Friday, June 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዝቅተኛ ዋጋን የሚወስን የቡና የወጪ ንግድ መመርያ ሊተገብር ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መመርያውን የሚተላለፉ ላኪዎች ከአንድ ዓመት እስከ ወዲያኛው የሚታገዱበት ቅጣት ተቀምጧል

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ ከጥር 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባር ላይ የሚውል የቡና ሽያጭ ውል አስተዳደር መመርያ ይፋ አደረገ፡፡ መመርያው ከዋጋ በታች የሚሸጡና ውል የማያከብሩ ላኪዎችን እንዲከላከል ታስቦ የወጣ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ አማካይ የዓለም የቡና ዋጋን መነሻ በማድረግ ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋን እንደሚወስን ታውቋል፡፡

በባለሥልጣኑ የገበያ መረጃና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኸይሩ ኑሩ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ‹‹የወጪ ቡና ሽያጭ ውል አስተዳደር መመርያ ቁጥር 03/2012›› የተሰኘው አዲስ መመርያ ላኪዎች ወደ ውጭ የሚልኩት ቡና ዋጋ ከዓለም የወቅቱ አማካይ የቡና ዋጋ ጋር ተመሳክሮና በየዕለቱ ተተንትኖ እንደ ደረጃውና ጥራቱ መጠን ዝቅተኛ ዋጋ ይወሰንለታል፡፡

ከዝቅተኛ ዋጋ በታች መሸጥ እንደሚያስጠይቅ የገለጹት አቶ ኸይሩ፣ የመጀመርያ ደረጃ ጥፋት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደሚያስከትል አስታውቀዋል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ መመርያውን በመተላለፍ ከዝቅተኛው ዋጋ በታች የሸጠ ላኪ፣ ለአንድ ዓመት ከማንኛውም የቡና ግብይት እንደሚታገድ ሲደነገግ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ከዝቅተኛው ዋጋ በታች ሲሸጥ ከተገኘም የብቃት ማረጋገጫው ተሰርዞበት፣ የአገርን ጥቅም በማሳጣት ወንጀል ወይም አግባብ ባለው ሕግ መሠረት እንደሚጠየቅ መመርያው አሥፍሯል፡፡

በመመርያው ክፍል ሦስት በተቀመጠውና አቶ ኸይሩም ባብራሩት መሠረት፣ ወቅታዊ ዓለም አቀፍ አማካይ ዋጋ የሚወሰነው በየዕለቱ የቡና ዋጋና ግብይት ትንታኔ ተዘጋጅቶ የሽያጭ ዋጋው በባለሥልጣኑና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጋራ በሚወሰነው መሠረት ይፋ ይደረጋል፡፡ ላኪዎችም መረጃው በአግባቡ እንዲደርሳቸው እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

የቡናን አማካይ ዋጋ ለመወሰን መሟላት ከሚኖርባቸው ጉዳዮች መካከል፣ በቡና አምራች ኅብረት ሥራ፣ በዩኒየን፣ ቀጥታ ግብይት ትስስር፣ በተቆላ፣ በተፈጨና እንዲሁም በገፍ በሚቀርብ የቡና ዓይነትና የጥራት ደረጃ ላይ እንደሚመሠረት መመርያው አስቀምጧል፡፡

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያም፣ ከዋጋ በታች የሚሸጡትንና ከገዥዎች ጋር የገቡትን የሽያጭ ውል የማያከብሩ ላኪዎችን ለመቆጣጠር የሚተገበረው ይህ መመርያ፣ ላኪዎች የገቡትን ውል በ24 ሰዓት ውስጥ ለብሔራዊ ባንክና ለባለሥልጣኑ የማስታወቅ ግዴታ ይጥልባቸዋል፡፡ የተገባው ውል የቡናውን መጠን፣ የሚሸጥበትን ዋጋና የምርቱን የጥራት ደረጃ በዝርዝር ማሳየት ይኖርበታል፡፡

ይህ ከተደረገ በኋላ የቡናው ግብይት በ90 ቀናት ውስጥ ተፈጻሚ እንዲደረግ፣ የተሸጠው ቡና ለላኪው እንዲደርሰው ተደርጎ ገንዘቡም በተጠቀሱት ቀናት ውስጥ ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ እንዲደረግ ያስገድዳል፡፡ ይህ ሲደረግ ከገዙበት ዋጋ በታች መሸጥም ሆነ፣ የተገባን የሽያጭ ውል አለማክበር አስቸጋሪ እንደሚሆን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

2009 ዓ.ም. ጀምሮ ከ81 ያላነሱ ቡና ላኪዎች በኮንትራት ጥሰትና ከዋጋ በታች በመሸጥ ተግባር ውስጥ መሳተፋቸው ተረጋግጦ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውና እንዲታገዱ መደረጋቸውን አቶ ኸይሩ አስታውሰው፣ ከእነዚህ ውስጥ 16 ላኪዎች መረጃቸውን አቅርበው የተወሰኑት ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ከዘርፉ ከነጭራሹ በተለያዩ ምክንያቶች መውጣታቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እንደተገኙ ገልጸዋል፡፡ ሌሎች መረጃቸው ታይቶ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ተልኮ በጥፋተኝነት እንዳስፈረጃቸው አስታውቀዋል፡፡

እንዲህ ያሉትን ችግሮችን እንደሚቀርፍ የሚጠበቀው የወጪ ንግድ የቡና ግብይት መመርያ፣ ከጥር 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ አዱኛ (ዶ/ር) አስታውሰው፣ ከመመርያው በፊት የተገቡ የሽያጭ ውለታዎች ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን ሆኖም በሦስት ወራት ውስጥ ሽያጫቸውን አጠናቀው የሽያጩን ገንዘብ ወደ ብሔራዊ ባንክ ቋት ማስገባቱ እንደሚመለከታቸው አብራርተዋል፡፡ 

በሌላ በኩል 1,500 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት ዓለም አቀፍ የቡና ኮንፈረንስ፣ ዓውደ ርዕይና ፌስቲቫሎች የተካተቱበትን ዝግጅት ከአንድ ወር በኋላ ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ባለሥልጣኑ ይፋ አድርጓል። ከሚመጡት የውጭ ተሳታፊዎች መካከል ከ500 በላይ ቡና ገዎች፣ አልሚዎች፣ ቡና ቆይዎችና ምሁራን እንደሚገኙበት ተገልጿል።

ታኅሳስ 24 ቀን 2012 .. አዱኛ (ዶ/ር) በጽሕፈት ቤታቸው ከዘርፉ ማኅበራት ኃላፊዎች ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደውን ዓለም አፍ የቡና ኮንፈረስ፣ ዓውደ ርዕይና ፌስቲቫል ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ በመመረጧ ዝግጅቷን አጠናቃለች ብለዋል። በዚህም መሠረት ከጥር 28 እስከ ጥር 30 ቀን 2012 .. ዝግጅቱ በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

‹‹ኮፊ ድም ላንድ ኦፍ ኦሪጂንስ›› በሚል ስያሜ በሚካሄደው በዚህ ዝግጅት ላይ ለመታደም ከውጭ ከሚመጡት በተጨማሪ፣ 1,000 ገር ውስጥ ተሳታፊዎችና 56 የቡና ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ መሰናዳታቸው ታውቋል።

በሚሊኒየም አዳራሽ በሚዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ወቅት የኢትዮጵያ ቡናን የሚያስተዋውቅ አዲስ መለያ ወይም ብራንድ ይፋ እንደሚደረግ (ዶ/ር) አዱኛ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያን ቡና ዝርያዎች፣ ባህልና ትሁፊት የሚተዋወቁበት የኢትዮጵያ ቡና ፓርክም በኮንፈረንሱ ይፋ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች