Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፌዴራል ፍርድ ቤቶች ክሶች ሒደት አስተዳደር መተግበሪያ መመርያ ረቂቅ ተግዳሮትና ተቃውሞ ገጠመው

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ክሶች ሒደት አስተዳደር መተግበሪያ መመርያ ረቂቅ ተግዳሮትና ተቃውሞ ገጠመው

ቀን:

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያዘጋጀው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔርና መሰል ጉዳዮች ሒደት አስተዳደር መተግበሪያ መመርያ ረቂቅ በተለይ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ዳኞች ተቃውሞ ገጠመው፡፡

ረቂቁ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር 2011 ዓ.ም. የተዘጋጀ ቢሆንም፣ ለውይይት የቀረበው በዚህ ዓመት ነው፡፡ ረቁቁን ለማፅደቅ ቅዳሜ ታኅሳስ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ከፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች ጋር በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል ሙሉ ቀን በተደረገ ውይይት ላይ፣ ዳኞች ተግዳሮቶችንና ተቃውሞዎችን አንስተዋል፡፡

የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔርና መሰል ጉዳዮች ሒደት አስተዳደደር ቀልጣፋ፣ ግልጽና ተገማች በማድረግ የጉዳዮች ሒደትና የዕልባት ጊዜ መጓተት የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ መቀነስ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ከመሆኑ አንፃር መመርያው መዘጋጀቱን ዳኞቹ ጥሩና አስፈላጊ መሆኑን ቢደግፉም፣ በቅድሚያ ሊተገበሩ የሚገቡ ተግባራት እንዳሉ ግን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ መመርያውን ለማዘጋጀት ተደርጓል ስለተባለው ጥናት አስተያየታቸውን የሰጡ የውይይቱ ተሳታፊ ዳኞች እንደተናገሩት፣ ጥናት ሲጠና መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ዝም ብሎ ‹‹ጥናት አጥንተን ነው መመርያ ያወጣነው›› ለማለት ከሆነ፣ ነገ ተመልሶ ያው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መመርያውን ለማፅደቅ የተዘጋጀው ውይይት ጥሩ ቢሆንም፣ የማይተገበር መመርያ ማዘጋጀት ግን የኅብረተሰቡን የፍትሕ ጥማት የማያረካ መሆኑን በምሳሌ አስረድተዋል፡፡ ከአሠሪና ሠራተኛ ጋር የሚነሳን ክርክር በሚመለከት በ‹‹አሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ›› ቀነ ገደብ ተዘጋጅቶለት ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አስገዳጅ የሆነውን አዋጅ እንኳን ማስፈጸም እንዳልተቻለ በመግለጽ ያሉትን ተግዳሮቶች ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ከነባራዊ ሁኔታው በመነሳት ‹‹ለምን ማስፈጸም አልተቻለም?›› የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ለመመለስ፣ ከሥር መሠረቱ መሬት ላይ ያለውን ችግር ማየትና ምላሹን ማግኘት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንኳን በመመርያ በአዋጅ ተደንግጎ የሚገኘውን አስገዳጅ ሕግ መፈጸም እንዳልተቻለ እየታየ የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔርና መሰል ጉዳዮችን ሒደት አስተዳደር መመርያ በጥንቃቄና ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ሳያጣጥሙ ማፅደቅ መልሶ ያው ነው ብለዋል፡፡

አንዳንድ ያደጉ አገሮችን አሠራር በመመልከት ወይም አጋዥ ኃይሎች ድጋፍ ስላደረጉ ብቻ ‹‹የጉዳዮች ሒደት አስተዳደር መተግበሪያ መመርያ እናውጣ›› ማለት ተገቢ አለመሆኑን ዳኞቹ በአስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመርያ ለማውጣት በአገሪቱ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች ያለው ነባራዊ ሁኔታ ማለትም ‹‹ችግራችን ምንድነው?›› የሚለውን ጥያቄ በጥንቃቄ፣ በዝርዝርና ሁሉንም ባሳተፈ አኳኋን ጊዜ ተሰጥቶ ውይይት በማድረግ እንጂ የይድረስ ይድረስ መሆን እንደሌለበትም አሳስበዋል፡፡ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከተፈገለና ዘላቂ የሆነ መመርያ ለመተግበር ከሆነ፣ በአግባቡ መታየት እንዳለበትና ዝም ብሎ ጊዜ የሚወስድና ወጪ የሚያስወጣ መሆን እንደሌለበት አክለዋል፡፡

ሁሉም ዳኞች በጥናቱ ሳይሳተፉ፣ ተቃውሞአቸውንና ድጋፋቸውን ከሙያ አንፃር ሳይገልጹ ዝም ብሎ መመርያና ሕግ እያወጡ ይተግበር ማለት ውጤታማ ሊያደርግ እንደማይችል የገለጹት ዳኞች፣ ጥናት ሲጠና አንድ ችሎትን ለሙከራ በመውሰድና ከውዝፍ መዝገቦች ነፃ በማድረግ በታሰበው መመርያ መሠረት ጉዳዮች ተግባራዊ መሆን መቻል አለመቻላቸውን በማየት ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል እንጂ፣ ከ150 እስከ 200 የሚደርሱ ውዝፍ መዝገቦች የያዘን ችሎት መመርያውን ተግባራዊ እንዲያደርግ አስገዳጅ አሠራር ማስቀመጥ የማይሆን እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በርካታ መሟላት ያለባቸው መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች፣ ማለትም ችሎቶች ዳኞችን በብቃት ሳይሟሉ፣ በተለይ የምስክሮች አጠራር ሁኔታ ሳይስተካከል መመርያ አውጥቶ ‹‹ጉዳዮች በዚህ ጊዜ ተጀምረው በዚህ ጊዜ ማለቅ አለባቸው›› ማለት፣ የሌሎችን የመሰማት መብት መጋፋት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ለምስክሮች መጥሪያ ለማድረስና ማስረጃ ሰነዶችን ለማግኘት ያለውን ውጣ ውረድና የሚወሰደውንም ጊዜ ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል፡፡ በተለይ ምስክሮችን በሚመለከት በቴሌቪዥን የሚጠሩበትን ሕጋዊ መሠረት አስይዞ መተግበር፣ ቅድሚያ የሚሰጠውና መሠረታዊ ነገር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ ቤት ጉዳዮች ሒደት መተግበሪያ መመርያ ማውጣት የፈለገው የዳኝነት ነፃነት፣ ተጠያቂነትና ሚዛናዊነት ተጠብቆ ዜጎች ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ ፍትሕ የማግኘት መብታቸው እንዲረጋገጥ መሆኑን ገልጿል፡፡ ‹‹የዘገየ ፍትሕ እንደተከለከለ ይቆጠራል›› የሚለውን አባባል ለማስቀረት ብቻ ሳይሆን፣ ባልዘገየ ቀነ ገደብ ውስጥ ፍትሕ የመስጠት ባህልና አሠራር ለመዘርጋትም መሆኑን አብራርቷል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ለፍርድ ቤት የቀረቡ ጉዳዮች ተመሳሳይ በሆነ ቀነ ገደብ ውስጥ ዕልባት አግኝተው፣ ባለጉዳዮች ከዳኝነት ሥርዓቱ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል መመርያው አስፈላጊ መሆኑም በረቂቁ ተጠቁሟል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች ግን የረቂቁን የሕጋዊነት ጥያቄ በማቅረብ ተቃውመዋል፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መመርያውን የማውጣት ሥልጣን እንደሌለው በመጠቆም፣ ሥልጣን ባለው አካል እንዲዘጋጅም አሳስበዋል፡፡

የሕዝብን እሮሮ መንግሥትም ሆነ የፍርድ ቤት ኃላፊዎች እንደማያውቁና እንደማይረዱት የገለጹ አንድ አስተያየት ሰጪ፣ የሕዝብ አመኔታ ለማግኘትና የተሻለ ፍትሕ ለመስጠት ችግሩን ማዳመጥ (ባለጉዳዩን) አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የፍትሕ ሳምንት ወይም ወር እያሉ መሰብሰብ ፍትሕ አያሰፍንም፤›› ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ የፍርድ ቤት ባለጉዳይ ችሎት ከመግባቱ በፊት ቀድሞ በመድረስ፣ በመጠየቅና በመረዳት ችግሩን ለማስወገድ መጣር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የመመርያውን ረቂቅ ‹‹የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መሠረታዊ ሐሳቦች›› በሚል ርዕስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ዳይሬክተር ዳኛ ሰላማዊ ግርማይ አቅርበዋል፡፡ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ከሕግ አንፃር በሚል አጭር ጽሑፍ በዓለም ባንክ ተወካይዋ ፋንቱ ፋሬስና የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አንፃር የሚል ጽሑፍ ደግሞ አቶ ብዙነህ በቀለ በተባሉ የአይቲ አማካሪ ቀርቧል፡፡ ውይይቱን የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አሸነፈች አበበ በንግግር የከፈቱ ሲሆን፣ የፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ንዋይ አወያይተዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...