Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የስኳር ኢንዱስትሪ ባለሙያዎችን ተስፋ ያነሳሳ ጅምር

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ መስክ የካበተ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ በገፍ ከዘርፉ እየተገፉ እንዲለቁ መደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ አብዛኞቹም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ውስጥ በመሠማራት ብሎም ከአገር በመውጣት ተበትነው እንደሚገኙ ሲገለጽ፣ በአሁኑ ወቅት ለዘርፉ በሚታሰበው ጅምር የለውጥ ሒደት ሳቢያ በርካቶች ተስፋ አድሮባቸዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ከየት ወዴት? የባለሙያዎች ሚና ለኢንዱትሪው›› በሚል ርዕስ፣ የኢትዮ ስኳር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ይኸው የባለሙያዎች ሚናና ተሳትፎ ጎልቶ ተደምጧል፡፡

ከዘርፉ ተገፍተው መውጣታቸውን የሚገልጹት ባለሙያዎች፣ ኢትዮጵያ በዓለም የሸንኮራ አገዳም ሆነ በስኳር ምርት ረገድ ትልቅ ደረጃ እንደነበራት ያወሱት ባለሙያዎች፣ ይህንን የኢትዮጵያ የቀድሞ ስኬታማነት ዳግም ወደ ቦታው ለመመለስ ባለሙያዎች ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተወስቷል፡፡ ይህ እንዲሆን ግን ባለሙያዎች ድርሻውን መወጣት እንዳለባቸው፣ የኢትዮ ስኳር አክሲዮን ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቢተው ዓለሙ አሳስበዋል፡፡ ባለሙያዎች ሚናቸውን ባልተወጡ ቁጥር ኪሳራው እንደሚያይል፣ ኢንዱስትሪውም አገርም እንደሚጎዱ ጠቅሰዋል፡፡

የአክሲዮን ኩባንያው የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ ጉርሙ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በሸንኮራ ምርት ረገድ ለዓለም የሚተርፍ ተሞክሮና የምርት መጠን መለኪያ ወይም መነሻ መሆን የምትችል አገር ስለመሆኗ ገልጸው፣ ባለሙያዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከዘርፉ እየተገፉ መውጣታቸው ግን ለኢንዱስትሪው መውደቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

የባለሙያዎቹ አስተያየት እንደሚያመላክተው፣ የስኳር ኢንዱስትሪው በቀድሞ ቁመናው ውጤታማነትና ምርታማነት መገለጫዎቹ ነበሩ፡፡ ዘርፉ የሚመራውም በዕውቀት ነበር፡፡ በወንጂ/ሸዋ፣ በመተሐራና በፊንጫኣ የስኳር ኢንዱስትሪ አብዮትን ያስጀመረው የኔዘርላንድስ ኩባንያ የሆነው ኤችቪኤ ነበር፡፡ ኩባንያው በውጤታማነት የመሠረታቸውን ፋብሪካዎች ተረክበው እስከ ቅርብ ጊዜ ሲያስተዳድሯቸው የቆዩት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ነበሩ፡፡

በዚህም መሠረት በ26 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ሦስቱ ፋብሪካዎች በዓመት ከሦስት ሚሊዮን ቶን በላይ የስኳር ምርት ለገበያ ማዋል የቻሉበት አቅም ተፈጥሮ ነበር፡፡ አሁን ወደ 13 አድገውም፣ በዓመት የሚመረተው ወደ 2.5 ሚሊዮን ቶን ወርዷል፡፡ ይህ ምርትም ቢሆን በእነዚሁ ሦስት ፋሪብካዎች አማካይነት እየተመረተ የሚቀርብ ስለመሆኑ ባለሙያዎቹ በቁጭት ያወሳሉ፡፡

ምንም እንኳ የባለሙያዎች ምስክር ከኢንዱስትሪው በገፍ መገለል ትልቅ ተፅዕኖ ቢያሳርፍም፣ ለዘርፉ ጥሩ የልማት አቅጣዎች ተጠንስሰው መተግበራቸው ትልቅ ጅምር እንደነበር ይጠቀስም ነበር። ይሁን እንጂ አካሄዳቸው ከኢንዱስትሪው አቅምና ደረጃ በላይ በመሆኑ፣ በአንድ ጊዜም 13 ፋብሪካዎች በነባሮቹ ላይ ለመጨመር የተኬደበት መንገድ ነባሮቹንም እንዳንኮታኮተ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።

ፋብሪካዎቹ በደጉ ጊዜ በሔክታር ከ180 እስከ 200 ቶን የሸንኮራ አገዳ ይመረት እንደነበር፣ ለዚህም የተቀናጀ ግብርናና የፋብሪካ ምርት አመራር ሥርዓት ስለነበር፣ እንዲህ ያለው ውጤታማነት ሲመዘገብ መቆየቱንና ወደፊትም ይህ ዓይነት አካሄድ መመለስ እንደሚገባው ያሳሰቡት ባለሙያዎቹ፣ ‹‹አሁን ዘርፉ ኦና ሆኗል፤›› በማለት ቁጭታቸውን ገልጸዋል።

በሸንኮራ አገዳ ምርት ረገድ ኢትዮጵያ የነበራትን ደረጃ አብራርተው ያስቀመጡት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ በአገዳ ምርትና በአገዳ ውስጥ በሚገኝ የስኳር መጠን ‹‹ኤክስትራክሽን ሬት›› ከ12 በመቶ ድረስ እንደነበር፣ ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያ ከአውስትራሊያ በመከተል በዓለም ሁለተኛዋ ተሰላፊ እንደነበረች አስታውሰዋል።

ይህንን የተረዱት ኔዘርላንዶች በወንጂና በመተሐራ ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ መነሻ ስለመሆናቸው የሚነገርላቸውን ፋብሪካዎች ተክለዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የፈነጠቀው የኢንዱስትሪ ባህል ወደ ተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ሊዛመትና ሊጎለብት ሲገባው፣ የነበሩትንም በቀደመ አምራችነታቸው ማቆየት አልተቻለም። አዳዲሶችም ተጨምረው፣ ኢትዮጵያ በዓመት ከ3.5 ሚሊዮን ቶን ያላነሰ የስኳር ምርት ለመሸመት የተገደደችበት የኋሊት ጉዞ ውስጥ ትዳክራለች።

በስኳር ኢንዱስትሪው መስክ በአመራርነት፣ በከፍተኛ ባለሙያነት ሲሳተፉ ከነበሩት ባሻገር በታች ሠራተኞች ዘንድም የቀድሞውንና የአሁኑን የዘርፉ ችግሮች ያወሱ አንጋፋ ተሳታፊም ስለዘርፉ ከወንጂ/ሸዋና ከመተሐራ ሠራተኞች አደራ ተቀብለው በስብሰባው እንደተገኙ ተናግረው፣ በጥዑም ገለጻቸው ስለኢንዱስትሪው አብራርተው ነበር።

ስለሠራተኞች የሥራ ህልውና አደጋ በማሳሰብ የጀመሩት እኝህ ሠራተኛ፣ የስኳር ኢንዱስትሪው ‹‹ከሕይወት ወደ ሞት፣ ከትርፍ ወደ ኪሳራ፣ ከላይ ወደ ታች፤›› መውረዱን አስረግጠው ገልጸዋል። ይህም ሆኖ የስኳር ዘርፉን ለመታደግ አቅም ብቃቱም ያላቸው ባለሙያዎች ኢትዮጵያ እንዳሏት ጠቅሰው፣ በኪሳራና በደካማ አፈጻጸማቸው ወደ ግል ይዞታነት የሚዛወሩትን ፋብሪካዎች፣ ባለሀብቶች በገንዘባቸው፣ ባለሙያዎችም በዕውቀትና ልምዳቸው ሕይወት እንዲዘሩባቸው ጠይቀዋል።

የቀድሞዎቹን የእርሻ ባለሙያዎች ‹‹የሸንኮራ ዶክተሮች››፣ ‹‹የሸንኮራ ማሳን የሚያነጋግሩ›› ብለዋቸዋል። መሐንዲሶቹን፣ ‹‹የፋብሪካ የውስጥ ደዌ በድምፅ የሚያውቁ›› በማለት ገልጸዋቸዋል።

እንዲህ ባለው አኳኋን የሚጠቀሱ ባለሙያዎች የነበሩት የስኳር ኢንዱስትሪው፣ ሸንኮራ ግን ደስታ እንጂ ሐዘን እንደማይወድለት በዘዴኛ ገልጸውታል። ይህ አባባላቸው ሠራተኛው እንደ ሥራው ልክ የደመወዝ፣ የጥቅማጥቅምና የቦነስ ጭማሪ እንደማያገኝ ይባስ ብሎ በመዋቅርና አሠራር  ለውጥ ሰበብ በገፍ እየተቀነሰ በመሆኑ የሥራ ዋስትና ማጣቱን፣ ማሳዎችም እየተጎዱ ምርትም እየተበደለ እንደመጣ ገልጸዋል።

እንዲህ ያሉትን ጉዳዮች ያስተናገደው የምክክር መድረክ፣ ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር ተነሳሽነቱን እንደጀመረው በመውሰድ የኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች ማኅበር ዕውን እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነቱን ወስዶ እንዲንቀሳቀስ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል የሦስት ቢሊዮን ብር አክሲዮን ሽያጭ በማከናወን፣ አብዛኛውን እንዳሳካ ያስታወቀው ይኸው ኩባንያ ወንጂ/ሸዋን እንዲሁም መተሐራን ለመግዛት እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ እስከ 60 ሺሕ ባለአክሲዮኖችን እንደሚያሰባስብ ያስታወቀው ኢትዮ ስኳር፣ ከ60 እስከ 63 በመቶ የሸንኮራ አገዳ ማልማት የሚችልበት፣ በሔክታር 160 ቶን በማምረት በዓመት 1.4 ሚሊዮን ቶን የሚፈጭ ሸንኮራ ማዘጋጀትና በዓመት 172 ሺሕ ቶን ስኳር ማምረት የሚችልበት አቅም እንዳለው ማስጠናቱን የኩባንያው ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ እንደ አቶ ለማ ማብራሪያ ከሆነ ግን ምንም እንኳ በአሁን ወቅት በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙት የስኳር ፋብሪካዎች ወደ ግል ተዛውረው ውጤታማ እንደሚሆኑ ቢጠበቅም፣ የውጤታማነት ሒደቱ ግን ከአራት እስከ አምስት ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች