የበርካታ ስፖርቶች መሠረት መሆኗ የሚነገርላት አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በክልል ከተሞች ብልጫ ሲወሰድባት መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡ ለዚህ በማሳያነት በእግር ኳሱ እየተወሰደባት ያለውን ብልጫ መመልከት በቂ ይሆናል፡፡ በፕሪሚየር ሊግ ብቻ ከስድስትና ሰባት ክለብ በላይ የነበራት አዲስ አበባ አሁን ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ብቻ ተወክላ ትገኛለች፡፡
የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ለዚህ ችግር መፍትሔ እንዲሆን የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ላይ ለመሥራት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽን ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ በ2012 የውድድር ዓመት በከተማዋ ከሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ 2,680 ታዳጊዎች በ122 የሥልጠና ጣቢያዎች ዘመናዊና ሳይንሳዊ ሥልጠና እንዲያገኙ ቅድመ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ይገኛል፡፡
ኮሚሽኑ ለዚህ ይረዳው ዘንድ በከተማ አስተዳደሩ ሥር የሚገኙ ሁሉም ፌዴሬሽኖች ከእግር ኳስ በስተቀር ዓመታዊ ጉባዔያቸውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን እንደየስፖርቱ ባህሪ ዕውቀቱና ብቃቱ ያላቸው አዳዲስ አመራሮች ምርጫ እንዲያከናውኑ መመሪያ ማስተላለፉ ታውቋል፡፡
ምርጫ ካደረጉ ፌዴሬሽኖች አትሌቲክስና ወርልድ ቴኳንዶ ጨምሮ የተሻለ ውጤት እያስመዘገቡ ካሉት መካከል የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ይጠቀሳል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳትነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ረዘነ በየነ በድጋሚ በነበሩበት ኃላፊነት እንዲቀጥሉ በሙሉ ድምፅ መመረጣቸውን ጭምር በስፖርት ኮሚሽኑ ድረ ገጽ የተለቀቀው መረጃ ያመለክታል፡፡