Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ አይቀየርም አሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ17 ዓመታት በኋላ ተሻሽሎ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው አዲሱ ረቂቅ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ላይ ማሻሻያ እንደማይደረግ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስታውቁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼንን ያሉት ቅዳሜ ታኅሳስ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው፣ የኤሌክትሮኒክስ የአንድ መስኮት አገልግሎትን ይፋ ሲያደርጉ ነው፡፡

አዲሱን ረቂቂ አዋጅ በሚመለከት ታክስ ተጨምሯል በሚል ከፍተኛ ሽብር በከተማ ውስጥ እንዳለ መስማታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን እየገቡ ያሉት መኪኖች አገሪቱ በስፋት መኪና ማምረት ስትጀምር የት እንጣላቸው የሚባልበት ጊዜ ስለሚመጣ፣ ነጋዴዎችና አስመጪዎች የማይቀየር መሆኑን አውቀው ወደ አዲሱ መንገድ ለመሄድ እንዲሞክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይኼ አዋጅ የማይቀየርበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ከአንድ ሚሊዮን የማይበልጥ መኪና ነው ያለው፡፡ 110 ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት አገር አንድ ሚሊዮን የመኪና ባለቤቶች እንዳያኮርፉ ተብሎ ሕግ አይቀየርም፡፡ 109 ሚሊዮን መኪና የሌለው ሰው ስላለ፤›› ብለው፣ በተደማጭነት ሳይሆን ለብዙኃኑ በሚጠቅም መሆን ስላለበት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ይሁንና ለታክሲ ባለንብረቶችና የብዙኃን ትራንስፖርት ለሚያቀርቡ ሰዎች የተለየ ድጋፍ ተደርጎ አዳዲስ መኪኖችን እንዲያስገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡

መንግሥት ያስተዋወቀው አዲሱ አሠራር ከረዥም ጊዜ አንፃር አዋጭ ስለሆነ፣ ምናልባት በደንብ ያልተገነዘቡ ሰዎች መንግሥት ብዙ ገቢ ለማስገባት ብሎ ያወጣው ሕግ አድርገው እንዳያስቡ፣ ይልቁንም ብዙ ገቢ ለማስገባት ሳይሆን ገቢ በመቀነስ ብዙ ሰዎች ለማዳን መሆኑን ከግንዛቤ እንዲከቱ ጠይቀዋል፡፡

አዲሱ የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ከስኳር፣ ከምግብ፣ ከዘይት፣ ከአልባሳትና ከጌጣጌጥ አንስቶ እስከ የእርሻ መሣሪያዎችና ትራክተሮች፣ እንዲሁም ሌሎች ተሽከርካሪዎች ድረስ እስከ 500 በመቶ የሚደርስ ታክስ የጣለ ሲሆን፣ ከሰባት ዓመታት በላይ ያገለገሉ አውቶሞቢሎች ከፍተኛው ታክስ ተጥሎባቸዋል፡፡ የዚህ ዕሳቤ አሮጌ መኪና ከመግዛት ይልቅ አዲስ መግዛት ለነዳጅና ለመለዋወጫ ከሚወጣው ወጪ፣ እንዲሁም ከትራፊክ አደጋ ጉዳቶች ያድናል የሚል እንደሆነ ከሳምንት በፊት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ተናግረው ነበር፡፡ ከተሽከርካሪዎች በተጨማሪ በአልኮልና በሲጋራ ምርቶችም ላይ ከፍተኛ ታክስ ተጥሏል፡፡

ይኼንን አያይዘው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ኤክሳይስ ታክስ የተፈለገበት ዋናው ምክንያት በአሮጌ መኪናና በመጠጥ ላይ ተጨማሪ ታክስ በመጨመር የመንግሥትን ገቢ ማሻሻል ብቻ ሳይሆን፣ ከሲጋራና ከመጠጥ የሚገኘው ገቢ በቀጥታ ለጤና ሚኒስቴር ፈሰስ የሚደረግና እዚያ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚውል ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን በቀን ምን ያህል ሰው በካንሰር፣ ምን ያህል ሰው በወባ እንደሚሞት ስለማታውቁና ፌስቡክም ስለማይናገር፣ ተጠያቂ የጠፋበት አንዱ ችግር [ሆኖ] የማይተላለፉ በሽታዎች በጣም ብዙ ሰው እየቀጠፉ ነው፡፡ ስትሮክና ካንሰር በጣም ብዙ ሰው እየቀጩ ነው፡፡ ግን መድኃኒት የላቸውም፡፡ ይኼንን መከላከል ባለቤት እንደሌለው እየተወሰደ ስለሆነ በአንድ በኩል መጠጥና ሲጋራን ላለማበረታታት፣ በሌላ በኩል ከዚያ የሚገኘውን ገቢ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፈሰስ በማድረግ በዚያ ረገድ ያለውን አደጋ ለመቀነስና የእናቶች፣ የሴቶችንና የሕፃናትን ሞት ለመቀነስ መሆኑን ከግምት በማስገባት መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለፓርላማው የተመራው ረቂቅ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ፣ ቀድሞውንም ከፍተኛ የሆነውን የአገሪቱን ታክስ ያከፋዋል በሚሉና በተጠቃሚዎች ላይ የኑሮ ጫና ያመጣል በሚሉ ወገኖች ከፍተኛ ተቃውሞ እየቀረበበት ይገኛል፡፡ በተለይ አምራቾች እኛ ዋጋ እንድንጨምርና ተጠቃሚው እንዲጎዳ ይደረጋል ሲሉ፣ የተወሰኑት ደግሞ ማስፋፊያዎቻቸውን ከማከናወን እንደተቆጠቡ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አገሪቱ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ለመሳብ በምታደርገው ጥረት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ሲሉ የሚከራከሩ አልጠፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች