Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክችላ የተባለው የመረጃ አጠባበቅ ሕግ ነገር

ችላ የተባለው የመረጃ አጠባበቅ ሕግ ነገር

ቀን:

በውብሸት ሙላት

በግላዊነት ላይ የተደቀኑ ዘመን አመጣሽ ተግዳሮቶችን ለመዳሰስ መንደርደሪያ የሚሆን ባለፈው ሳምንት በዚሁ ዐምድ ቀርቧል፡፡ ዋና ማጠንጠኛውም የግላዊነት መብት ታሪኩንም ይዘቱንም ለከቱንም ማሳየት ነው፡፡ ይህ ጽሑፍም የዚያ ክትያ ነው፡፡ ክትያ ይሁን እንጂ ራሱንም የቻለ ስለሆነ በዚያኛው ላይ የተንጠለጠለ አይደለም፡፡ የዚህኛው ትኩረቶች ሁለት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው መንግሥት መረጃ ስለሚወስድበት (የግላዊነት መብት ገደቦች) ሲሆን፣ ሁለተኛው የግለሰቦች መረጃ አጠባበቅ ሕግን ይመለከታሉ፡፡

የግላዊነት መብት ገደቦች

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ግላዊነት የሰብዓዊ መብት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱም ዕውቅናና ጥበቃ ተሰጥቶታል፡፡ የአንድ ሰው የግላዊነት መብት ሊገደብ (ጣልቃ ሊገባበት) የሚችለው ሦስት ጥምር ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 26 (3) ተወስኗል፡፡

ግላዊነትን መገደብ አስገዳጅ ሁኔታ ሲፈጠር (ግላዊነት ሳይገደብ ሊፈጸሙ የማይችሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ)፣ እነዚህ አስገዳጅ ሁኔታ ሲኖሩ ግላዊነት ሊገደብ እንደሚችል ቀድሞ በሕግ (ለምሳሌ በአዋጅ) ከተገለጸ፣ እንዲሁም የሕጉ ዓላማ ተገቢነት (ተቀባይነት) ያላቸውን ግቦች (ለምሳሌ ወንጀል ለመከላከል፣ ብሔራዊ ደኅንነትንና የሕዝብ ሰላምን ለማስጠበቅ ወዘተ) ለማሳካት ሲባል ብቻ ነው፡፡ በአጭር ለመግለጽ አስገዳጅ ሁኔታ፣ ሕግና ተገቢ ግቦች የሚሉት ናቸው፡፡

ፓርላማው ግላዊነትን የመገደብ አዝማሚያ ያላቸውን አዋጆች በሚያወጣበት ጊዜ አስቀድሞ ሕጉ ሊያሳካቸው ያሰበው ግቦች ተገቢነትና ተቀባይነት፣ እንዲሁም ግላዊነት ሳይገደብ ሊሳካ ስላለመቻሉ ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕግ መኖሩ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ በዚህ መንገድ ካልሆነ በቀር ግላዊነት የማይደፈር መብት ነው፡፡

. በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ

ከስድሳ ዓመታት በፊት የወጣውና አሁንም ፀንቶ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ግላዊነት ተገድቦ ሰውነትና ንብረት (ቤትን ጨምሮ) ፍተሻ የሚደረግባቸውን አጋጣሚዎች ወስኗል፡፡ እንደ ነገሩ ሁኔታ በፍርድ ቤት የፍተሻና የብርበራ ትዕዛዝ በመያዝም ይሁን ሳይያዝም መቼ እንደሚከናወን በዝርዝር ተገልጿል፡፡ በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 32 (1) እንደተቀመጠው ፖሊስ አንድ ሰው “በተከሰሰበት ወይም ወንጀል ሠርቷል ተብሎ በተጠረጠረበት ነገር ማስረጃ የሚሆን ማስረጃ የሚሆን በሰውነቱ ደብቋል የሚያሰኝ በቂ ምክንያት ከሌለ የተያዘውን ሰው መበርበር  አይቻለውም፡፡”

በዚሁ አንቀጽ እንደተገለጸው ሰውነት የሚበረበረው በተመሳሳይ ፆታ ባለው ሰው ሆኖ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢያዝ አልበለዚያም እጅ ከፍንጅ የተያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ የቤትም ፍተሻ እንዲሁ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለበለዚያም ተጠርጣሪውን እጅ ከፍንጅ ለመያዝ ክትትል በሚደረግበት ጊዜም ሊሆን ይችላል፡፡

እጅ ከፍንጅና እንደ እጅ ከፍንጅ ከሚቆጠሩ የወንጀል ድርጊቶች ውጪ ለመያዝም፣ እንዲሁም ከያዙ በኋላ ለመፈተሽ በሰውነቱ ማስረጃ የሚሆን ወይም ጉዳት ማድረሻ መያዙን በበቂ ምክንያት የሚያሳምን ሁኔታ ሳይኖር መፈተሽ እንደማይቻል ከልክሏል፡፡ በበቂ ምክንያት መኖር ወይም አለመኖሩን የሚወስነው ተጠርጣሪውን የሚይዘው የፖሊስ መኮንን ነው፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ፣ ግላዊነት የሚገደበው በዚህ መልኩ ነው፡፡

. በሌሎች ናሙና አዋጆች

በሳይበሩ ዓለምና ከአኃዛዊ መረጃ አኳያ ለግላዊነት መብት ጥበቃ የማድረግ አስፈላጊነትንና አንዳንድ መርሆችን ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገሮች ተሞክሮ አንፃር ጥቂት ነጥቦችን ለመጠቋቆም ተሞክሯል፡፡ ከዚህ በመቀጠል በኤሌክትሮኒክ የመረጃ ልውውጦች፣ በስልክ፣ በቴሌግራምና በመሳሰሉት የመገናኛ ዘዴዎች የግላዊነት መብትን መንግሥት የሚገድብባቸውን ወይም የሚተላለፍባቸውን የተወሰኑ አዋጆችን በምሳሌነት በአጭር በአጭሩ እንጠቅሳለን፡፡ ከዚያም ሕገ መንግሥታዊነታቸውን እናጠይቃለን፡፡ 

የፀረ ሙስና አዋጁ

በፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ አዋጅ (ቁጥር 434/1997)፣ በአንቀጽ 46 እንደሠፈረው ለሙስና ወንጀል ምርመራ አስፈላጊ ከሆነ የተጠርጣሪው የስልክና ማናቸውም ዓይነት የኤሌክትሮኒክስ ግንኙነቶችን አግባብ ባለው የበላይ አካል (ፍርድ ቤት አይደለም) ትዕዛዝ አማካይነት መጥለፍ ተፈቅዷል፡፡ በጠለፋ የተገኙት ማስረጃዎችም እንደሌሎች ማስረጃዎች ሁሉ ተገቢነትና ተቀባይነት እንደሚኖራቸው ይኼው አዋጅ ይገልጻል፡፡

በዚህ መንገድ የግለሰቦችን ግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ መጥለፍና ግላዊነት ክልል ውስጥ በአስፈጻሚው አካል ሹመኛ ትዕዛዝ ወይም ፈቃድ ብቻ ዘው ብሎ መግባት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 26 ንዑስ ቁጥር 3 የተዘረዘሩትን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላቱ አጠያያቂ ነው፡፡

በአንድ በኩል መጥለፍ አስገዳጅ ነው ወይ? በሌላ አገላለጽ ሳይጠልፉ መረጃ ማግኘት የሚቻል ከሆነ መጥለፍ ይቻላል ወይ? አዋጁ በሙስና ወንጀል የተጠረጠረን ሰው ሁሉ ያለምንም ተጨማሪ መሥፈርት የመረጃ ልውውጡን (ግንኙነቱን) መጥለፍ እንደሚቻል እንጂ ሳይጠልፉ ማስረጃ ማግኘት የማይቻል በሚሆንበት ጊዜ የሚል የለውም፡፡

በቴሌኮም የማጭበርበር ወንጀል አዋጅ

የቴሌኮም የማጭበርበር ወንጀል አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 761/2004) መሠረት ፖሊስ ወንጀል እንደተፈጸመ ወይም እንደሚፈጸም ካወቀ በድብቅ ብርበራ ለማድረግ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመቀበል መበርበር ይችላል፡፡ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል ምን ምንን እንደሚይዝ በግልጽ በማይቀመጥም ሕጋዊ ያልሆነ አገልግሎት መስጠትም አገልግሎት እንዲቋረጥ ማድረግም፣ የቴሌኮም ዕቃዎችም ጋር የተገናኙ ክልከላዎችን መተላለፍ፣ ለሕገወጥ ዓላማ መጠቀምም ዋጋ ማጭበርበርንም ያካትታል፡፡

በአጭሩ ከቴሌኮም ጋር የተገናኙ ወንጀሎችን ስለሚያጠቃልል ፖሊስ በድብቅ ብርበራና ፍተሻ ለማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይኼም ቢሆን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 26 ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ የሠፈረውን ቅድመ ሁኔታ (ለምሳሌ አስገዳጅ ሁኔታ ሲፈጠር የሚለውን) ማሟላቱ አጠያያቂ ነው፡፡ በሌላ መንገድ ማግኘት እየተቻለም ቢሆን ወንጀሉ የቴሌኮም ማጭበርበር ስለሆነ ብቻ በድብቅ (በሥውር) መበርበርን ልቅ አድርጎ መፍቀድ ሕገ መንግሥታዊነት አጥር ነው ማለት ያስደፍራል፡፡

በኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ

በዚህ አዋጅ (ቁጥር 958/2008) የተዘረዘሩ የኮምፒውተር ወንጀሎች ከተፈጸሙ ወይም ሊፈጸሙ ከሆነ ምርመራው በዓቃቤ ሕግ መሪነት በፖሊስ ይከናወናል፡፡ ምርመራዎቹ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማውጣት የሚከናወኑ ሲሆን፣ አስቸኳይና በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸም ወንጀል በሆነ ጊዜ ፖሊስ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ፈቃድ በማግኘት ምርመራ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉም በ48 ሰዓታት ውስጥ ለከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ማቅረብና የብርበራ ትዕዛዝ ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ አንቀጽ 25 ውስጥ ተዘርዝሯል፡፡

በዚህ አዋጅ መሠረትም በልዩ ሁኔታዎች ግላዊ መረጃዎች የሚወሰዱበት፣ ከላይ ከቀረቡት በተሻለ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያስፈልጋል፡፡ ያ ባይሆን እንኳን ወንጀሎች የሚፈጸምባቸውን (ቁልፍ መሠረተ ልማት) በመለየትና አስቸኳይ ከሆነ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ፈቃድ ለዚያውም በ48 ሰዓት ለከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት የማቅረብ ግዴታን ጥሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ካልሰጠ የተገኙት መረጃዎች በማስረጃነት እንዳይቀርቡ አዋጁ ደንግጓል፡፡ 

ከላይ በናሙና መልክ በመውሰድ ያየናቸው ግላዊነት ላይ ገደብ የሚደረግበትን፣ መረጃም የሚወሰድበትን ሁኔታ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል መረጃ የሚጠበቅበትን እንቃኛለን፡፡ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጁን እናስቀድም፡፡

የግል መረጃ ጥበቃ በመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ጥበቃ አወጁ

ስለግለሰብ መረጃ (Personal Information) በተሻለ መልኩ ጥበቃ የተሰጠው በመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አወጁ (አዋጅ ቁጥር 590/2000) ነው፡፡ ጥበቃው የሚመለከተው በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኝን የግለሰብ (ግላዊ) መረጃን እንጂ ከዚያ አልፎ መንግሥታዊ ባልሆኑና በግለሰብ እጅ የሚገኙትን አይደለም፡፡ በመሆኑም ጥበቃው በተለያዩ ምክንያቶች በመንግሥት እጅ የገቡትን መረጃዎች ነው፡፡

በአዋጁ ላይ በተሰጠው ትርጓሜ መሠረት መረጃ (Information) በየትኛውም ዓይነት ቅርፅ የተሰናዳን ስለሚይዝ፣ በተለይም ስለሰነድ ሲገለጽ በኤሌክትሮኒክ መልክ የተዘጋጁትንም በዝርዝር ስለጠቃቀሰ አኃዛዊ መረጃዎችንም እንደሚጨምር ግልጽ ነው፡፡

በመርህ ደረጃ ግለሰባዊ መረጃዎች በመረጃ ነፃነት ሰበብ ለሌላ አካል አይተላለፉም፡፡ አይሰጡም፡፡ ሊሰጡ የሚችሉበት ልዩ ሁኔታዎች ቢኖሩም በአዋጁ ተለይተዋል፡፡ በመንግሥት እጅ የሚገኝ (በየመሥሪያ ቤቱ) የግለሰብ መረጃ ግላዊ ይዘት ካለው ለሌላ አካል (ለጋዜጠኛም ቢሆን) አሳልፎ መስጠት በወንጀልም ያስጠይቃል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 2 ንዑስ ቁጥር 8 በተገለጸው መሠረት፣ በመንግሥት እጅ ሆነውም ግላዊ መረጃ በሚል ከተዘረዘሩት መካከል፣ አንድን ተለይቶ የሚታወቅን ሰው በሚመለከት የግለሰቡን የትምህርት፣ የሕክምና፣ የወንጀል፣ የቅጥር፣ የፋይናንስና የንግድ፣ ከማኅበራዊ ሁኔታዎችን (ብሔር፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ እምነት፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ዕድሜ፣ የፆታዊ ግንኙነት ዝንባሌ፣ እርግዝና ፣ጋብቻ፣ የአካል ብቃት/ጉዳት ሁኔታ…)፣ የግል መለያ ቁጥሮች፣ አሻራ፣ ደም፣ ስለግለሰቡ ዕድገት፣ ሽልማት፣ የገንዘብ ድጋፍ የተሰጡ አስተያየቶችና እንዲህ ዓይነት የግለሰብ መረጃዎችን አሳልፎ መስጠት ክልክልም ወንጀልም ነው፡፡

እነዚህ መረጃዎች በወረቀት የተያዙም ይሁን በኤሌክትሮኒክ ቅርፅ ልዩነት የለውም፡፡ ቁም ነገሩ ግላዊ መረጃ መሆናቸው ነው፡፡ ሹመኞችም ይሁኑ ቅጥረኛ ሠራተኞች ልዩነት በሌለው ሁኔታ ጥበቃው ተመሳሳይ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ የግለሰብ መረጃዎች፣ በተለይም አኃዛዊ የሆኑት ለመጠበቅ ሲባል ሕግ አልወጣም፡፡

የመረጃ አጠባበቅ ሕግ አስፈላጊነት

አዲስ ቴክኖሎጂ ሲመጣ፣ የሥጋት ዓይነቶች ሲጨምሩም ቢሆን እነዚህ ሕገ መንግሥታዊ ጥምር ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያሟሉ ግላዊነትን መድፈር (መገደብ) አይቻልም፡፡ ግለሰብም ሆነ ድርጅት የማንኛውንም ሰው የግላዊነት መብት የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ መንግሥት ደግሞ ማክበርም ማስከበር ግዴታው ነው፡፡

ከግላዊነት መብት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ካላቸው መካከል የአኃዛዊ (ዲጂታል) መረጃ ዋናው ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ግላዊ መረጃ (Personal Data or Information) በዚህ ጽሑፍ ውስጥ፣ መረጃ የሚለው በእንግሊዝኛ ‘ዳታ’ እና ‘ኢንፎርሜሽን’ (Data and Information) የሚሉትን ሁለት ጽንሰ ሐሳቦች ይወክላል፡፡ አንዳንድ ሕጎች የመጀመርያውን ከሁለተኛው ለይተው ጥቅም ላይ ቢያውሉትም፣ ሌሎች ሕጎች (ለምሳሌ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ) መረጃ የሚለው ሁለተኛውን ነው፡፡ ከግላዊነት መብት ጋር በተገናኘ ‹‹Personal Data or Personal Information›› የሚል ስያሜ ቢይዙም የሚያንፀባርቁት ግን ተመሳሳይ ሐሳብ ነው፡፡

የግል መረጃ ሲባል ግለሰብን ነጥሎ ለማመለከት፣ ለመለየት፣ ለማሳወቅ ጥቅም ላይ የሚውሉ መረጃዎችን፣ ለምሳሌ ስም፣ ዕድሜ፣ ብሔርና ዘር፣ ሃይማኖት፣ የደም ዓይነት፣ አሻራ፣ የልዩ ልዩ መታወቂያ ቁጥሮች፣ የቤተሰብ ብዛት፣ የቅጥር ሁኔታ፣ የትምህርትና የሕክምና መረጃዎችና ሌሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አንድን ግለሰብ ከሌላው የሚለዩ ወይም ለመለየት የሚውሉ መረጃዎችን ያጠቃልላል፡፡ እነዚህና መሰል መረጃዎች የሚሰበሰቡበት፣ የሚደራጁበት፣ የሚያዙበት፣ የሚተላለፉበትን ሁኔታ በመወሰን የግለሰብን መረጃ ደኅንነትም ግላዊነትም መጠበቅና ማስጠበቅም የመንግሥትም ጭምር ግዴታ ነው፡፡ መረጃ የሚሰበስቡ፣ የሚደራጁና ጥቅም ላይ የሚያውሉ፣ የሚይዙ ሰዎች (ድርጅቶችም ጭምር) ግዴታዎች ሊኖርባቸው ያስፈልጋል፡፡

መንግሥት ወንጀልን ለመከላከልም ከተፈጸመም ለምርመራ ሲባል የመረጃ ልውውጦች ላይ ክትትል ማድረጉ አይቀርም፡፡ የዘመኑ ቴክኖሎጂ በራሱ መረጃዎችን በቀላሉ ተደራሽ ያደርጋል፡፡ ለንግድ፣ ለትምህርት፣ ለሕክምና፣ ለባንክና ኢንሹራንስ፣ ወዘተ የሚሰጡ የግል መረጃዎች አጠባበቅን በሚመለከት ሕግና ሥርዓት መዘርጋት ተገቢ ነው፡፡ የግል መረጃዎችን ከየትም ሆነ ከየት አፈላልጎና መንትፎ በሚዲያዎች በሚወጡበት ጊዜ ንግድ ሊቃወስ፣ ቤተሰብ ሊበተን፣ ግለሰቦች ለአዕምሮ ሕመም ሊጋለጡም ራሳቸውን ሊያጠፉ ይችላሉ፡፡

የግለሰብ መረጃ አጠባበቅ ሕግ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ ስላልሆነ በዓለም አቀፍ፣በአኅጉርም በአገሮችም ትኩረት ከሳበ በደርዘን የሚቆጠሩ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ከመቶ በላይ አገሮች ራሱን አስችለው ሕግ አውጥተዋል፡፡ ወደ ሃምሳ ገደማ የሚሆኑ አገሮች ቢያንስ  በረቂቅ ደረጃ እንዳቸው መረጃዎች አሉ፡፡ በእስያም፣ በአውሮፓም፣ በአፍሪካም ይህንኑ የሚመለከቱ ስምምነቶች ወጥተዋል፡፡ የአውሮፓው (የቡዳፔስት) እና አፍሪካው (የማላቦ) ስምምነቶች ጎላ ብለው ይጠቀሳሉ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔም እ.ኤ.አ. በ2016 ዓ.ም. ይህንኑ በሚመለከት የግላዊነት መብት በአኃዛዊ ዘመን (The Right to Privacy in the Digital Age) የሚል ውሳኔ (GA Res. 71/99) አሳልፏል፡፡

የግለሰብ መረጃ አጠባበቅን የሚወስን ራሱ የቻለና በቂ ሕግ ከሌላቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ የግለሰብ መረጃዎችን የሕግ አስከባሪ አካላት (በተለይ ወንጀል ለመከላከልና ግብር ለመወሰንና ለማስከፈል) ግላዊነትን ተራምደው መረጃ ማግኘት የሚችሉበትን የብዙ አዋጆች አካል ሲያደርጉ፣ የግለሰብ መረጃ የሚጠበቅበትን ግን እዚህ ግባ የሚባል ጥበቃ ለማድረግ አልተፋጠኑም፡፡

በዘመነ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በሳይበሩ ምኅዳርም ቢሆን ይኼው አካሄድ የተጠበቀ ነው፡፡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (ኢንፎቴክ) እና ባዮቴክኖሎጂ (ባዮቴክ) መስፋፋት፣ ግላዊ መረጃዎችን በቀላሉ የትም ሆኖ ሊገኙ የሚችሉበትን ሁኔታ ይበልጥ እየጨመረው ዜሮ ግላዊነት ወደሚባል ደረጃ እያስጠጉት ነው፡፡ በግላዊነት ላይ የተጋረጠው ሥጋት ከፍተኛ ስለሆነ፣ ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እየተሰጠም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጉዞ ግን የኤሊም ሳይሆን የኋሊት ይመስላል፡፡ የኋሊት ያስመሰለው፣ ግላዊነትን ለመገደብ በተለያዩ አዋጆች ውስጥ በርካታ አንቀጾችን መሰግሰግ እንጂ፣ ጥበቃ ለማድረግ ሲባል ሕግ ለማውጣት (የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጁ ላይ ከተሰነቀረችው የግል መረጃ ጥበቃ በቀር) ‘ጆሮ ዳባ’ መባሉ ነው፡፡ የሰዎች ግላዊነት ጋር የተቆረኙ አኃዛዊ (ዲጂታል) መረጃ እየበዛ ቢሄድም ኢትዮጵያ ግን ይህንን ለመጠበቅ የሚያስችል በቂና ዘመኑን የዋጀ ሕግ አላወጣችም፡፡

የሳይበሩ ዓለም ኗሪዎች ስለግላዊነታቸው ጥበቃ የሚወስንና በሁሉም ዘንድ በወጥነት የሚተገበር ሕግም፣ ፖሊሲም፣ የሥነ ምግባር ደንብም የለም፡፡ ከአገር አገር፣ ከአኅጉር አኅጉር ይለያያል፡፡ መለያየቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የአገሮችና አኅጉሮቹ ሕግም ሆነ ፖሊሲ አሊያም የሥነ ምግባር መርሆች ከዕለት ወደ ዕለት እየተመሳሰሉ ከመሄድም አልፈው አሃዳዊነትን እየተስተዋለባቸው ነው፡፡ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ለኢኮኖሚያዊ ትብብርና ልማት (Organization for Economic Co-operation and Development aka OECD) የተባለው ተቋም እ.ኤ.አ. በ2013 የተወሰኑ መመርያዎችን ይፋ አድርጓል ሌሎችም አብነት አድርገው ይከተሏቸው ዘንድ፡፡

መጥኖ መሰብሰብ (Collection Limitation) ማለትም በሕጋዊና በፍትሐዊ መንገድ ቢቻል የመረጃው ባለቤት አውቆት መሰብሰብ አንዱ መርህ ነው፡፡ የመረጃ ጥራት (Data Quality) ትኩረት በመስጠት የሰበሰበው መረጃ ለሚፈለገው ዓላማና ግብ ተገቢነት ያለው፣ የተሟላና በሚፈለገውን እንጂ አለማግበስበስ ሌላው መርህ ነው፡፡

የግብ ልየታ (Purpose Specification) ደግሞ ሌላው ነው፡፡ መረጃ የሚሰበሰብበት ግብ ተለይቶ የታወቀና የተለየ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ የአጠቃቀም ለከት (Use Limitation) ማለትም የተሰበሰበን መረጃ ከታለመለት ውጭና ለሌላ ወገን ለመስጠትም ለመግለጥም የመረጃው ባለቤት ከፈቀደ አሊያም በሕግ መሠረት ብቻ እንዲወሰን ማድረግ መረጃ ከሚሰበስበው፣ ከሚደራጀውም ከሚይዘውም ይጠበቃል፡፡

የደኅነት መጠበቂያ (Security Safeguards) በመዘርጋት የግል መረጃን ከተሰበሰበበት ዓላማና አካል በቀር ሌላ እንዳሻው እንዳያገኘው የሚያደርግ መጠበቂያ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ማዋልም ሌላው መርህ ነው፡፡ ግልጽነት/ክፍትነት (Openness) ተግባራዊ በማድረግ ስለግላዊ መረጃ አሰባሰብና አጠቃቀም ሁኔታ ሕግና ፖሊሲዎቹ የታወቁ፣ ግልጽ የሆኑ መሆን አስፈላጊ ነው፡፡

የግለሰብ ተሳትፎ (Individual Participation) ማለትም የመረጃ ባለቤት የሆነ ሰው ስለመረጃው ሁኔታ የሚሳተፉበት (ለምሳሌ እንዲወገድ፣ እንዲስተካከል፣ እንዲሟላ፣ እንዲሻሻል ወዘተ) ለማድረግ ዕድል መስጠት፣ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከመረጃ ሰብሳቢና አከማቺ፣ አድራጅና ያዥ ይጠበቃል፡፡

ተጠያቂነትም (Accountability)  አንዱ መርህ ሲሆን መረጃ ሰብሳቢዎች ከላይ የተገለጹትን መርሆች ስለማክበራቸው ተጠያቂነት ማስፈን አለባቸው፡፡ መንግሥትም እነዚህን መርሆች ወደ ሕግ በመለወጥ አስገዳጅነት እንዲኖራቸው፣ በማይከበሩበት ጊዜም ሰዎች መብታቸውን የሚያስከብሩበት ሥርዓት መዘርጋት ይጠበቅበታል፡፡

የመረጃዎቹ ባለቤቶች፣ ማለትም ባለመረጃዎቹ ግለሰቦች፣ ስለመረጃዎቻቸው የማወቅ፣ የማግኘት፣ የማስተካከል ወይም የማስቆምና የማስወገድ፣ የመቃወም፣ የመውሰድ መብት ይኖራቸው ዘንድ ሕግ ያስፈልጋል፡፡ በሕግ ዕውቅና ያልተሰጠው ጥቅምን መብት ማድረግ አይቻልምና፡፡ መብት ከሆኑ በኋላ በሚጣሱበት ጊዜ ካሳን ጨምሮ ሌሎች ሕጋዊ መፍትሔዎች ማግኘት የሚያስችሉ ዘዴዎችን መዘርጋት፣ የመረጃ ሰብሳቢዎች፣ አድራጆች፣ ያዦች ግዴታዎችንና ኃላፊነቶች መወሰን የመረጃ አጠባበቅ ሕጉን የሚከታተል መንግሥታዊ ተቋም ማቋቋምም፣ ከመንግሥት የሚጠበቅ ነው፡፡

ይህም ሆኖ የተለያዩ ተግዳሮቶች መኖራቸው ላይቀር ይችላል፡፡ በሳይበር የሚገኙ መረጃዎች ድንበር ስለማያውቁና ጥበቃ የሚደረግላቸውን የግል መረጃዎች ለይቶ መወሰን ላይ ከአገር አገር መለያየት፣ የግል መረጃዎችን ጥበቃ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችም እንዲሁ ለየቅል የመሆን ዕድላቸው፣ ጥበቃ የሚደረግባቸው ሕጎች ብሔራዊነትና የመረጃዎች በቀላሉ ድንበር አልፈው መሄድ (መተላለፍ) ብሎም ለሕግ ማስከበር አስቸጋሪነት ለመረጃ አጠባበቅ ሥርዓት ተግዳሮት መሆናቸው እንደቀጠለ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ለማጠቃለል ያህል፣ ግላዊነት ራስን በራስ ከማስተዳደርም፣ ከነፃነትንም፣ ከክብርም፣ ከንብረት መብትም ጋር በጥብቅ ቁርኝት ስላለው ጥበቃ ሳያደርጉ፣ በጥሰቱ ጊዜ ምን እንደሚደረግ መፍትሔውን ሳያበጁ፣ ምንተዳዬ ተብሎ መንግሥታዊ ትከሻን ከፍ አድርጎ በመስበቅ ይተውት ዘንድ ቀላል አይደለም፡፡ ይልቁንም ጠንካራ፣ ቴክኖሎጂ ላይ ያልተንጠለጠለ ሕግ (ለቴክኖሎጂው ዓይነት ገለልተኛ የሆነ ሕግ)፣ ቴክኖሎጂው ሲዘጋጅና ዲዛይን ሲደረግ ግላዊነትን ማስጠበቅ እንዲችል በማድረግ፣ የግል መረጃዎች እንዴት መሰብሰብ፣ መቀመጥና መከማቸት፣ መሠራጨት እንዳለባቸው የሚገራ የሥነ ምግባር መርሆችን ማሳደግ አስፈላጊ ነው፡፡

ኢንተርኔት ሶሳይቲ’ የሚባለው ዓለም አቀፍ የሲቪል ማኅበረሰብ የሚከተሉትን በመፍትሔነት አቅርቧል፡፡ ትብብር፣ ሥነ ምግባር፣ የግላዊነት መጣስ ተፅዕኖ ላይ መስማማት፣ ስም አልባነትና የብዕር ስምን መጠቀም፣ መረጃ ቅነሳ፣ ግለሰቦች መምረጥ እንዲችሉ ማመቻቸት (መረጃ ለመስጠትም፣ ለመቀነስም)፣ የሕግ ማዕቀፍ ማመቻቸት፣ ቴክኒካዊ ማስጠበቂያ (መሣሪያም መረጃ ማመሳጠሪያም)፣ ግላዊነትን መጠበቅ የንግድ መወዳደሪያ አንድ አካል ማድረግ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተለይ የሕግ ማዕቀፍ መዘርጋቱ የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ ሕግ ከሌለ ሌሎቹም ውጤታማ መሆናቸው ያጠራጥራል፡፡

አዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...