ሰላም! ሰላም! “ካላጣሽው አካል በልቤ ላይ ተሰንቅረሽ፣ ታሰኚኝ ጀመረ ደግሞ ደግሞ እንደ ምን አለሽ?” እያልኩ ሳፏጭ ማንጠግቦሽ አልጣማትም። “እኔ ያለሁት እዚህ አጠገብህ ማን ናት እሷ ተሰንቃሪዋ?” ብላ ፍጥጥ። ጉድ እኮ ነው። ብለን ብለን በ‹ኢማጅኔሽንም› ልንጣላ ነው? ምኑን ቀረው። በስም ስንጣላ፣ በአቀማመጥ ስንጣላ፣ በአረማመድ ስንጣላ ከረምንና ደግሞ አሁን በተውላጠ ስም ጭቅጭቅ። ምንድነው ግን ጉዱ? ‘ፈራሁ የምፀናበት ልብ አጣሁ ነው’ ያለው ያ ባለቅኔ። አይ ሞት ሁሉን አፈር አልባሹ። “ሞት ባይኖር ኖሮ እኮ እንዲህ አንናናቅም ነበር፤” ሲለኝ ነበር ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። “ማን ከማን ሲናናቅ አየህ?” ስለው፣ “ተማሪና አስተማሪ፣ መሪና ተመሪ፣ ፈጣሪና ፍጡር ናቸዋ። አታይም እንዴ ዙሪያህን?” አለኝ። እኔ ደግሞ አንዳንዴ ነካ የሚያደርገኝ ነገር አለ። ዙሪያህን ሲለኝ ቀጥታ ወስጄው ዘወር ስል ማንጠግቦሽ ቆማለች። “ዛሬ ያቺን ስንቅር ሳታወጣ ወደ ቤት እንዳትመጣ፤” ብላ ረግጣን ሄደች። “ምንድነው?” አለኝ የባሻዬ ልጅ ደንግጦ። የሚያስደነግጠን በዛ እኮ!
ነገሩን በጥሞና አስረዳሁት። “የአሞራ ክንፍ ባደለኝ የሚባልበት ዘመን ላይ ደረስን በለኛ። ምነው ማንጠግቦሽ ያውም በሕዝብ ዘፈን እንዲህ የምትሆነው?” ብሎ ሲታዘባት ምንም ወዳጄ ቢሆን ቅር አለኝ። እንግዲህ ይኼው ነው። ሲለን በምናፍርባት ሲለን በምንኮራባት አገራችን ‘ሁለት ሞት ሙቱ’ ብሎ ሲያዝብን እንኳን በዋልንበት ባልጠረጠርነው ነገር ለመኳረፍ ቅፅበት አይፈጅብንም። እናም እኔ የምላችሁ ዝም ብላችሁ ከላይ ከላይ ስታስቡት፣ ይኼ ‹ጥልቅ ተሃድሶና ዘላቂ ልማት› በኩነኔና በፍረጃ የደመቀ የእያንዳንዳችንን ጓዳ ሳያፀዳ እንዲያው ብቻውን ይዘልቅ ይመስላችኋል? አፌ እንዳመጣለት በፉጨቱ ትዳሬ እንደ ቀልድ ብርድ ከገባው፣ የራሴ የሆነ አቋምና እምነት አርቅቄ ያፀደቅኩ ቀን ምን ሊፈጠር ነው? ብላችሁ ማሰብ እኮ ነው። አሁን ይኼ ከአገር ጉዳይ ጋር ምኑ ይገናኛል ባዮች ካላችሁ ‘በእኔ ሕይወት ቀዳዳ ብትገባ አገርህን ታያለህ’ ያለውን ደራሲ ፈልጋችሁ ጠይቁ፡፡ መጠየቅ ነው የሚያዋጣችሁ!!
ይልቅ አሁን ተሃድሶ ምናምን ስል አንድ ነገር ትዝ አለኝ። መቼም እኛ ብዙ ነገር የምናከሽፈው ጠርጥረን ከዚያ በጥርጣሬ ላይ በተመሠረተ ወሬ ነገራ ነገሩን ሁላ በማራከስ ነው። ምስኪኗ አገራችን መቼም በትከሻዋ ስፋቱ ይኼው አለን። እናም መጠርጠር እያለ እርግጠኛ መሆን ብሎ ነገር መዝገበ ቃላታችን ውስጥ ሆነ ተብሎ የተዘለለ ነገር ይመስለኛል። ምነው እኔ ብቻ ሆንኩ? እናንተስ አይመስላችሁም እንዴ? በቃ ፌስቡክ ካልሆነ ‹ኮሜንትና ላይክ› ነውር ሆኖ ቀረ? ይሁና። ይኼም በልዩነት ይመዝገብልኝ። ልዩነት ደግሞ ውበት ነው ብሏል። ማ? የገባቸው። በልዩነት ማመን ከእኔና ከእናንተ ካልጀመረ ከላይ ይመጣል ብሎ መጠበቅ ዘንድሮ አላዋጣም። ለነገሩ በዚህም እርግጠኛ አይደለንም። እርግጠኛ ለመሆን እኮ መመርመር ያስፈልጋል!
አንድ ቀን ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሳይቀር በነፈሰው ነፍሶ በነደደበት ስለሚያነደን ኑሯችን ስንጫወት፣ “እኔ አንዳንዴ ሳስበው እንኳን ስለዕርምጃችን በልተን ስለማደራችን፣ ስለኢኮኖሚ ዕድገታችን ቀርቶ ስለድህነታችንም እርግጠኞች ነን ብዬ አላስብም። ዓይናችን ስለማየቱ፣ ጆሯችን ስለመስማቱ፣ በማሰባችን ከእንስሳት የምንለይ ሰብዓዊ ፍጡራን መሆናችንን ማመን ብሎ ነገርንማ እርሳው፤” አለኝ። ከሁሉ ደሃ ስለመሆናችንም እርግጠኞች አይደለንም አባባሉ አስደንግጦኝ ትንሽ ቆይቶ (የምሁር ነገር ምን ይታወቃል) ‘ድህነታችን በጥናት ይረጋገጥ’ እንዳይለኝ ፈርቼ ዞር አልኩ። ዞር ስል ለስንት አሥርት ዓመታት በኖርኩበት ሠፈር የሚገኝ ፎቶ ቤትን አንዱ ቢጠይቀኝ፣ “ወደ ቀኝ ታጥፈህ መሰለኝ . . . ” ብዬ መመለስ። በዚህ ዓይነት ‘የረገጥከው አፈር የማን ነው?’ ቢለኝ ‘የእኛ መሰለኝ’ ልለው ይሆን? በቁም አፈሩ ይቅለላቸውና እየተባልን ታዲያ ሌላ ምን ይመጣልኛል፡፡ ላምጣውስ ብል የት ይገኛል!
እንዲህ የኖርኩትን ሁሉ በዜሮ የሚያባዛ ግራ መጋባት ሲጠናወተኝ ታዲያ መድኃኒቴን አውቀዋለሁ። እሱም በሥራ መወጠር ነው። መድኃኒት በመፈለግና በማሠራት ያዳከምነው ወኔ ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ ዛሬ እኛን ነበር ማየት። ለነገሩ አድርገነው ቢሆን ዛሬ የያዝነውን ይዘን እንዳለነው ቢሆን፣ የምንለው ዕድሜ ይመርበት ይክፋበት እርግጠኛ መሆን አንችልም። ነገርኳችሁ እኮ? ማጣራት የእኛ ተግባር አይደለም ስላችሁ? እኔን ካላመናችሁ አዛውንቱ ባሻዬ አንድ የሚሉት አባባል አለ። “ላለፈው ዕድሜ ከመቆጨት ለሚመጣው አስብ፤” ይላሉ። ይመስለኛል እኛ ግን የምናስበው ገና ላለፈው ቂም በቀል ማስታወሻነት ስላላቆምናቸው ሐውልቶች ነው። ካልመሰላችሁ ይችም በልዩነት ትያዝልኝ። ይህች የባሻዬ አባባል ከዚህ በፊት የሰማናት ስለመሰለን የራሳቸው ትሁን አትሁን እርግጠኛ መሆን አንችልም’ ካላችሁ ደግሞ እንደ ፈቀደችሁ። የመጠርጠር መብታችሁ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በጎዳናው ተምኔት የተፈቀደ ነው። መረጋገጡን እንኳ እንጃ፡፡ ግን አደራ ባሻዬን በኩረጃ ስማቸውን ስታጠፉ እንዳይሰማና ኢንተርኔቱን በሴራ እንዳታዘጉት። ደግሞ ለመዝጋት ማን ይሰንፋል ብላችሁ ነው!
ለነገሩ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ተዘግቷል። የድግግሞሽ አቆጣጠሬ ቅኔው ካልገባችሁ በቃ ይኼን ፋይል ቶሎ ዝጉት። ደግሞ በኋላ . . . ሆ የምሬን ነው! እና ባሻዬ ፍራሽ ማደስ በእሳቸው አልተጀመረም። ስንቱ ብርሁነቱን ንቆ፣ ትኩስ ኃይሉን በመምሰልና በማስመስል አምክኖ በሰው ወርቅ እየደመቀ እያየን፣ አንድ የአገር አንጡራ ሀብት አረጋዊ ያለችውን ቢያሽሞነሙንና ቢያቀርብ ነውር አይመስለኝም። አያችሁ ሰው መጠየቅ ያለበት ባለው አቅምና እውቀት ልክ መሆን አለበት። ምን ደላላ ብሆን አልተሳሳትኩም መቼም። “ጥሬ እፈጭ ብለሽ ዱቄት አታፍሺ፣ ታዋቂ እሆን ብለሽ ታላቅ አታርክሺ . . .” ሲባል የሰማሁበት ጊዜ ለምን እንደሆነ እንጃ ሩቅ ይመስለኛል። እናንተ ሰዓቱ ነው ትውስታችን ነው እየፈጠነ ያስቸገረን? በ40 ሳንጨማደድ እንደ ባለ 80 ምርኩዝ ማለት አበዛንና እኮ! መቼም ምርኩዝ ለያዘ 40/60 ቅድሚያ ይታደላል ብለን አይመስለኝም። ነገሩን ማለቴ ነው እንጂ የቤቱ ጉዳይ አንጀታችንን ይበላዋል!
ሥራና ነገር እየተምታታብኝ ጊዜውን እንዴት እንደምዘልቀው ጨንቆኛል። እስኪ ወደ አሻሻጥኩት ከባድ መኪና ገጠመኝ ልውሰዳችሁ ደግሞ። ገጠመኝ ላውሳችሁ ይባላል እንጂ ወደ ገጠመኝ ልውሰዳችሁ አይባልም ስትሉ ሰማሁ መሰለኝ። ይኼ ጭቅጭቅ መሆን ያለበት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር መሰለኝ። እሱ ውኃ ወቀጣ ነው ካላችሁ ምንም ችግር የለም፣ ከእኔ ጋር መቀንጠስ ነው። መቼም በድለላ ሥራ ጥርስ ስትነቅሉ ትልቁ ወሮታችሁ በከባድ ሚዝን ከሚጫወቱ የኑሮ ተፋላሚዎች ጋር መዋል ነው። ከቀላል ሚዛኑ ጋር ጥርስ ሳታበቅሉም ትውላላችሁ። ታዲያ አንድ የጭነት መኪና የሚገዛ ደንበኛዬ፣ መኪናውን ቶሎ አስፈትሾ ቀልቡን ሰብስቦ ሊዋዋልልኝ አልቻለም። በቅርብ ሠርቶ ስላጠናቀቀው ቤት በየአቅጣጫው እየተደወለለት ያወራል። በቅርቡ ፎርብስ መጽሔት ላይ ልማቱ ያፈራው ቢሊየነር የመባል ዕቅዱን ይነዛል። ደግሞ ወሬ ለመንዛት!
ደንበኛዬ በመርከብ አስጭኖ ከአውሮፓና ከቻይና ስለሚያስመጣቸው የቤት ዕቃዎች ይቀዳል። በዕቃ ግዥ ለሚያግዙትና ከዚያው ሆነው ለሚያማክሩት ሰዎች በስልክ ሲመልስ፣ አንድም ርካሽ ዕቃ እንደማይፈልግ “የሰው መሳቂያ አታድርጉኝ” በሚል መኩራራት ይጋበዛል። “ያዝኩ ሲሉ መያዝ፣ አለሁ ሲሉ መቅረትን በሰው እንኳ አይቶ አልተማረም እንዴ ይኼ ሰው?” ብሎ የሚሸጠው መኪና ባለቤት ቢታዘበው ጓደኛው ጣልቃ ገብቶ፣ “ምን ይደረግ ገንዘብ እውቀትን የትና የት መርቶት እያየህ ለምን በእሱ ትፈርዳለህ?” ይለዋል። መልሶ ደግሞ በከፊል ወደ እኔ ዘወር ብሎ፣ “እንደ እኛ ያለውን ደካማ ደግሞ መኖሪያ ቤት መንግሥታችን በዕጣ ሊያንበሸብሽ ሲገባው እያዘገመ ነው። ከሁሉ የገረመኝ ግን የዘንድሮ ጉንጭ አልፋ ዲስኩር በቤት ዕደላና በሌሎች የልማት ሥራዎች በማሳበብ መታጠፉ ነው፤” አለኝ። ይኼኔ ጓደኛው ተቀብሎ፣ “ታዲያ በአንዲት መርፌ ላይ ስንት ሺሕ መላዕክት መቆም ይችላሉ?’ ከሚል ውኃ የማይቋጥር ክርክር ለእኛስ ቢሆን ይኼ አይሻለንም?” አለውና ፈገግ አለ። እየበሉ ማልቀስን እንዴት እንደተካንንበት ታያላችሁ? ምን ምርጫ አለ እንዳንል አምስተኛው ዓመት ሊጠናቀቅ ወራት ቀርቶ ይታዘበናል ብለን ዝም። ዝምታን እያነገሥን መሰለኝ ራሳችንን የአደፍራሾች መቀለጃ ያደረግነው!
በሉ እስኪ እንሰነባበት። ኮሚሽኔን ዘግቼ ሳበቃ ውኃ ጥም ሊገድለኝ ደረሰ። የባሻዬን ልጅ ደወልኩለትና የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ቀጠርኩት። ስንገናኝ ግሮሰሪዋን ከወትሮዋ በተለየ የዋጋ ጭማሪ አድርጋ ታዳሚዎቿን ታስተናግዳለች። የግሮሰሪያችን ባለቤት፣ መቼም ይኼ ሕዝብ በሃይማኖቱና በሚስቱ ነው የሚገኘው ብሎ ከመጽሐፈ መክበብ ያገኘው መሆኑን በትልቁ ጠቅሶ፣ “ራሱን የማይወድ ሌላውን አይወድም” የሚል ጥቅስ ለጥፏል። ለዚህም የተጋነነ ጭማሪ ስላደረገ በዝምታ የሚታለፍ መስሎታል። ገና አንድ መለኪያ ሳይቀምስ የዋጋ ጭማሪው ያሰከረው የዘወትር ደንበኛው ጥጉን ይዞ፣ “የት ሄደን እንብላ?’ ስንል ዝም የተባልነው አንሶ ‘የት ሄደን እንጠጣ’ በሚልም ከመንግሥት ጋር ልታቀያይመን ነው? ተው የቄሳርን ለቄሳር የእኛን ለእኛ!” ይለዋል። ሌላው ደግሞ፣ ‹‹የኤክሳይዝ ታክስ ሕጉ ሳይፀድቅ ዋጋ የጨመርከው ለፅድቅ ነው ለኩነኔ?›› ሲለው፣ አንገቱን ደፍቶ የሰው ዓይን ሸሸ፡፡ ምናለበት ዓይናቸውን የሚያጉረጠርጡብን እንዲህ አንገታቸውን ቢደፉ ያሰኛል!
“አወይ ዘመን! አወይ መጨካከን! ላያችን ላይ የትርፍ ክብድት እያነሱብን ገላጋይ አጥተን እኮ ክብደት የለሾችን ሆንን ጎበዝ! ሲያዩን አንከብድ ሲቆጥሩን አንሞላ፤” ይላል ሌላው። ገና ከአሁኑ በዚህ ሁኔታ እንደለመደው ተመላልሶ እየጠጣ ፀንቶ ኑሮውን የመርሳቱ ዓላማው አደጋ ላይ እንደወደቀ የተረዳው ደግሞ፣ “እሱ ምን ያድርግ? እስከ ዛሬ የተጎዳው አይበቃም? ስንት ጓደኞቹ ሕንፃ እየሠሩ በጥቅም ተቧድነው የዘረፋ ማኅበር ሲመሠርቱ፣ እሱ እስከ ዕለተ ሞቱ ግሮሰሪ ላይ መቅረት አለበት?” ይላል። ከዚህ ሁሉ በላይ በቅዱስ መጽሐፍ ጥቅስ ይገኛሉ ተብለን፣ ዝም ይላሉ ተብለን እንደ ሞኝ መታሰባችን ያንገበገበው፣ “ራሱን ቢወድ ነዋ ክርስቶስ እስከ መስቀል ሲጓዝ አንገቱን የደፋው? የምድር ሕግ አደረግከው የፈጣሪን ቃል እንዳሻህ ለራስህ መጠቀሚያ እያደረግክ የምትለጥፈው? አንሳ ወዲያ!” ሲል አምባጓሮ ያስነሳል። እኔና የባሻዬ ልጅ፣ መለኪያችንን እያጋባን በተመስጦ ውስጥ እንዳለን አንዱ፣ ‹‹ወገኖቼ ሆይ በምድር ላይ ስንኖር ለሥጋችንም ሆነ ለነፍሳችን እኩል ማሰብ ይኖርብናል፡፡ በዚህ መሠረት አንዳችን ለሌላችን ፍቅር መስጠት አለብን፡፡ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠርን ሰዎች ነንና እንደ ፈጣሪ ልጆች እንተሳሰብ፡፡ አንዳችን ስንጎዳ ሌላውን ይመመው፡፡ ሌላው ሲደሰት ሌላኛው አይክፋው፡፡ ልባችንን ከፍተን እንተሳሰብ፡፡ ከተሳሰብን ትንሹ ነገር ይትረፈረፋል፤›› ሲለን ‹ቃለ ሕይወት ያሰማልን› ብለን በሙሉ ልብ ተቀበልነው፡፡ አዎ! እኛ ከተሳሰብን በቂ አይደል? አጉል ከመራገጥ ማረጋገጥ ማለትም ይኼ አይደል! መልካም ሰንበት!