Sunday, July 14, 2024

የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በመገናኛ ብዙኃን የሚያገኘው ሽፋን ምን ይመስላል?›› በሚል ርዕስ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ታኅሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡

በውይይቱ ላይ ሴቶች በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡበት መንገድ፣ የፖለቲካ ተሳትፏቸውና መገናኛ ብዙኃን ሴቶች ከፖለቲካው እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያላቸውን ሚና አስመልክተው ዳሰሳ ያቀረቡት በቻትሃም ሃውስ የያዳ ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያ ተወካይ ወ/ት ኤደን ሳህሌ እንደሚሉት፣ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እምብዛም ባልነበረበት የቀደሙት ዓመታት መገናኛ ብዙኃን ስለሴቶች ተሳትፎ አስፈላጊነት የጎላ ግንዛቤ ሲፈጥሩ አልነበረም፡፡

የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙኃን ሴቶችን የሚያቀርቡበት መንገድም ከሴቶች መጎዳት ጋር በተያያዘ ነበር፡፡ ይህ አቀራረብ የሚበዛውን ያህል በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ሴቶች ለኢትዮጵያ ያደረጉዋቸው አበርክቶዎች በብዛት አይቀርቡም ነበር፡፡

አብዛኞቹ ሴቶች በመገናኛ ብዙኃን ሲቀርቡ ደካማና ተጠቂ እንደሆኑና ረዳት እንደሚፈልጉ፣ ወንዶች ደግሞ እንደሚችሉ ነው፡፡ በፊልም፣ በማስታወቂያ፣ በማኅበራዊ ሚድያው የሚታየውም፣ የሴቶችን የመምራት ችሎታ ሳይሆን አገልግሎት ተቀባይ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተሻለ የመገናኛ ብዙኃን ዕድገት ቢኖርም፣ መገናኛ ብዙኃን ጠንካራ ተፅዕኖ መፍጠር የመቻላቸውን ያህል ለሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ትኩረት አለመስጠታቸው፣ ስለሴቶች መዘገብ ምን ማለት እንደሆነም አለመረዳታቸው፣ ተመሳሳይና አሳዛኝ ለሆኑ ክስተቶች ማድላታቸው መታየቱን ገልጸዋል፡፡  

ሴቶች በታሪክ ከፖለቲካ መራቃቸውና የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ካለማግኘታቸው ጋር ይህ ዓይነቱ አዘጋገብ ተጨምሮ፣ ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ገብተው ተፅዕኖ እንዳይፈጥሩ ምክንያት ሆኗል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ሆኖም አሁን የተፈጠሩ መልካም ዕድሎች ለመገናኛ ብዙኃንም ሆነ ለሴቶች ጥሩ መደላድልን የፈጠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

መገናኛ ብዙኃን የሴቶችን የፖለቲካ ተሳታፊነት ለማጠናከር የሚሰጡት ሽፋን አናሳ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ በፖለቲካው ውስጥ አሉ የሚባሉ ጥቂት ሴቶችም መገናኛ ብዙኃን ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር አለመቻላቸው፣ ራሳቸውን አለማውጣታቸውና የማኅበረሰቡን አመለካከት ለመቀየር ከመገናኛ ብዙኃን ጋር አለመሥራታቸው ተጠቅሷል፡፡

ወ/ት ኤደን እንደሚሉት፣ ማኅበረሰቡ ለወንዶች ብዙውን ነገር አቅልሎ ሠርቶላቸዋል፡፡ ሴቶች ግን ወደ ፖለቲካ ኃላፊነት ሲመጡ ከወንዶች ያልተናነሰ ወይም የበለጠ ዕውቀትና ችሎታ ቢኖራቸውም፣ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ወይ የሚል ጥያቄ ይነሳባቸዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በካቤኔ 50 በመቶ ሴቶች፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንትም ሴት ቢሆኑም ይህ የአንድ ሰሞን ዜና ከመሆን ባለፈ ስኬታቸው፣ እንዴት ለዚህ እንደበቁና ያለፉበት መንገድ ለሌሎች ሴቶች አርዓያ እንዲሆን ሲቀርብ አይስተዋልም፣ ያስመዘገቡት ውጤትም አይነገርም ሲሉ አክለዋል፡፡

አምና ጥር ላይ በተደረገ ዳሰሳ፣ ‹ሴቶች ፖለቲካ የእኔ ሥራ አይደለም፣ ፖለቲካ የወንዶች ነው› የሚል አመለካከት እንዳላቸው ለማየት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ይህም ቤተሰብ ልጆቹን ሲያሳድግ ለፖለቲካ ዝግጁ አድርጎ ካለማሳደጉ የመነጨ ሊሆን እንደሚችል አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባ በተደረገ ዳሰሳ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የመምራትን ኃላፊነት ለወንዶች መስጠታቸው የታየ ሲሆን፣ ሴቶች ትምህርታቸውን ከማሳደግ ባለፈ በፖለቲካ የመሳተፍ ፍላጎታቸው አናሳ መሆኑ ታይቷል፡፡ ወንዶች በሴት መመራትን ራስን አደጋ ውስጥ እንደ መክተት አድርገው የሚቆጥሩበት አመላካች ነገሮች አሉም ብለዋል፡፡

‹‹የሴቶች ጉዳይ የሴቶች ነው›› በሚል ወንዶች አጀንዳዎችን ወደ ሴት መግፋታቸው፣ ወንዶች ለሴቶች መለወጥ ቁልፍ መሆናቸውን አለመገንዘባቸው፣ ሁለቱም አብረው መሥራት እንደሚገባቸው መገናኛ ብዙኃን ትኩረት ሰጥተው አለመሥራታቸው መሠረታዊ ችግሮች ተብለዋል፡፡

ሴቶች ተፈጥሮ በሰጣቸው የመውለድ ፀጋ ከቢሮ የሥራ ኃላፊነት መራቃቸው፣ ሴቶች ሲወልዱ ከቢሮ ስለሚቀሩ ኃላፊነት አይገባቸውም የሚል የተዛባ አመለካከት መኖሩ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በንግድ ዓለም መኖሩም እንደ ችግር ተወስተዋል፡፡

በተለያዩ ዘርፎች ተፅዕኖ የፈጠሩ ሴቶች በሚዲያው ለመቅረብ ፍላጎት ማጣትና ሚዲያውም ስለነሱ አለመሥራቱ፣ ሃይማኖት፣ ባህልና የኅብረተሰቡ አመለካከት ሴቶች ላይ የፈጠረው ጫና በመገናኛ ብዙኃን በሚገባው መጠን አለመዘገቡ ሴቶች ወደ ሕዝቡ ዘልቀው ተፅዕኖ እንዳይፈጥሩ ካደረጉ ምክንያቶችም ይጠቀሳሉ፡፡

በቀረበው ሐሳብ ላይ አስተያየት የሰጡት የሴቶች ማረፊያና ልማት ማኅበር መሥራች ወ/ሮ ማሪያ ሙኒር፣ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ጥያቄ ሲነሳ ከ20 ዓመታት በፊት የገጠማቸውን አውስተዋል፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት በፓርላማ የሴቶች ኮታ መኖር አለበት በሚል የሕግ ባለሙያ ሴቶች ሐሳብ ሲያነሱ፣ ስሙን ባልጠቀሱት መገናኛ ብዙኃን ሴቶች አጫጭር ለብሰው በፓርላማ ጓሮ በር በደረጃ ሲገቡ የሚያሳይ ሥዕል ማስፈሩን አስታውሰዋል፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሳምንት አንዴ የሚቀርበው የሴቶች ፕሮግራም ወቅታዊ ጉዳይ በመጣ ቁጥር ይታጠፍ እንደነበርና ቀስ በቀስ ግን ሁኔታዎች እየተቀየሩ መምጣታቸውን፣ መገናኛ ብዙኃንም ምርጫ ሲመጣ ሽፋን እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሴቶች ራሳችንም ሆንን ሚዲያውን ክፍት አድርገን መሥራት አለብን፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ሴቶች ማኅበር የቦርድ አባል ወ/ሮ ቅድስት ክፍለ ዮሐንስ በበኩላቸው፣ ጥናቶች ወደኋላ የተሠሩ በመሆናቸው አሁን የተፈጠረውን ዕድል ይዞ መሥራት እንደሚገባ መክረዋል፡፡

‹‹ወንዶች እያንዳንዱን ነገር ሰብረው እንደሚገቡት ሴቶች እናደርጋለን ወይ?›› የሚለው እንዲታይ፣ ሴቶች ወደ ሚዲያው ለመቅረብ የሚፈሩበትን ሐሳብ መስበርም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ሚዲያው በደፈናው አልሠራም የሚባልበትን እንደማይስማሙ፣ ነገር ግን የሚገባውን ያህል ሠርቷል ወይ? ቢባል ጥያቄው እንደሚያስማማም አክለዋል፡፡

የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በመገናኛ ብዙኃን የሚዘገብበት መንገድ አሰልቺና ለማንበብም ሆነ ለማድመጥ የማይጋብዝ ነው ያሉት ወ/ሮ ሕይወት እምሻው ናቸው፡፡

ዘገባዎች ከእሮሮ የወጣ ቅርፅ ያስፈልጋቸዋል፣ ስኬት፣ ተስፋና የአሁኑን ትውልድ ያካተተ መሆንም አለበት ብለዋል፡፡

የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ምርጫ ሲቀርብ የሚጎላ መሆኑን፣ ሆኖም በሌላውም ጊዜ ትኩረት እንደሚፈልግም ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል ውክልና እንዲኖራቸው ማድረግ፣ ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ በኮታ እንዲገቡ ማድረግ፣ ሚዲያው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን እንዲያሳትፉ ተፅዕኖ እንዲፈጥሩ ማስቻል፣ በፓርቲዎች ውስጥ ፆታዊ እኩልነት ያለበት መረጣ ማድረግ፣ በወንድ ልጆች ላይ የሌሉ ገደቦችን ከሴቶች ላይ ማንሳት፣ ወንዶችና ሴቶች ተደጋግፈው እንዲሠሩ ማስቻል እንደሚያስፈልግ ወ/ት ኤደን አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ወ/ት ሶሊያና ሽመልስ፣ ቦርዱ በምርጫ አስፈጻሚነት በርካታ ሴቶችን ለማካተት ቢያስብም፣ ኃላፊነቱ ምርጫን ማስፈጸም በመሆኑ ከቦርዱ ይልቅ መገናኛ ብዙኃንና ሲቪል ማኅበራት ሴቶች ወደ ፖለቲካ ተሳትፎ እንዲመጡ ሊሠሩ ይችላሉ ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -