Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊኢትዮ ቴሌኮም ሆን ተብሎ በሚፈጸሙ የኬብል ስርቆቶች የ100 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንደደረሰበት...

ኢትዮ ቴሌኮም ሆን ተብሎ በሚፈጸሙ የኬብል ስርቆቶች የ100 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንደደረሰበት አስታወቀ

ቀን:

ስምንት የጥበቃ ሠራተኞቹ በኬብል ዘራፊዎች እንደተገደሉበት ገልጿል

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ በመጡ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ውድመት በተለይም ኬብሎችን ሆን ብሎ በመቁረጥ የሚፈጸሙ ስርቆቶች እንዳስመረሩት ያስታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 100 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው 547 ጉዳቶች እንደተፈጸሙበት አስታወቀ፡፡ አጥፊዎች ተገቢውን የፍትሕ ቅጣት እንደማያገኙ ገልጿል፡፡

ባለፈው ዓመት ከ300 ያላነሱ የቴሌኮም ኬብሎች ጉዳት እንደደረሰበት፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ሐሙስ ታኅሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደ የመሠረተ ልማት የምክክር መድረክ ላይ ይፋ አድርገዋል፡፡ እየተስፋፋ የመጣው ጉዳት ከሚያስከትለው የቴሌኮም አገልግሎት መስተጓጎል ባሻገር፣ በሠራተኞች ላይ ሳይቀር ድብደባና ግድያ ማስተከል መጀመሩ ኩባንያው ከሚችለው በላይ እንደሆነበት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል፡፡

- Advertisement -

ሆን ተብሎ የሚፈጸመውን የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ስርቆትና ጥፋት ለመከላከል የሞከሩ ስምንት የኢትዮ ቴሌኮም የጥበቃ አባላት መገደላቸውን ያስታወቁት ወ/ት ፍሬሕወይት፣ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ከባድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡ፣ የሕግ አካላትና ሌሎችም የሚመለከታቸው ሁሉ በአገር ሀብትና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ትኩረት እንዲሰጡት ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የተለመደውና በቴሌኮም መስመሮች ላይ ይደርስ የነበረው ጥፋት በአብዛኛው የኮፐር ኬብሎችን ቆርጦ ለመሸጥ ይደረግ የነበረው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ከተቆረጠ በኋላ ምንም ዋጋ የማይኖረውን የፋይበር ኬብል የመቁረጥና ጉዳት የማድረስ ተግባር እየተስፋፋ መምጣቱን፣ የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊዎችና የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች እንደገለጹትም፣ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ውድመት እየተፈጸመ ነው፡፡ ለዚህ አባባላቸው ማሳያ የሚያደርጉትም በመንግሥት ላይ ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደርና መንግሥትን ለማማረር በሚያስመስል ሁኔታ ሆን ተብሎ ኬብሎች እየተቆራረጡ እዚያው ተጥለው እንደሚገኙ በመግለጽ ነው፡፡

የፖሊስ ባልደረቦች የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኞች ስለመሆናቸው የሚገልጽ መታወቂያ የያዙ ግለሰቦች ሳይቀሩ መስመር የሚጠግኑ በመምሰል ጉዳት ሲያደርሱ እንደሚታዩ፣ ተቋሙም ራሱን እንዲፈትሽ ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር እየተስፋፋ ለመጣው እንዲህ ያለው ጥፋት ሕጉ ከፍተኛ የወንጀል ቅጣት ቢያስቀምጥም፣ በፍርድ ቤት የሚተላለፉ ውሳኔዎች ግን በዚህ ዓይነቱ ወንጀል ተከሰው የሚቀርቡ ግለሰቦችን በዋስትና ከመልቀቅ ባሻገር በቅጣት ማቅለያ ጭምር በዝቅተኛ የእስራት ቅጣት ውሳኔ ስለሚያሰናብቱ፣ በርካታ ጥፋተኞች ተመልሰው በቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ጥፋት ላይ ሲሳተፉ እንደሚታዩ የኢትዮ ቴሌኮም የስትራቴጂክ ዘርፍ የኦፕሬሽን ኃላፊ አቶ ሰሎሞን መኮንን ገልጸዋል፡፡

በቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ላይ ዘንድሮ ከደረሱ አደጋዎች መካከል 52 በመቶ ሆን ተብለው በግለሰቦች የተፈጸሙት ሲሆኑ፣ በፀጥታ ችግሮች 18 በመቶ፣ በተፈጥሮ አደጋዎች 12 በመቶ፣ እንዲሁም በግንባታ ወቅት በቸልተኝነት 14 በመቶ ጉዳቶች መከሰታቸውን አቶ ሰሎሞን አስታውቀው፣ ሆን ተብለው የሚፈጸሙ ጉዳቶች እየተባባሱ መምጣታቸው ግን የሁሉንም አካል ርብርብ እንደሚጠይቁ አሳስበዋል፡፡ በጠቅላላው 91 በመቶ የሚሸፍኑ ጉዳቶች ሆን ተብለው በሚፈጸሙ የስርቆት ተግባራትና በግንባታ ወቅት በቅንጅት ዕጦት በሚፈጸሙ የግዴለሽ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በተሽከርካሪዎች በሚደርሱ አደጋዎች የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው ብለዋል፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ የደረሱት ጉዳቶች ያስከተሉት የ100 ሚሊዮን ብር ኪሳራ፣ 25 የሞባይል ጣቢያዎችን ለማስገባት፣ እንዲሁም ከ56 ሺሕ በላይ አዳዲስ ተጠቃሚዎችን ለማዳረስ ያስችል እንደነበር አቶ ሰሎሞን አብራርተዋል፡፡       

የቴሌኮም መሠረተ ልማቶችን ለማስጠበቅ የወጡ ሕጎች ሆን ተብሎ በሚፈጸም ተግባር የሚደርስ ጉዳትን በወንጀል ድርጊት ከአምስት እስከ 20 ዓመታት በሚደርስ እስራት የሚያስቀጡ ሲሆን፣ በቸልተኝነት የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችም ከስድስት ወራት እስከ አምስት ዓመታት በሚደርስ እስራት ያስቀጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ቅጣት ስለማይተገበር ጉዳቶቹ እየተበራከቱ መምጣታቸውን የገለጹት ኃላፊዎቹ፣ የአገሪቱ ሀብትና ንብረት በዚህ ደረጃ እየወደመ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ እያንዳንዱ ዜጋም ሆነ የመንግሥት አካላት ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ያሰባሰበው ኢትዮ ቴሌኮም፣ የ2012 በጀት ዓመት ገቢውን ወደ 45 ቢሊዮን ብር ለማድረስ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ባለፈው ዓመት የ36.3 ቢሊዮን ብር ገቢ በማስመዝገብ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ በዚህ ገቢ ላይ ዘንድሮ የ25 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ፣ ካለፈው ዓመት አኳያ ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ ለማግኘት ማቀደኑንና እስካሁንም እየተሳካለት እንደሚገኝ ወ/ት ፍሬሕይወት አስታውቀዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...