱ ስፖርት ዕድገት ከፍ ያለ ድርሻ ስለመወጣቱም ተናግረዋል፡፡ በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ለማስ ስፖርት እየሰጠ ያለው ትኩረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

ሌላው በኢትዮጵያ ሊተኮርበት የሚገባ፣ ነገር ግን ትኩረት ያላገኘ የትምህርት ቤቶች ስፖርት መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ፀጋዬ፣ ‹‹ትምህርት ቤቶች የሁሉ ነገር መሠረት ናቸው፡፡ በጀርመን ትምህርትና ስፖርት ተነጣጥለው የሚታዩ አይደሉም፣ ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው፡፡ ለጀርመን ስፖርት ዕድገት መነሻ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ትምህርት ቤት ላይ መሠረት ያልጣለ ስፖርት ዋጋ የለውም፡፡ በግሌ አሁን ላይ ለኢትዮጵያ ስፖርት ውድቀት አንዱና ዋናው መንስዔ በትምህርት ቤቶችና በሠራዊቱ ቤት የነበረው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እየተዳከመ መምጣቱ ነው፣ የታዘብኩት እውነታም ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ስፖርት ትኩረት ይፈልጋል፣ ይህ ሲባል ስለስፖርት የሚናገረው ሰውም መለየትና መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ስፖርት እንደ ማንኛውም ዘርፍ ዕውቀትና ክህሎት ይጠይቃል፡፡ በዚህ ደረጃ ካልተቃኘ ዕድገት ማምጣትም ስለማይቻል ማለት ነው፡፡ ዘርፉ በአሁኑ ወቅት ትልቅ ኢንዱስትሪ እየሆነ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥታት ለፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተግዳሮቶቻቸው መፍቻ ቁልፍ አድርገው መመልከት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፤›› ብለው ይህ በኢትዮጵያም ሊለመድ የሚገባ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተዘጋጀ ባለው አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መካተት ከሚገባቸው ጉዳዮች አንዱና ዋናው ስፖርት መሆን እንደሚገባው ሐሳብ ማቅረባቸውን ያከሉት ዶ/ር ፀጋዬ፣ መንግሥት ይህን በማድረጉ ሊያገኝ የሚችለው ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ አንዱና ዋናው ብቃት ያላቸው ሙያተኞችን ለማፍራትና የስፖርት ቱሪዝም እንዲስፋፋ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋልም ብለው ያምናሉ፡፡

ሌላው ቀደም ሲል ተደበላልቋል ብለን ላነሳነው የስፖርት ሕግና የተጠሪነት ወሰን መፍትሔ ይሆናል የሚሉት ባለሙያው፣ ይህ ማለት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 41 ቁጥር 9 ላይ የተቀመጠው ጥቅል ደንብ ማለትም የስፖርት አፈጻጸም ሕግና የስፖርት ድጎማ ሕግ ዘርዘር ብሎ እንዲቀመጥ ያግዛል፣ የስፖርት መመርያውም በተመሳሳይ፡፡ እዚህ ላይ መመርያው በተለይ ማኅበራትን ለማቋቋም የአምስት ክልልና የአምስት ክለቦች ድጋፍ የሚል ነገር እንዳለው ለመታዘብ መቻላቸውን ያከሉት ሙያተኛው፣ ይህ በየትም አገር የሌለ ነገር ስለመሆኑ ጭምር ተናግረዋል፡፡

የስፖርት ሕግ፣ ደንብና መመርያ ተለይቶ በግልጽ ቢቀመጥ በስፖርት ማዘውተሪያዎች የሚስተዋሉ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደሎችን በቀላሉ መፍታት እንደሚቻል ያከሉት ዶ/ር ፀጋዬ፣ አሁን በኢትዮጵያ ባለው ጉዳዩ የሚፈታው በዓለም አቀፉ ማኅበር መመርያ ወይም በፍትሐ ብሔር ወይስ በወንጀል የሚለውን በማወቅ ችግሩን ለመፍታት እንደማይቻል ያስረዳሉ፡፡ በስፖርት መልካም አስተዳደርን ለማስፈንም ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ያምናሉ፡፡

በውጪ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በሚመለከት የስፖርት ፌዴሬሽኖች የሚጠቀሙበት ሕግ፣ በሕገ መንግሥቱ  የተቀመጠውን  የሚጥስ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት ዜግነቱ ሌላ ሆኖ በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው በአገር አቀፍ ምርጫ፣ በወታደራዊ ተቋማት በቋሚነት ካልሆነ በአገሩ መሥራትና ማገልገል እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ በፌዴሬሽኖች ያለው ሕግ ደግሞ ለሥራ አስፈጻሚነት የሚወዳደር ማንኛውም ሰው ኢትዮጵያዊ የመሆን ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ የሚገርመው ይህ የሆነው በሕገ መንግሥቱ ‹‹ሕግ›› ሥር ባለው መመርያ ላይ በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባው ይናገራሉ፡፡ ሌላው ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ከአዲስ አበባ ውጪ መዋቅራቸውን ወደ ክልሎች ማውረድ መቻል እንደሚጠበቅባቸው ጭምር ይመክራሉ፡፡

ትውልደ ኢትዮጵያዊ በኮንስትራክሽንና መሰል ሥራዎች ካልሆነ በስፖርት ዘርፍ እንዲሰማራ የሚያበረታታ ነገር እንደሌለ የሚናገሩት ዶ/ር ፀጋዬ፣ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዳያስፖራ ያላት ኢትዮጵያ በዚህ በኩል እየተጠቀመች እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...