Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልለኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለውለታ የተሰናዳው ድግስ

ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለውለታ የተሰናዳው ድግስ

ቀን:

የድምፃውያንና የሙዚቀኞችን ሥራ ከኅብረተሰቡ ዘንድ በማድረስ ረገድ በዘመናዊቷ አዲስ አበባ ታሪክ ከሚጠቀሱት ውስጥ የሙዚቃ ቤቶች (መደብሮች) በቀዳሚ ይወሳሉ፡፡ በ1960ዎቹ የሙዚቃ ሥራን በቴፕ ካሴቶች ማሳተምና ማሠራጨት ከመጀመሩ በፊት ሥራዎች ይቀርቡ የነበሩት በሸክላ ነበር፡፡

በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች ባህር ማዶ ድረስ በመዝለቅ ስማቸው ጎልተው ከተሰሙት ሙዚቃ ቤቶች ከግንባር ቀደሞቹ አንዱ ‹‹ታንጎ ሙዚቃ ቤት›› ነበር፡፡ ኮከቧ ድምፃዊት አስቴር አወቀ ስትነሳ ከመጀመርያዋ እስከ አምስተኛዋ ካሴት ድረስ አብሯት የሚነሳው ታንጎ ነው፡፡ እንዲሁም ዓሊ ቢራ፣ ንዋይ ደበበ፣ (የጥቅምት አበባ) ወዘተ. ከታንጎ ጋር ስማቸው ይያያዛል፡፡

ታንጎ ሙዚቃ ቤት የቆረቆረውና ሙዚቃን የማሳተምና የመነገድ ሥራ የገባው አቶ ዓሊ አብደላ ካይፋ (በቅጽል ስሙ ዓሊ ታንጎ) ነው፡፡ ከሸክላ ማጫወቻ፣ ወደ ቴፕ ሪኮርደር ከቴፕ ወደ ሲዲ እየተሸጋገረ በመጣው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሒደት ውስጥ በተለይ ቀደም ባለው ዘመን በ1960ዎቹ አጋማሽና በ70ዎቹ ሙዚቃን በማሳተም አቶ ዓሊ አብደላ (ታንጎ) ተጠቃሽ ስም እንዳለው ይወሳል፡፡

የመጀመርያውን ሸክላ የዓለማየሁ ቦረቦር ‹‹በላያ በላያ›› ካሳተመ በኋላ የብዙነሽ በቀለ፣ ዓለማየሁ እሸቴ፣ መሐሙድ አህመድ፣ አያሌው መስፍን፣ ሙሉቀን መለሰ፣ እርሱ ‹‹ሸገኔዎች›› ብሎ ባወጣላቸው ስም የእነ አሰለፈች አሽኔና ጌጤ ሥራን በሸክላ አሳትሞ ለገበያ አቅርቧል፡፡ ከአብዮቱ መምጣት በኋላ የሸክላ ኅትመት ሥራ ሲቀዛቀዝ ወደ ካሴት ኅትመት በመግባትም ሥራውን ሲቀጥል ቀዳሚ ሥራው የታዋቂው የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቹ ኃይሉ መርጊያ ነው፡፡

የዋሊያስ ባንድ አባሉን የኃይሉ መርጊያ በሙዚቃ መሣሪያ ብቻ ለተቀነባበረ የካሴት ቀረፃ በድምፅ ለማጀብ ከሀገር ፍቅር ከመጡት ሦስት ድምፃውያን መካከል ድምፃዊት አስቴር አወቀ አንዷ ነበረች፡፡ ድምጿን ሲሰማው ትልቅ ተስፋ የሚጣልባት መሆኗን በመገመት የመጀመርያዋንና ከዚያም በኋላ አምስት ተከታታይ ካሴቶችን በማስቀረፅ ለዕውቅና እንዳበቃት ይወሳል፡፡

 ታንጎ ሙዚቃ ቤት ካይፋ ሪከርድስ በተለይም ለወጣት ድምፃውያንና ለሌሎችም ዕውቅ ድምፃውያን ከ1973 ዓ.ም. እስከ 1977 ዓ.ም. ብቻ ከ53 የሚሆኑ የሙዚቃ ሥራዎችን አሳትሞ ለሕዝብ አቅርቧል፡፡

ዓሊ ታንጎ በሸክላ ያስቀረፃቸውን ሥራዎችና የኢትዮጵያን ሙዚቃዎች በመውደዱ ‹‹ኢትዮጲስ›› በሚል የዘፈን ስብሰብ በማዘጋጀት ለዓለም ያስተዋወቀው ፍራንሲስ ፋልሲቶ የዓሊን የሸክላ ኅትመቶች በኢትዮጲስ የ13ኛ ሲዲ ኅትመት ላይ ‹‹ወርቃማዎቹ 70ዎቹ›› ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡

ከ76 ዓመታት በፊት በጅማ ከተማ ውስጥ ከየመናዊ አባቱና ከኢትዮጵያዊ እናቱ የተወለደው ዓሊ አብደላ ካይፋ (አሊ ታንጎ) በዕድገቱም ከትምህርቱ ጎን ለጎን የአባቱን የቡና ንግድ ያከናውን የነበረ ሲሆን፣ በእግር ኳስ ችሎታውም ተመርጦ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ለአምስት ዓመት ተጫውቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሙዚቃን በማዳረስ አሻራውን ያኖረውን ዓሊ አብደላ (ታንጎ) ‹‹የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለውለታ›› በሚል ክብርና ዕውቅና የሚሰጥ ዝግጅት ሐሙስ ጥር 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት በሸራተን አዲስ ተዘጋጅቷል፡፡ መድረኩን ኢትዮ ግሬት ኢንቨስትመንት ሰፖርት ሰርቪስ ከኪነ ጥበቡ ቤተሰብ፣ ከመንግሥት አካላትና ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...