Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንቱን በሽልማት ሸኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከስድስት ዓመታት በላይ ኅብረት ባንክን በፕሬዚዳንትነት የመሩት አቶ ታዬ ዲበኩሉ፣ ባንኩን ሲመሩ በቆዩባቸው ዓመታት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የቶዮታ ሥሪት የሆነ ቪ-8 ሞዴል ተሽከርካሪ፣ የግማሽ ሚሊዮን ብርና የአንገት ሐብል ሽልማት ተበረከተላቸው፡፡

የባንኩ የቦርድ አመራሮች ለአቶ ታዬ አበርክቶ ዕውቅና ለመስጠትና ለሽኝታቸው በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት፣ ከባንኩ ጋር ስለነበራቸውን ቆይታና ስላበረከቱት አስተዋጽኦ አመሥግነዋቸዋል፡፡ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዳይሬክተር አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣  ‹‹ይህ ዕለት የሽኝት መርሐ ግብር የምናከናውንበት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ወደ ኋላ ተመልሰን መልካም የሥራ ውጤቶችን የምንዘክርበትና ባንካችን በተጓዘባቸው የፈተናና የስኬት ዓመታት ውስጥ የተመዘገቡ መልካም ውጤቶችን የምናወሳበት ጭምር ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውጤታማነታችን ላይ አዎንታዊ ሚዛን ያሳረፉ በርካታ መልካም አጋጣሚዎች የመፈጠራቸውን ያህል አሉታዊ ጎናቸው ያመዘነ ተግዳሮቶች ባንካችንን ፈትነውት አልፈዋል፤›› በማለት፣ እነዚህን በመሰሉ አስቸጋሪ አጋጣሚዎች ውስጥ ኅብረት ባንክ የገነባውን መልካም ስምና ዝና ጠብቆ እንዲጓዝ ብርቱ ጥረት ማድረግ ግድ ይል እንደነበር አቶ ኢየሱስ ወርቅ አውስተዋል፡፡

ከእነዚህ ጥረቶች በስተጀርባ የአቶ ታዬ ሚና የጎላ ስለመሆኑ የገለጹት የቦርድ ዳይሬክተሩ፣ በዕለቱ የተሰናዳው ፕሮግራም ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት በኃላፊነት በቆዩባቸው ዓመታት ባንኩ የተቀዳጃቸውን መልካም ውጤቶች ለመዘከርና ከሥራ ባልደረባዎቻቸው ጋር በሥራ ሒደት ለነበራቸው የሥራ ግንኙነት ዕውቅና ለመስጠት ብሎም ለፕሬዚዳንቱ ያላቸውን አክብሮት ለመግለጽ የተሰናዳ ፕሮግራም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ ታዬ ኅብረት ባንክን በፕሬዚዳነትነት እንዲመሩ ኃላፊነት ከተረከቡበት ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ባንኩ የደንበኞቹን ፍላጎቶች ያሟሉ ወይም አካታችና ተደራሽ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ማቅረብ እንዲችል ከፍተኛ ሚና ስለመጫወታቸው ተነግሮላቸዋል፡፡

አቶ ታዬ በኃላፊነት በቆዩበት ጊዜ ባንኩ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት እንዲጀምር በማድረግና አገልግሎቱን በግንባር ቀደምነት በማስተዋወቅ ከሚጠቀሱ ሁለት ባንኮች አንዱ እንደነበር ተወስቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር የኅብር ወኪል የባንክ አገልግሎትን በቀዳሚነት እንዲጀመር በማድረግ በባንክ ኢንዱስትሪው ፈር ቀዳጅ እንዲሆን የላቀ አስተዋጽኦ በማበርከት ረገድ አቶ ታዬ የነበራቸው ሚና ትልቅ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ኅብረት ባንክ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው በቀዳሚነት ያስተዋወቀውን የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎት ተሻሽሎና አዳዲስ ይዘቶችን አካቶ ‹‹ኅብር ኦንላይን›› በሚል መለያ እንዲቀርብ ስለማድረጋቸውም ተወስቶላቸዋል፡፡ ይህ ሥራ የአቶ ታዬ አስተዋጽኦ እንደነበረበት የሚገልጸው የባንኩ መረጃ፣ ‹‹በኅብረት ባንክ ሁሌም አዲስ ነገር አለ›› በሚል መርህ ለባንክ ኢንዱስትሪው ፈር ቀዳጅ አገልግሎቶች እንዲተዋወቁ ጥረት ማድረጋቸው ተነግሮላቸዋል፡፡ እንደ አብነት ማሳያ የተደረገው ደንበኞች በኤቲኤም ብቻ ተጠቅመው ያለ ተጨማሪ የሰው ዕገዛ ገንዘብ መላክና መቀበል የሚችሉበት የአገር ውስጥ የኤቲኤም የሐዋላ አሠራር ማስተዋወቃቸው ነው፡፡

አቶ ታዬ ኅብረት ባንክ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችን ለኢንዱስትሪው እንዲያስተዋውቅ ከተጫወቱት ሚና በተጨማሪ በርካታ ተሞክሯቸው ተወስቷል፡፡ የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ሒደት ላይ የራሳቸውን አሻራ አሳልፈዋል፡፡  ኅብረት ባንክ በ2030 ዓ.ም. ከምሥራቅ አፍሪካ አምስት ታላላቅ ባንኮች አንዱ ለማድረግ የተቀመጠውን ስትራቴጂ ለመቅረፅ ድሎይት ከተባለው አማካሪ ድርጅት ጋር ስምምነት በመፈጸም ሥራው እንዲጀመር ማድረጋቸውም ተጠቅሷል፡፡

‹‹አቶ ታዬ ዲበኩሉ ባንኩን በፕሬዚዳንትነት መምራት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ እያንዳንዱ ቀን በስኬት አልፏል ባይባልም፣ ከባንኩ የሥራ አመራር ቡድንና ከመላው ሠራተኛ ጋር መልካም ቅንጅት በመፍጠር ባንኩ አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የጎላ ሚና አበርክተዋል፤›› ያሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ‹‹የባንካችን ፕሬዚዳንት በነበሩበትና ከዚያም አስቀድሞ በምክትል ፕሬዚዳንት ባገለገሉበት ወቅት ላሳዩት ውጤታማ ሥራ ምሥጋና በማቅረብ፣ ይህንንም ምሥጋና ለመግለጽ አቶ ታዬ የአንድ ቪ-8 ተሽከርካሪና የ500 ሺሕ ብርና የኅብረት ባንክ ዓርማ ያለበትን ወርቅ ፒን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በዕለቱ አቶ ታዬ ከዚህ ኃላፊነታቸው መልቀቅ በኋላ በግል ሥራ ላይ እንደሚሰማሩ አስታውቀው፣ ለተደረገላቸው የዕውቅናና የሽኝት ፕሮግራም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች