Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መሸሽ አይቻልም!

እነሆ መንገድ። ከመርካቶ ወደ መገናኛ ልንጓዝ ነው። እዚያ ሰማይ አለ። ከሰማዩ በታች ታኅሳስን እንደ በረዶ ያቀዘቀዘው ቅዝቃዜ አለ። ከሰማዩ በታች የታክሲው ጣራ አለ። ከጣራችን በታች ያልተከፈለበት፣ ያልተቆጠበበት፣ በዕጣ ያልተሰጠን ትንፋሻችን አለ። በትርፍነት ከታጎሩት አራት ሰዎች ትንፋሽ ጋር ተዳምሮ የ18 ሰዎች ትንፋሽ መስኮቶቹ ላይ የደመና መጋረጃ ሠርቷል። በዚህ ሁሉ ትፍግፍግ ውስጥ ነው እንግዲህ ወያላው ቅጠሉን እየቀነጠሰ ጉንጩን በመወጠር የተጠመደው። ‹‹ምናለበት ሥራ ላይ እንኳ ብትተወው? ለአንተስ ቢሆን ምን ምቾት አለው?›› ይሉታል ከሾፌሩ ጀርባ ለብርድ የደረቡትን ጃኬታቸውን እያስተካከሉ የሚቁነጠነጡ አዛውንት። ‹‹በረደኛ! ምን ላድርግ ታዲያ? ቅቅል ድንች እንዳልበላ ድንቹን እየነቀለ ጫት የሚያበቅለው አራሽ ነጋዴ በሩን ዘጋው። እንኳን ቀዝቅዞን እንዲሁም በርዶናል አባት፤›› ይላል ወያላው። ምክንያት በየቦታው አያሳጣ ማለት ይህ አይደል!

‹‹ወይኔ የሰውዬው ልጅ! እኔ ሥልጣን ቢኖረኝ ይኼን ጫት የተባለ ተክል ነበር ከምድረ ገጽ ጠራርጌ የማጠፋው፤›› ብላ መሀል መቀመጫ ጥጓን ይዛ የተሰየመች ወጣት ስታጉተመትም፣ ‹‹ለምንድነው ግን ሰው ሥልጣንና ጥፋትን አጣምሮ የሚመኛቸው?›› ብሎ መጨረሻ ወንበር ከተሰየሙት አንዱ ጠየቀ። ‹‹እኛ ምኑን አውቀን ወንድሜ! የናፈቀን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሆኖ ሳለ፣ ምርጫና አማራጭ የሚያቀርብ ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ ሳለ፣ የሚያስታርቅና የሚመክር ሽማግሌ ሆኖ ሳለ፣ ያም እየተነሳ እኔ ሥልጣን ቢኖረኝ ብሎ ስለመጨፍጨፍ፣ ያም ተነስቶ ስለመደምሰስ፣ ያም ዘሎ ስለመደፍጠጥ፣ ያም እየፎከረ መሬት ዘርፎ ሕንፃ ስለመገንባት ያወራል። እንዴት አንድ እንኳ እኔ ሥልጣን ቢኖረኝ ይኼን በገዛ ፍላጎቱና ሐሳቡ መመራት የሚፈልግ ሕዝብ የናፈቀውን የአገር ባለቤትነት ስሜት መልሶ እንዲያገኝ፣ በትንሽ ትልቁ ጉዳይ ምርጫው የራሱ እንዲሆን ጠበቃ እቆምለታለሁ የሚል ጀግና ይጠፋል?›› ብሎ አንድ በአንድ በአንክሮ መነጠረን። የነፃነት ታጋይ ነኝ ባዩ ሁሉ በተቃራኒው ማዕዘን ቆሞ ሲመዘን፣ የባርነት ጠበቃ እየሆነ አስቸግሮ እኮ ነው እንዲህ የሚወራው፡፡ ከወሬ የዘለለ ስንት ነገር አለ እኮ!

ጉዟችን ከተጀመረ ጥቂት ጊዜ አልፏል። ጨዋታው ገና መጀመሩ ነው። ‹‹ምንድነው እንደዚህ የጫት ጉዳይ ሁሌ ሲካበድ የምሰማው?›› ብሎ ሦስተኛው ረድፍ ላይ አጠገቤ የተቀመጠ ሲጠይቅ፣ ‹‹ከብዶን ነዋ የምናካብደው። ይህች ማካበድ የምትባል ቃል መቼም ከአምባገነኖቻችን በላይ ተጫውታብናለች እኮ እናንተ? ያቃለልን መስሎን አታካብድ አታካብጂ ስንባባል ኖረን ይኼው ዛሬ ነገር ሁሉ አናታችን ላይ ወጣ፤›› አሉ አዛውንቱ በጥልቅ የሐዘን ስሜት። ወያላው ተራውን ጉዳዩ ይመለከተዋልና፣ ‹‹ወይ አያበሉን ወይ አያስቅሙን። ፖለቲከኛው ሳይቀር በጫት መርቅኖ አገር ሲያተራምስ በደሃ መጫወት የሚወደው በዝቶ ነው ብራዘር፤›› አለው። ያኛው ቀጠለ፣ ‹‹እኔ እኮ ምን ለማለት ፈልጌ መሰላችሁ? ከኢትዮጵያ ውጭ ብዙ አገር ኖሬያለሁ። እንደ ጫት ዓይነት አወዛጋቢ ዕፆችን በተመለከተ ግን በዓለም ላይ እንደ ሆላንዳውያን የዘየደ አላየሁም። እዚያ ያውም ማሪዋና በግላጭ ይጨሳል፣ ይሸጣል። መንግሥት ከሽያጩ ታክስ ይሰበስባል። ድብብቆሽ የሚባል ነገር የለም። ሰው ሁሉ ተፈቅዶለት የሚኖረው ግን ምንም እንዳልተፈቀደለት ነው። ጭር ባለ ሌሊት አሽከርካሪው ቀርቶ እግረኛው አረንጓዴ መብራት ካልበራለት አስፋልት አይሻገርም። በመከልከል አያምኑም ግን ደግሞ ምንም ነገር አይተላለፉም። ከተጻፈው የነፃነት ሕጋቸው ያልተጻፈው ገደባዊነት ይታይባቸዋል፤›› አለ፡፡ ምሳሌማ ብዙ ነበር አዳማጭ ጠፋ እንጂ!

‹‹ኧረ አሳጥረው አቦ ናሽናል ሶሺዮሎጂ አደረግከው?›› እኮ ብሎ አንድ ወጣት  ፈገግ አደረገን፡፡ ‹‹እኔ እዚህ አገር ብዙ ነገር አይገባኝም። በአንድ ወገን ከስንት ዓመታት በፊት የሠራ የታይዋንና የኮሪያ የዕድገት ተሞክሮ ዛሬ ካልሠራ ብሎ ችክ ይባላል። በጎን ደግሞ ማኅበራዊ ጉዳዮችና ጥያቄዎች በጥበብ፣ በሰው ልጅ ሥነ ልቦና ፍላጎት ላይ ተመሥርተው እንደ አሸዋ በባህር የሚመሰለውን ሕዝብ የገደቡ ሰዎች ተሞክሮ አይታይም። እስከ መቼ ነው ግን ተከልከል በአዋጅ ፀባይ የሚነግሠው? ሰው ይለወጣል ተብሎ የሚታሰበው?›› ሲል፣ ‹‹ኢሕአዴግ ያልሰማው ጉድ ኒዮሊብራሊዝም ታክሲ መሳፈር ጀምሯል?›› ብሎ ከጀርባችን አንዱ ያላግጣል! አላጋጭ ሲበዛ ያስጠላል!

ጉዟችን ቀጥሏል። አሁንም መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ተሳፋሪዎች መሀል ጠና ያለች ወይዘሮ በአይፎኗ ፌስቡክ እየጎረጎረች ቆይታ፣ ‹‹በምን ቀን ነው የፌስቡክ አካውንት የከፈትኩት?›› ብላ ጨዋታ ጀመረች። ‹‹አቤት ሰው ግን የምርጫ ካርድ ለማውጣት አይመዘገብም፡፡ ፌስቡክ ላይ ግን ሲንጋጋ አንደኛ ነው፤›› ይላል በሹክሹክታ ዳያስፖራው። ምናልባት የዘመኑ የምርጫ ካርድ ፌስቡክ ሆኖስ እንደሆን?›› ብላ ወይዘሮዋ ስትመልስለት ወዳጃችን ደነገጠ። ‹‹ሰምተሽኝ ኖሯል እንዴ?›› ሲላት እንደ ማፈር ብሎ፣ ‹‹ምነው ስንት አገር አላየህም እንዴ? አንዳንዴ የሚይዝ እየያዘን እንጂ እኛም የሶሻል ኔትወርኩ አባል ነን፤›› አለችው። ‹‹አባልነት ብቻ ምን ዋጋ አለው? ቁም ነገር ካልሠሩበት?›› አለች ከሾፈሩ ጀርባ ያለው ረድፍ ላይ የተሰየመች ቆንጆ። እንዲህ ነው እንጂ ሞጋች!

‹‹እስኪ በነካ ምላስሽ አስታውሽን ቆንጂት ቁም ነገር ምንድነው?›› ሲላት ጋቢና የተሰየመ አፍሮ፣ ‹‹ሐሳብን በሐሳብ ማሸነፍ፣ መመዘን፣ ሳያላምጡ አለመዋጥ፣ ወዘተ. የመሳሰሉት ናቸው፤›› አለችው። ‹‹አቤት ወደፊት ማትሪክ ምርጫ መሆኑ ቀርቶ አብራሩ ይዞ የመጣ ቀን፣ ይኼ ሶሻል ኔትወርክ የማይናቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ባንቺ አየሁ፤›› ሲላት፣ ‹‹ለተጠቀመበት፤›› ብላ ድምፅ አልባ ፈገግታ አሳየችው። ‹‹ላይቭ ቻት መሆኑ ነው፤›› ይለኛል ዳያስፖራው። መቼም ታክሲ ውስጥ ስንገናኝ ‹ሎግ አውትና ሎግ ኢን› ያለን አንመስልም። ምናልባት ብሶታችን መውጫና መግቢያ ተምታቶበት ይሆን? አይምታታብን ማለት ነው!

ወያላችን ምርቅን ብሎ ሃምሳ ሳንቲም ለሚገባው አምስት ብር ይመልሳል። አሥር ብር ለሚሰጠው ሃምሳ ሳንቲም ያቀብላል። ያም ያም ይወርድበት ጀምሯል። አንዱ፣ ‹‹እንደተምታታባቸው ፖለቲከኞቻችን አሥር ብርና ሃምሳ ሳንቲም አትለይም?›› ብሎ ሲጮህበት ከጎኑ ተደርቦ የተቀመጠ ነጭ ጃኬት ለባሽ፣ ‹‹ሁለቱ ልዩነት አላቸው እንዴ?›› ብሎ ነገር ጀመረው። ‹‹አሁን ገና ጨዋታ አመጣችሁ . . .›› ትላለች ወይዘሮዋ። ‹‹ይብላኝ በይሉኝታ ለተወጠሩት እንጂ ለዘንድሮ ፖለቲከኞችና ጀሌዎቻቸው አሥሩም አምስቱም ያው ሆኗል፤›› አሉ አዛውንቱ። ‹‹ምነው አባታችን መቶውን ረሱት?›› ሲላቸው ከጎናቸው፣ ‹‹ተው! የከዳና የተከዳ አታዘበራርቅ። መቶ እኛ ዘንድ በመንፈስ ካልሆነ በአካል ገብቶ አያውቅም። አሁን ኪስህ ያለች ይመስልህ ይሆናል። ግን እኮ ሰማዩም ያለ እየመሰለህ እንጂ ኖሮ አያውቅም፤›› ከማለታቸው አዛውንቱ፣ ‹‹እንዴ ሰማዩም ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ የልማት አቅጣጫ አልላቀቅም አለ እንዴ?›› ብሎ መጨረሻ ወንበር የተሰየመ ጮኸ። በጩኸት ዘመን እየኖረ እንዴት አይጮህ!

‹‹እኮ ምን የሚያስጮህ ነገር አለ?›› ሲለው አጠገቡ የተሰየመ ተሳፋሪ በሽቆ፣ ‹‹እንዴት አልጮህም አብዮትና ዴሞክራሲ ያላቻ ተጋብተው?›› ብሎ አፈጠጠበት። ሁለቱ ሲፋጠጡ ያየች ከመካከለኛ ረድፍ የአንዱን ኮሳሳነት የአንዱን ፈርጣማነት አስተውላ፣ ‹‹ወይ ዘንድሮ! ያላቻ ከሚጋባው ያላቻ የሚፋጠጠው አላስቀምጠን አለ እኮ እናንተ?›› ብላ አሸሞረች። ‹‹ደግሞ መቼ ተቀምጠን እናውቅና? ተቀምጠውብን እንጂ?›› ሲላት ከጎኗ የተሰየመ ጎልማሳ፣ ‹‹ኧረ እባካችሁ እናንተ ልጆች የሽግግሩ ዘመን በሰላም አልፎ ለምርጫ እንብቃ። ከአሁን አሁን ቀውስ ውስጥ ገባን እያልን እንጨነቅ? ወይስ እኛ ራሳችን ወንበዴ ሆነን እንተራመስ ነው የምትሉት?›› ሲሉ አዛውንቱ፣ ‹‹ምነው አባት ተቆጡ? መፋጠጥ እኮ ያለ፣ የነበረ፣ ወደፊትም የሚኖር ነው፤›› አለ ጎልማሳው። ጥያቄው መፋጠጡ ለምን ዓላማ ነው የሚለው ላይ ታዲያ ይሰመርበት!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጋቢና ከተሰየሙት ተሳፋሪዎች አንደኛው በስልክ ወሬ ይዟል። ‹‹አይዞህ ወዳጄ! እኔ የቤት ባለቤት ሳልሆን ሦስተኛው የዓለም ጦርነት እንደማይጀመር በሕልሜ አይቻለሁ. . . እመነኝ ስልህ. . . ፑቲን?. . . መቼ? ግድ የለም እኔ የቤት ባለቤት ሳልሆን ሦስተኛው የዓለም ጦርነት የሚባል ነገር አይኖርም፤›› ይላል። ‹‹የምን ጦርነት ነው እሱ?›› አዛውንቱ ብርግግ አሉ። ጎልማሳው፣ ‹‹አልሰማችሁም? ጓድ ፑቲን እኔ ከዚህ ወዲያ የምዕራባውያንን ህቡዕ አጀንዳ ማባበልና ማድበስበስ ሰለቸኝ ደከመኝ በማለት ይፋ ያወጡትን ሚስጥር?›› ሲል ሁላችንም ጆሯችን ቆመ። ‹‹ለነገሩ ማን ይነግረናል? ሚዲያዎቻችን እንዲህ ያለ ነገር አነፍንፎ ከማውራት ስለሮናልዶ የጫማ ክር መጥፋት ነው ማውራት የሚቀላቸው። ኢንተርኔቱም ለቻት አልሆነ እንኳን ለሰፊ ሐተታ ንባብ፤›› ካለ በኋላ ፑቲን በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት በአሜሪካና በአውሮፓውያን ጥፋት ሲጀመር እንደሚታያቸው ያብራሩትን አብራራልን። አሪፍ ማብራሪያ ሲገኝ ማን ይጣላል! 

‹‹ዲቪ ወደ ኢትዮጵያ ሞልታችኋል የሚባልበት ጊዜ እየመጣ ነው በለኛ?›› ሲል አንዱ፣ ‹‹ፍሬንድ! ውጊያው እኮ በቆመህ ጠብቀኝ ጠመንጃ አይደለም በኑክሌር ነው። እኛስ እዚህ ያለነው ተረፍን ይባል። እዚያ ማን ተርፎ ነው ዲቪ የሚሞላው?›› አለችው ነጭ ቶፕ ለባሽ ቆንጆ። ‹‹አይ ሰው? በቃ ሥልጣኔ ሄዶ ሄዶ የሚያውቀው አዋግቶ ማፈራረስ ነው?›› ስትል ወይዘሮዋ፣ ‹‹ምን ይደረግ? የሰው ልጅ ከትናንት ጥፋቱ አልማር አለ! የብሔርተኝነት ስሜት ገነነ! ዘረኝነት ገነነ! ሽብርተኝነት ገነነ! ቀበሌያዊነት ገነነ! እኔነነት ገነነ!›› እያለ ጎልማሳው አዲስ ነገር ሲያመጣ ወያላው ‹መጨረሻ› ብሎ በሩን ከፈተው። አንዳንዱ ግብግብ ብሎ ብሶቱን ሲዘረግፍ ሌላው እያላገጠ ይሰማዋል፡፡ የማይደርስበት ይመስል ራሱን ያሸሻል፡፡ መሸሽ ግን አይቻልም፡፡ መልካም ጉዞ!         

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት