የሰዎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማግኘት ከሚቻልባቸው መድረኮች “ማስ ስፖርት” ተጠቃሽ ነው፡፡ ሰዎች ዕድሜ፣ ጾታና የአመለካከት ልዩነታቸውን ወደ ጎን ብለው የሚመስላቸውን አካላዊ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፣ ይዝናናሉ፣ በአጠቃላይ ፍላጎታቸውን የሚያጣጥሙበት ዓይነተኛ መድረክ ለመሆኑ ባለፈው እሑድ ታኅሣሥ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተከናወነው 6ኛው ከተማ አቀፍ የማስ ስፖርት ትዕይንትና እንቅስቃሴ በማሳያነት መመልከት ይቻላል፡፡
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ የአገር አቀፉና የከተማ አስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽነሮችና ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ስታዲየም “ውበት” በሚል የሚታወቁትን የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች፣ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የሰርከስ ባለሙያዎች እንዲሁም በርካታ የከተማዋ ነዋሪ የታደመበት 6ኛው ከተማ አቀፍ “ማስ ስፖርት” ትርጉም ያለው ሆኖ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡
በመስኩ የቀረቡ መዛግብት እንደሚያስረዱት ከሆነ “ማስ ስፖርት” ጤናማና አምራች ዜጎችን ከማፍራት ጎን ለጎን፣ ለአገራዊ ሰላምና አንድነት የሚያበረክተው ፋይዳ ትልቅ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን፣ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት፣ የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽንና የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ስለ ከተማ አቀፍ ማስ ስፖርት በጋራ ቀደም ሲል በሰጡት መግለጫ፣ ዝግጅቱ በከተማው ከዚህ በፊት ከተደረጉት ተመሳሳይ ፕሮግራሞች በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ የተሻለ ሆኖ እንደሚዘጋጅ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
እንደ ከተማ አስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽን መረጃ ከሆነ፣ የከተማዋ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል ይችል ዘንድ ፕሮግራሙ ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡ እየተዳከመ ለመጣው ለአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ስፖርት ከዚህ የተሻለ መፍትሔ እንደማይኖር የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ዮናስ አረጋይ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በርካታ የዝግጅቱ ታዳሚዎችም የኮሚሽነሩን አስተያየት ይጋራሉ፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዱ፣ “ቀደም ባሉት ዓመታት እንዲህ እንደ አሁኑ ቁጥሩ የበዛ ባይሆንም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በትምህርት ቤቶች፣ በወታደራዊ ተቋማት፣ ወረዳና ቀበሌ ጨምሮ በሌሎችም ተቋማት ማስ ስፖርት ስለሚዘወተር በሁሉም ስፖርቶች አሁን ላይ የሚስተዋለው ዓይነት የውጤት ቀውስ አልነበረም፤” በማለት ትውስታቸውን ያወሳሉ፡፡
ከሚጠበቀው በላይ የተሳታፊው ቁጥር የተመዘገበበት 6ኛው ከተማ አቀፍ ማስ ስፖርት፣ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደነዚህ የመሰሉ መድረኮች ሲያጋጥሙ አይደለም፣ በትንንሽ ዝግጅቶች ሲከሰቱ ከታዩ መሰል አለመግባባቶችና ሁከቶች የፀዳ፣ ከዚህ ይልቅ ብሔራዊ አንድነትን የሚያቀነቅኑና ማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ሕብረ ዝማሬዎች የተደመጡበት፣ የታዩበት መድረክ ሆኖ ታይቷል፡፡
በዕለቱ ዝግጅት በሁሉም የአዲስ አበባ ወረዳዎች የሚገኙ የስፖርት ጽሕፈት ቤቶች፣ ሠላሳ ሁለት የስፖርት ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ከፍተኛ የሥራ አመራሮች፣ ሕጻናትና በዕድሜ የገፉ አረጋውያን በአጠቃላይ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል መሳተፋቸው ታውቋል፡፡ ከአዲስ አበባ የተውጣጡ የሰርከስ ባለሙያዎች ትዕይንት ለዝግጅቱ ልዩ ድምቀት ነበር፡፡ የማስ ስፖርት ፕሮግራም ከከተማ ወደ አገር አቀፍ ከፍ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁ የተነገረ ከመሆኑ ባሻገር በቀጣዩም ባህር ዳር ከተማ ላይ እንዲደረግ ቀጠሮ መያዙ ጭምር ተነግሯል፡፡