Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ማሳተፍ አንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ እንደሆነ አልተረዱም›› ወ/ሮ ሳባ ገብረ መድኅን፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

 

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ባለፉት ሦስት አገራዊ ምርጫዎች የዕጩ ሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ፣ የተለያዩ የአቅም ግንባታና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማዘጋጀቱ ይታወሳል፡፡ ዘንድሮ ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫም የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማጠናከር የተለያዩ የውይይት መድረኮችን እያዘጋጀ ነው፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአየርላንድ በጀንደር ራይትስና ግሎባላይዜሽን ያገኙት ወ/ሮ ሳባ ገብረ መድኅን የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (ኒዋ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ ለበርካታ ዓመታትም በልዩ ዓቃቤ ሕግነት አገልግለዋል፡፡ ከምሕረት ሞገስ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንዲህ ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ሴቶች በተለያዩ ዘርፎች እንዲሳተፉና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሥራት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዘንድሮ የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫ በማስመልከት፣ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጨምር የተለያዩ መድረኮች እያዘጋጃችሁ ነው፡፡ ሒደቱ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ሳባ፡- እስካሁን በነበረን አካሄድ የሴቶችን ከማኅበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የምርምርና የክትትል ሥራ ስናከናውን ነበር፡፡ የመሬት መብት ተጠቃሚነታቸቸውን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ተጫውተናል፡፡ በኢኮኖሚ ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆኑም አበርክቶ አድርገናል፡፡ የሴቶችን ተጠቃሚነት ስንናገር ሁንተናዊ ነው፡፡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ከሴቶች ተጠቃሚነት ውስጥ የምንነጣጥላቸው ጉዳዮች አይደሉም፡፡ ስለዚህ የሴቶች ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ፣ ውሳኔዎች ለሴቶች በሚሆኑና ፍላጎትን ባካተተ መንገድ እንዲተላለፉ ይረዳል፡፡ በሌላ በኩል ሰብዓዊ መብታቸውና  እኩልነታቸው ይረጋገጣል፡፡ እስካሁን ድረስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ግፊት በማድረግ፣ ጥናት በማካሄድና ውይይት በማዘጋጀት ከዚህም አልፎ ዕጩ ሴት ተመራጮችን በመደገፍ ስንሠራ ነበር፡፡ አሁን የተለየ የፖለቲካ ዓውድ ውስጥ ስለምንገኝና እስካሁን ከነበረው በጣም በተለየ ሁኔታ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ እንቅስቃሴ ስለገቡ፣ እነዚህ ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ የሚሳተፉ ከሆነ ሴቶችን ያሳተፈ ሥርዓት እንዲከተሉና ሴቶች ወደ ሥልጣን መምጣት እንዲችሉ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሥራ ጀምረናል፡፡

ሪፖርተር፡- የምርጫ ሕጉ ላይ የሴቶች የምርጫ ተሳትፎ ወይም ተመራጭ ሆነው እንዲቀርቡ የሚያስችል ሥርዓት እንዲኖርም ስትንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ስለዚህ ቢያብራሩልን?

ወ/ሮ ሳባ፡- ከምርጫ ሕጉ ነበር የጀመርነው፡፡ የሴቶች የምርጫ ተሳትፎ በምርጫ ሕጉ እንዲካተት ሞክረን ነበር፡፡ የምርጫ ቦርድ በተወሰነ ሁኔታ ያስቀመጣቸው አሉ፡፡ ሴቶችን ወደ አመራር ለሚያመጡ የሚሰጠው ድጋፍም አለ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ባለፈ እኛ አስበን የነበረው፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን በኮታ እንዲያስገቡ ነበር፡፡ ይህ ግን አልሆነም፡፡ ስለዚህ አሁን አያደረግን ያለነው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማገዝ ነው፡፡ በውይይት፣ በሥልጠና፣ አቅም በሚፈልጉበት ዘርፍ አቅም በመገንባት ሥራውን ጀምረናል፡፡ እስካሁን ጥሩ እየሄድን ነው፡፡ ሆኖም ዕጩዎች ገና ስላልቀረቡ በምን ያህል መጠን ሴቶችን ያሳትፋሉ የሚለውን አላወቅንም፡፡ ነገር ግን የመግባባት ነገር ይታያል፡፡ ይህ ጥሩ ነው፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን ሴቶችን እንዳላሳተፉ አምነዋል፡፡ ለማሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸውም ነግረውናል፡፡ ይህ እንዴት ተግባራዊ ይሆናል የሚለውን ከዚህ በኋላ የሚያደርጉት ጥረት ይወስነዋል፡፡ እኛም የምናደርገው ድጋፍ ይኖራል፡፡ ሁለታችንም ሚናችንን ከተወጣን፣ እነሱም የፖለቲካ ቁርጠኝነት ካሳዩና እኛም ድጋፋችንን ከቀጠልን የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ማምጣት ይቻላል፡፡ ማኅበረሰቡ ላይ ያለው ግፊት የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያጠናክር ሌላው መንገድ ነው፡፡

ሴቶች በምርጫ ለመሳተፍ ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ፣ ኅብረተሰቡ ሴቶችን ያልያዘ የፖለቲካ ሥርዓት አልቀበልም ማለት እንዲችል ማድረግ አለብን፡፡ አጀንዳውን በተከታታይ ግንዛቤ፣ ኅብረተሰቡ የሚሳተፍባቸው የመገናኛ ብዙኃን ውይይት ስናካሂድ ወደፊት እናመጣዋለን፡፡ ሴቶችን የፖለቲካ ተሳታፊ ለማድረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሴቶች ራሳቸውና ማኅበረሰቡ ወሳኝ ናቸው፡፡  እኛም የአቅም ውስንነት ቢኖርም ዕገዛ እናደርጋለን፡፡ በተለይ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ የዴሞክራሲ ሒደቱ አንድ አካል አድርገን ማሳየት አለብን፡፡ ትልቁ ችግር ስለሴቶች ሲወራ ሌላ ክፍል፣ ስለፖለቲካ ሲወራ ሌላ ክፍል ተደርጎ መታሰቡ ነው፡፡ ነገር ግን የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ጥያቄ የዋናው የዴሞክራሲ፣ የምርጫ፣ የፖለቲካ፣ በነፃነት የመደራጀትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ የምንላቸው የፖለቲካ መብቶች አካል ነው፡፡ ሴቶችን ወደዚህ ካላመጣንና ሐሳባቸው ካልተካተተ፣ ራሳቸው እንዲመሩ ወይም በፖለቲካ ሒደቱ ሐሳባቸው እንዲገለጽና እንዲታይ ካላደረግን፣ ግማሹን የኅብረሰብ ክፍል እየተውን ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ጥረት አድርገን ገጽታውን መቀየር አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ እስካሁን ጥሩ ብንሄድም የቀሩት ጊዜያት ከማጠራቸው የተነሳ ብዙ መሥራት፣ መተባበርና መተሳሰር የሚፈልግ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን በኮታ እንዲያካትቱ የቀረበው ምክረ ሐሳብ ተቀባይነት ያላገኘው ለምንድነው? ይህ ምን ያሳጣል?

ወ/ሮ ሳባ፡- ሴቶችን በፖለቲካ ማሳተፍ ከባድ ነው የሚል ብዥታ አለ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከባድ የሆነ ነገር እላያችን ላይ እየጣላችሁ ነው፣ ሴቶችን ሊስብ የሚችል ነገር የለንም ይላሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ ሴቶችን በአነስተኛና ጥቃቅን፣ እንዲሁም በሌሎች ሲያሳትፍ ስለቆየ ሴቶች ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመምጣት ዕድል አላቸው፡፡ ገዥው ፓርቲ መዋቅሮችን ተጠቅሞ ለመቀስቀስም ሆነ ለማሳተፍ ዕድሉ አለው የሚል ጉዳይ አንስተው ነበር፡፡ በሌላ በኩል ፖለቲካ በፍላጎት የሚሳተፉበት እንጂ፣ ሴትን ምረጡ አንልም የሚል ሐሳብም ተነስቷል፡፡ በእኛ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቋማት ስለሆኑ ማንኛውም ተቋም እንደሚጠየቀው ሁሉ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መጠየቅ አለባቸው ብለናል፡፡ ለምሳሌ አሁን በመንግሥት ካቢኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሴቶችን ተሳትፎ 50 በመቶ አድርገዋል፡፡ በቀጣዩ ምርጫ የምናያቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ካላካተቱ ነገ በሚኖረው ፓርላማ የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቷል ከተባለ ሴቶችን ማሳተፍ ግድ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ማለትም ሴቶችን ማሳተፍ እንጂ ማግለል አይደለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ማሳተፍ አንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ እንደሆነ አልተረዱም፡፡

በሌላ በኩል ከመሰል ጋር መሰባሰቡ አለ፡፡ ወንዶች ከሆኑ ከወንዶች፣ ሴቶች ሲሆኑ ከሴቶች ጋር ይሰባሰባሉ፡፡ ነገር ግን ወንዶች ከሴቶች ጋር አብረው መሥራት እንዳለባቸው ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉን ያሳተፈ ስብስብ ከሆነ በርካታ ደጋፊ ይገኛል፡፡ አለበለዚያ በአንድ ዓይን ብቻ ነው የሚታየው፡፡ አብሮ መሆን የበለጠ ዕድል ይፈጥራል፣ የዜጎችንም መብት ያስከብራል፡፡ በእኩልነት፣ በተሳትፎና በውክልና የሚያምን ተቋም ሴቶችን ማሳተፍ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን የውዴታ ግዴታ አለባቸው፡፡ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ አቋማቸው አድርገው ቢሠሩበት ጥሩ ነው፡፡ ብዙዎቹም ፓርቲዎች ሴቶችን ማሳተፍ የሚለውን ተቀብለውት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ሴቶችም ወደ ፖለቲካው መምጣት አለባቸው፡፡ እኛም መቀስቀስ አለብን፡፡ ሴቶች ከፖለቲካው ርቀው የቆዩ ስለሆኑ ወደ ፖለቲካ እንዲመጡ መወትወት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም በሁሉም አቅጣጫ መሠራት አለበት፡፡ ዕጩ እንዲሆኑ የምንፈልጋቸው ሴቶች፣ መራጮችና ፓርቲዎች ላይ መሥራት አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- የሴቶችን ተሳትፎ አስመልክቶ በነበረው መድረክ ገዥው ፓርቲ አልነበረም፡፡ ለምንድነው?

ወ/ሮ ሳባ፡- ልክ ነው፡፡ የመጀመርያው መድረክ ላይ ተሳትፈው ነበር፡፡ የሁሉም ፓርቲዎች መሳተፍ አስፈላጊ ነው፡፡ የአሁኑ ላይ ከኢሕአዴግ [ብልፅግና] ከኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ተገኝተው ነበር፡፡ ሴቶችን በፖለቲካው ለማሳተፍ የሚደረግ ውይይት ለሁሉም የሚያስፈልግ ነው፡፡ ቀጣዩ ሌላ ምርጫ ነው፡፡ ለምርጫው ይህንን ታሳቢ እያደረገ ካልሄደ ዋናውም ፓርቲ ጉድለት ሊገጥመው ይችላል፡፡ እስካሁን ዕጩ ተመራጮች ስላልታወቁ፣ ምን ያህል ሴቶችን አምጥተዋል የሚለውን አልገመገምንም፡፡ ያለን ጊዜ አጭር ስለሆነ ለሁሉም ፓርቲዎች በተለያየ መንገድ መልዕክት እያስተላለፍን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣዩ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎ ያንሳል የሚል ሥጋት እንዳለዎት በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡ ይህ ሥጋት ከምን መነጨ? ምን ዓይነት መፍትሔስ አለ?

ወ/ሮ ሳባ፡- ሥጋቱ ትክክለኛ ሥጋት ነው፡፡ ሆኖም ሥጋት ሆኖ ሊቀር ይችላል፡፡ ቅድመ ዕርምጃዎችን እንድንወስድ የሚያስችል ሥጋት እንጂ፣ በእርግጠኝነት የሚመጣ አደጋ አለ ለማለት አይደለም፡፡ ምን ዓይነት አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ የሚለው ይታያል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋቱ፣ ሴቶች በፓርቲዎች ውስጥ እንዲሳተፉ ፍላጎት መኖሩ፣ በአንድ ወይም በሁለት የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ ተወስኖ ሳይሆን፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አማራጮች መኖራቸው አዎንታዊ ነው፡፡ ሥጋታችን ባለፈው ምርጫ በኢሕአዴግ የነበረው የ38 በመቶ የሴቶች ኮታ፣ አሁንም በሌሎች ፓርቲዎችም ተጨምሮ ካልቀጠለ የሕግም ግዴታም ስለሌለባቸው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደውና ፈቅደው የሴቶችን ተሳትፎ ካላጠናከሩ፣ የነበረው 38 በመቶ የሴቶች የፓርላማ ተተትፎ ይቀንሳል የሚል ሥጋት አለብን፡፡ የሴቶች ተሳትፎ ሁሌም በየጊዜው የሚቆጠር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ‹በጀንደር ኢንዴክስ› ከነበራት ዝቅተኛ ቦታ በአንዴ ከፍ ያለችው፣ የካቢኔ ሴት አባላት ቁጥር 50 በመቶ ሲሆን ነው፡፡ የፆታ እኩልነት ከሚለካባቸው ነገሮች አንዱ ሴቶች በውሳኔ ሰጪነት ያላቸው ቦታ ነው፡፡ አንዱ ትልቁ መለኪያ ደግሞ ሴቶች በፓርላማ ያላቸው መቀመጫ ነው፡፡ በቀጣዩ ምርጫ ይህንን አስጠብቀን ካልሄድን ኢትዮጵያ በጀንደር ኢንዴክስ ያገኘችውን የተሻለ ሥፍራ ታጣለች፡፡ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ አለመኖር በተለይ ለእኛ በሴቶች እንቅስቃሴ ውስጥ ለቆየን ሰዎች ወደኋላ ነው እንዴ የምንሄደው ብለን እንድንሠጋ ያደርገናል፡፡ ነገር ግን ሥጋቱ ሊቀረፍ የሚችል ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልብ ብለው ከሄዱ እስካሁንም ዕጩ ስላላቀረቡ፣ ዕጩ ሲያቀርቡ ሴቶችን አካተው ለመወዳደር ዕድሉ አለ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስቀመጡት ኮታ ባይኖርም ከ40 በመቶ በላይ ሊያቀርቡ የሚችሉበት ዕድል አለ፡፡ ይህንን ያደርጋሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ለማወያየት ከመጥራታችሁ በፊት፣ ፕሮፋይላቸውን ስታዩ የሴቶች ተሳትፎ ምን ይመስላል? በፓርቲዎች ውሳኔ ሰጪነት ቦታ ላይ የሴቶች ጥመርታስ እንዴት ነው?

ወ/ሮ ሳባ፡- ከዚህ ቀደም በፓርቲዎች ላይ በሠራነው ዳሰሳ በአመራር ላይ አንድ ፓርቲ ውስጥ አንዲት ሴት ብቻ አግኝተናል፡፡ አሁን ደግሞ ሲመዘገቡ እናያለን፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ግን በጣም በጥቂት ቁጥር የሚገለጹ ሴቶች በአመራር ደረጃ ያሉባቸው አሉ፡፡ በአብዛኛው ግን የሉም፡፡ ነገር ግን ዳግም ምዝገባ ሲካሄድ ራሳቸውን አደራጅተው ስለሚመጡ፣ የሚመጣ ለውጥ ይኖራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በፓርቲ ምዝገባ ጊዜ በርካታ ሴቶችን በአባልነት ይዘው ቢመጡ እንኳን፣ በኋላ ለምርጫ በዕጩነት ያመጧቸዋል ወይ የሚለው ዋናው ጥያቄ ነው፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች ውስጥ በርካታ ሴቶች በአባልነት ተካተው አይተናል፡፡ ነገር ግን በአመራርነት ላይ አያሳትፏቸውም፡፡ ብዙ ሴት በአባልነት ማካተታቸው ለምዝገባ ይረዳቸዋል፡፡ ነገር ግን አመራርነት ላይ አያመጧቸውም፡፡ የአሁኑ ምዝገባ ግን ይህንን ይለይልናል ብዬ አምናለሁ፡፡ የፓርቲዎችን የውስጥ መዋቅርም ያሳየናል፡፡ የመጨረሻው መለያችን ግን ፓርቲዎች ዕጩ ተወዳዳሪ ሴቶችን አስቀምጠዋል ወይ የሚለው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሴቶች ተሳትፎ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አለመካተት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት በየመገናኛ ብዙኃን በሚደረጉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚም ሆነ የማኅበራዊ ጉዳይ ውይይቶችም የለም ማለት ይቻላል፡፡ አወያዮቹ፣ ተወያዮቹ፣ አስተያየት ሰጪዎቹም በብዛት ወንዶች ናቸው፡፡ ሴቶች አንዳንዴ ቢገኙ ነው፡፡ ይህንን ችግር እንዴት መቅረፍ ይቻላል?

ወ/ሮ ሳባ፡- የሴቶችን አጀንዳ የፖለቲካ አጀንዳ ማድረግ አለብን፡፡ በቅርብ ቀን አንድ ስብሰባ ሳወያይ መጀመርያ የነበረው አጀንዳ መገናኛ ብዙኃን ላይ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ሁሉም በትጋት ተሳትፈዋል፡፡ ሁለተኛው አጀንዳ ከሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ጥናትም ይቀርብ ነበር፡፡ ነገር ግን ተሳታፊዎች ግንዛቤ ለማግኘት እንኳን ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ የሴቶች አጀንዳ ለሴቶች፣ ለተወሰኑ ድርጅቶች፣ በመገናኛ ብዙኃንም ከሆነ ለሴት ፕሮግራም አዘጋጆች የተተወ ይመስለኛል፡፡ እኛ ራሳችን የሴቶችን ጉዳይ ወደ ‘ሜንስትሪም’ አጀንዳው ማምጣት አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ የሴቶች ጉዳይ ለሴቶች የተለየ ጊዜ፣ ፕሮግራም፣ ክፍል በመስጠት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አጀንዳዎች ውስጥ መካተት አለበት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙኃን ሲቀርቡ እምብዛም የሴቶች አጀንዳ ሲነሳላቸው አናይም፡፡ በተለያዩ ፖሊሲዎቻቸው ውስጥ ሴቶችን እንዴት ያሳትፋሉ የሚለው መነሳት አለበት፡፡ አንድ ሰው ለውይይት ሲጋበዝ ስለሴቶች ትጠየቃለህ ወይም ትናገራለህ ተብሎ ሳይሆን፣ የሴቶች ጉዳይ በመደኛው አካሄድ ገብቶ ነው፡፡ በየመድረኩ የሴቶች በብዛት አለመኖር ብቻ ሳይሆን፣ የሚነሱት አጀንዳዎች ሴቶችንም የሚመለከቱ መሆናቸው ከግንዛቤ መግባት አለበት፡፡ ነገር ግን ፖለቲካ ሲሆን ወንዶች፣ ሌላ ጉዳይ ሲሆን ሴቶች የነበረው የተለመደ አካሄድ መለወጥ አለበት፡፡ ፆታ የሴት ብቻ ሳይሆን የኅብረተሰብ አካል ተደርጎ መታየት ያለበት፡፡ ይህን የአመለካከት ችግር ልንለው እንችላለን፡፡ በተለምዶ የመሄድና አንድ መድረክ ሲዘጋጅ ሌላኛውን አካልና አቅጣጫ አለማሰብ ይታያል፡፡ ለዚህም ነው በተደጋጋሚ ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል የምንለውና ድጋፍ እያደረግን የምንገኘው፡፡

ሪፖርተር፡- ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በነበረ መድረክ ሴቶችን ታች ባለው ደረጃ ብናሳትፋቸው ይሻላል፣ አመራር ላይ ግን አይሆንም፡፡ ምክንያቱም በምንፈልጋቸው ጊዜ አይገኙልንም፣ በርካታ ኃላፊነት አለባቸው፣ ፖለቲካው እንኳን ለሴት ለወንድም አስቸጋሪ ነበር የሚሉ አስተያየቶችን የሰነዘሩ ነበሩ፡፡ ይህ አግላይ ምክንያት ሊሆን አይችልም?

ወ/ሮ ሳባ፡- እኔ አግላይ እለዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ‹ሴቶች ሲጠሩ እኮ አይገኙም› ብሎ አንዱ ከተናገረ ሌላውም ሳይሞክረው ይህንን ያስባል፣ ውዥንብር ውስጥ ይገባል፡፡ አንድ መገናኛ ብዙኃን አንዲት ሴትን ሲጠራት አልተመቸኝም ብትለው፣ ለወንዶች ባለሥልጣናት እንደሚሰጠው ጊዜ ያህል ለሴቶቹም መስጠት አለበት፡፡ በራስ በኩል ያለውን ክፍተት በሌሎች ማመካኘት፣ ሌሎች ጉዳዩን እንደ ቅድመ መከላከያ እንዲጠቀሙበት ያደርጋል፡፡ ምን ያህል ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሁኚ፣ ይህንን ተቋም ምሪ ተብላ ተጠይቃ እምቢ እንዳለች አላውቅም፡፡ ሴቶች ተጋብዘዋል ወይ? ከተጋበዙስ የት ነው? የሚለው መታየት አለበት፡፡ ሴቶች በአብዛኛው ለኃላፊነት የሚጋበዙት ከሴቶች ጋር ለተያያዘ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላ ቦታ ላይ ብዙም አይጋበዙም፡፡ ነገር ግን ሴት እንድትመራ መጠራት ያለባት፣ የግድ የሴት ጉዳይ ሲሆን ብቻ አይደለም፡፡ ፖለቲካውንና የተለያዩ የትምህርት፣ የጤና፣ የኢኮኖሚና ሌሎችንም ዘርፎች ልትመራ ትችላለች፡፡

ሪፖርተር፡- በማኅበረሰቡና በተለያዩ ተቋማት በኩል ሴቶች ሲናገሩ እምብዛም ቦታ አለመስጠት፣ ሐሳባቸውን ያለ መቀበል ሁኔታ አለ፡፡ ይህን ለመቀየር በእንተ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ተቋማት ምን መሠራት አለበት?

ወ/ሮ ሳባ፡- ይህ ትክክል ነው፡፡ የማኅበረሰብ ቅስቀሳ መካሄድ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ማኅበረሰቡ ካላመነበት ሴቶች የሚሉትን አይቀበልም፣ ወደ ላይም አያመጣትም፡፡ በአገራችን ብዙኃኑ በሴት እኩልነት አምናለሁ ይላሉ፡፡ እውነት ያምናሉ ወይ? የሚለው የሚያጠራጥርና በተግባር የምናየው ከሚነገረው የተለየ ነው፡፡ በአፍ እኩል ናት ቢባልም ባህሉም፣ አስተሳሰቡም ወደ ቀደመው ሊወስደው ይችላል፡፡ ማኅበረሰብን በመቀስቀስና በመለወጥ ላይ የበለጠ መሠራት አለበት፡፡ በተለይ በማኅበረሰብ ላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ያሏቸው ድርጅቶች፣ ማኅበረሰቡ ሴቶች ላይ ያለውን አመለካከት እንዲለውጥ መሥራት አለባቸው፡፡ ልማት ላይ ባተኮሩ ፕሮጀክቶች ብቻም ለውጥ አናመጣም፡፡ የአመለካከት ለውጥ ነው ወደ ተለያዩ አዎንታዊ ተግባራት የሚቀይሩት፡፡ ኅብረተሰቡን ለመለወጥ እየሠራን ከሆነ የማኅበረሰብ አመለካከት ላይ በጀት መድበንና ትኩረት ሰጥተን ልንሠራ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ከነበረው አካሄድ በተለየ መንገድ ለውጥ እንዲመጣ ይፈለጋል፣ አገሪቱ ማደግና እኩልነት መስፈን አለበት ከተባለ ይህንን ለማሳካት ወደ ፖለቲካው ከምትመጣ ሴት ምን ይጠበቃል?

ወ/ሮ ሳባ፡- ፖለቲካውን፣ የፖለቲካውን ምኅዳር፣ አጀንዳዎችን ማወቅና አቋም መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ሴቶች የመሪነት ሥፍራ እንዲይዙ እንፈልጋለን፡፡ ስለሆነም ሴቶች የፖለቲካ አቋማቸውን ተረድተው መሄድ አለባባቸው፡፡ በልጦ ለመገኘትም ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ፖሊሲዎችን ማወቅ፣ የሚጎዱ አሠራሮችን መለየት፣ መሪ ለመሆን በፓርቲ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ያለችበትን ማኅበረሰብ ማወቅ፣ መገንዘብና ማገልገል እንደሚገባት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ አባል ናት፣ የሴቶችም ምሳሌ ናት፡፡ ሌሎች ሴቶች እሷን ተከትለው እንደሚመጡ ማሰብ አለባት፡፡ እንደ ሴት ፖለቲከኛ ከሴቶች ድርጅቶች ጋር በመተባበር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የተለያዩ ድርጅቶች ላይ ያለውን ዕውቀት መጠቀምም ለሴት መሪዎች አጀንዳ ይፈጥራል፡፡ ጉዳዩ የሴት ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ነው፡፡ የማኅበረሰቡን ችግር መረዳትና ምላሽ መስጠትን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የትም ቦታ ብትሆን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አቋም መያዝ አለባት፡፡ እንዲሁ አቋም አለኝ ለማለት ሳይሆን ራሷ ሰምታ፣ አውቃና ተረድታ የምትይዘውን አቋም እስከ መጨረሻ ልትገፋበት፣ መስዋዕትነት ልትከፍልበት መዘጋጀት አለባት፡፡ ሴቶች ወንዶች ባበጁት ፍሬም ስለሆነ የሚገቡት የራሳቸውን አጀንዳ መቅረፅ አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን የሰው ልጅ ሁሉ ማድረግ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ስለምርጫ ሥልጠና እየሰጣችሁና የውይይት መድረክ እያዘጋጃችሁ ነው፡፡ ይህ ከምርጫው በኋላም ይቀጥላል?

ወ/ሮ ሳባ፡- ፕሮጀክታችን ከምርጫ ባለፈም የተቀረፀ ነው፡፡ ከምርጫ በፊት የምንሰጠው ሥልጠና አለ፡፡ በምርጫ አልፈው ፓርላማ ከገቡ በኋላም ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል፡፡ የተለያዩ ፖሊሲዎችና የአመራር ክህሎት ላይ ሥልጠናዎች ይኖራሉ፡፡ ሥልጠናውን ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንዶችም መስጠት እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ ባለፈም ለፖለቲካ ፓርቲዎች የፆታ እኩልነት ላይ ሥልጠና የመስጠትና ፖሊሲ ሲቀረፅ የማገዝ ሥራ ይኖረናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...