የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ የመጣባቸው በርካታ ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች የሚታዩበት ተቋም መሆኑ ይወሳል፡፡ የስፖርት ማዘውተሪያ ዕጦትና መጣበብ ያስከተለው ተፅፅኖ በአንድ በኩል፣ የሥልጠናና የልምምድ መሰል ተጓዳኝ አቅርቦት በሌላ በኩል የሚፈታተኑት ይህ ዘርፍ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የአየር ብክለት ችግሮችም ፈተና ሲገጥመው ይታያል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ አምስት በአንደኛ ዲቪዚዮን የሚወዳደሩ ክለቦች መከላከያ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ፌዴራል ማረሚያና ፌዴራል ፖሊስ ሲሆኑ፣ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ደግሞ 19 ክለቦች ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁንና የከተማ አስተዳደሩ ለዓመታዊ ፈቃድ ዕድሳት በሚል የመመዝገቢያ ክፍያ ከማስከፈል ባለፈ በራሱ በጀት በጅቶ የሚያስተዳድራቸው አለመሆናቸው ይታወቃል፡፡
ፋይናንስን በሚመለከት ከመንግሥት ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደማይደረግለት የሚታወቀው የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ታኅሣሥ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላለፉት አራት ዓመታት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አመራሮችን በማሰናበት አዲስ የሥራ አመራር ቦርድ ምርጫ አድርጓል፡፡ ተቋሙን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት “ማርሽ ቀያሪው” በሚለው መጠሪያ የሚታወቀው ታላቁ አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ልጅ አቶ ቢኒያም ምሩፅ መሆናቸው ሲታወቅ፣ ፌዴሬሽኑ ዘመኑን የሚመጥን አደረጃጀት ይኖረው ዘንድ በከተማ አስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽን ድጋፍና ይሁንታ የማሻሻያ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡
አትሌቲክሱን ጨምሮ በሁሉም ስፖርቶች “ውድድር ተኮር” ከነበረው አሠራር “ሥልጠና ተኮር” ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው የሚናሩት አቶ ቢኒያም፣ በሒደት አዲስ አበባ ከተማን የሚወክል ክለብ የማቋቋም ዕቅድ አላቸው፡፡ በፌዴሬሽኑ ከተጀመረው የሪፎርም ሥራ ጎን ለጎን በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ ወረዳዎች በተመረጡ ስድስት ክፍለ ከተሞች ላይ ዕድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች የታዳጊዎች ፕሮጀክት ሥልጠና ለመጀመር ክህሎቱና ብቃቱ ያላቸው ሙያተኞች የተካተቱበት አንድ ኮሚቴ ስለመቋቋሙ የሚናገሩት አቶ ቢኒያም፣ በተጨማሪነት በየካ ክፍለ ከተማ በወንድራድ ትምህርት ቤትና ካራሎ ሁለት ጣቢያዎች ላይ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የታዳጊዎች ፕሮጀክት ይቋቋማል፡፡
ለፕሮጀክቱ የተመረጡት ስድስቱ ክፍለ ከተሞች የካ፣ ቦሌ፣ አራዳ፣ ኮልፌና ጉለሌ ሲሆኑ ከፋይናንስና መሰል የቁሳቁስ አቅርቦትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የትጥቅ ድጋፍ የሚደረግለት ሲሆን፣ አዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ደግሞ የአሠልጣኞችንና ሙያተኞችን ወርኃዊ ክፍያ እንዲከፍል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ፌዴሬሽኑ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን በሚደረግለት ተጨማሪ ድጋፍ ጃንሜዳ ላይ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሥልጠና ማዕከል ለመክፈት ዕቅድ እንዳለውም አቶ ቢኒያም አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በሁሉም የስፖርት ተቋማት በምርጫ ወቅት እነዚህን የመሰሉና ሌሎችም የተለመዱ ዕቅዶች የማስፈጸም አቅም ውስንነት የሚመጣው ተመራጮች ኃላፊነት ከተቀበሉ በኋላ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በመነሳት የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዕቅዶቹን ወደ መሬት በማውረዱ ረገድ ምን ያህል ይሳካለት ይሆን? ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ አቶ ቢኒያም፣ “ሌላው ቢቀር አትሌቲክስና አባቴ [ምሩፅ ይፍጠር] ያላቸውን ቁርኝት አውቃለሁ፣ አቅሜ በፈቀደ መጠን ዕውን ማድረግ የምፈልገውና የምመኘው እንደማደርገውም ቃል የምገባው ያንን ታሪክ የሚደግሙ ታዳጊዎች የሚፈሩበት ሥርዓት ማመቻቸት ነው፤” በማለት ያላቸውን ቁርጠኝነት ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ አትሌቲክስ በአመራርነትም ሆነ በሙያተኝነት ከዚያም ሲያልፍ ግልፅ ባልሆነ የአሠራር ሥርዓት “ኔትዎርክ” በሚመስል መልኩ ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው የሚታወቁ ግለሰቦች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ማሳያ ሊሆን የሚችለው ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን የበላይ አመራርነት አትሌቲክሱን ጨምሮ በሁሉም ስፖርቶች እየተከናወነ ያለውን የሪፎርም እንቅስቃሴ ተከትሎ ከሚደመጡ ተግዳሮቶች መካከል ለስፖርቱ የገቢ ምንጭ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ተቋማቱ “ስፖንሰር” እንዳያደርጉ ማድረግ የሚለው አንዱና ዋነኛው መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ አትሌቲክስን ጨምሮ ሁሉም የስፖርት ተቋማት ግለሰብ ሳይሆኑ የመንግሥትና የኅብረተሰቡ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ቢኒያም፣ “እንደእኔ ስፖንሰር አድራጊ ተቋማት ይህ ይጠፋቸዋል የሚል እምነት የለኝም፣ ይህን አስበው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ይኖራሉ የሚል እምነት ባይኖረኝም ካሉ ግን ከድርጊታቸው ተቆጥበው፣ እንዲያውም በዘርፉ ያካበቱትን ተሞክሮ ለአዳዲሶቹ በማሳወቅ ረገድ ሊጫወቱት የሚገባው ትልቅ ሥራና ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ነው፤” ብለዋል፡፡
ሌላው በአዲስ አበባ እየተስፋፋ የመጣው የአየር ብክለት ለአትሌቶች ብቻም ሳይሆን፣ ለመላው የከተማዋ ነዋሪዎች ሥጋት መሆኑ ሳይንሳዊ መረጃዎች ማመላከት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ከፍተኛ የተሸከርካሪዎች ጭስ፣ የፋብሪካ ብናኞች፣ ከፋብሪካና ከየቤቱ የሚወጡ ጭሳጭሶች ብሎም በየመንገዱ የሚቃጠል ቆሻሻ ተደማምሮ ለመተንፈሻ አካላት በሽታ የማጋለጥ ዕድሉ እየጨመረ መምጣቱ መረጃዎቹ ያሳያሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በከተማዋ የተተከሉ የአየር ብክለት መለኪያ መሣሪያዎች ለዚህ ችግር ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር ለከተማው አትሌቲክስ ዘርፍ ተጨማሪ ሥጋት ሆኖ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ እንደዚህ ያሉ የውስጥና ውጫዊ ችግሮች ቢከቡትም፣ የከተማው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዲስ ጅምሮችን በመሰነቅ ዘርፉን ለመታደግ እንዳሰበ አዲሱ አመራር አቅዷል፡፡
ይህንኑ በሚመለከት አቶ ቢኒያም፣ “ችግሩ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ብቻውን የሚፈታው ሳይሆን አገር አቀፍ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ የበኩሉን ድርሻና ኃላፊነት ለመወጣት ከኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች ጋር በጋራ ለመንቀሳቅስ ዕቅድ ይዟል፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው ብዙዎቹ በአዲስ አበባ የሚኖሩ አትሌቶች ልምምድ የሚያደርጉት በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎች ማለትም እንጦጦና ሱልልታ ላይ ነው፡፡ ለዚህም ነው በጉዳዩ ከኦሮሚያ አትሌቲክስ ጋር በጋራ ለመሥራት ዕቅድ የያዝነው፤” በማለት የችግሩን አሳሳቢነት እንደሚጋሩ አስረድተዋል፡፡