Thursday, June 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተመድ ግብርና ልማት ፈንድ የ40 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል

በምዕራፍ ሦስት እንደሚተገበር ለሚጠበቀው የገጠር ፋይናንስ ፕሮግራም (ሩፊፕ-3)፣ ዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ (አይፋድ) 40 ሚሊዮን ዶላር የብድርና ዕርዳታ ድጋፍ ለማቅረብ መስማማቱን አስታወቀ፡፡

በሮም ከሚገኙ ሦስቱ የተመድ ኤጀንሲዎች አንዱ የሆነው አይፋድ ግማሽ ሚሊዮን አርሶ አደሮች የፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያግዛቸውን ፕሮግራም የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያስተገብር ለመደገፍ የ35.7 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታና የ4.9 ሚሊዮን ዶላር ብድር፣ በጠቅላላው የ40 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡

የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቱ ረቡዕ ታኅሳስ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በሮም ሲፈረም በአይፋድ ወገን የተቋሙ ፕሬዚዳንት ጊልበርት ሆንግቦ ሲፈርሙ፣ ኢትዮጵያን በመወከል በሮም የኢትዮጵያ አምባሳደርና በተመድ የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ ዘነቡ ታደሰ ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡

ፕሮግራሙን ለማስፈጸም ከሚያስፈልገው 306 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ከ52 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ማዋጣት እንደሚጠበቅበት ሲገለጽ፣ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ገበሬዎችም 900 ሺሕ ዶላር በማዋጣት ተሳታፊ እንደሚሆኑ አይፋይድ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ባለፈው ኅዳር ወርም በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች ታሳቢ በማድረግ የአነስተኛ መስኖ እርሻ ሥራ ላይ የሚያተኮር ፕሮጀክት በማስፈጸም እስከ 500 ሺሕ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ከሚያስፈልገው የ451 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ የተወሰነ ድጋፍ ለመስጠት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን አይፋድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሚሆኑ ዜጎች ከሚደርስባቸው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት የሚታደግ ፕሮጀክትን ለመደገፍ ይውላል የተባለው ይህ ገንዘብ፣ በምግብ ምርት አያያዝና ጥንቃቄ ላይ ትምህርት በመስጠት የሥነ ምግብ ሁኔታን በኢትዮጵያ ለማሻሻል እንደሚውል ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ የምትመራበት የግብርና ሥርዓት መሠረቱን በዝናብ ላይ ጥገኛ በማድረግ ብሎም በአርብቶ አደር ትከሻ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በተከሰቱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳቶች ሳቢያ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የሕዝቧ የኑሮ ሥርዓት ለጉዳት ተጋልጠው መቆየታቸውን በማውሳት፣ በተለይ በድርቅ፣ በደን መጨፍጨፍና በምግብ ዕጦት ሲደርሱ የነበሩ ጉዳቶች የአገሪቱ ፈታኝ ችግሮች እንደነበሩ ገልጿል፡፡

በመሆኑም ‹‹ሎውላንድ ላይቪሊሁድ ሬዚሊየንስ ፕሮጀክት፤›› (ለቆላማ አካባቢዎች አይበሬ የገቢ ምንጭ ፕሮጀክት›› ተብሎ ሊተረጎም የሚችል)፣ ወደ ሥራ እንዲገባ የሚያስችለው ድጋፍ የአይፋይድ ፕሬዚዳንት ጊልበርት ሆንግቦ፣ በሮም የተመድ የምግብና እርሻ ኤጀንሲዎች የኢትዮጵያ አምባሳደር ከሆኑት ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ ጋር ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነታቸው መሠረት፣ ከ451 ሚሊዮን ዶላር ድጋፉ ውስጥ 90 ሚሊዮን ዶላሩን አይፋድ በብድር የሚያቀርበው ገንዘብ ነው፡፡ 350 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ከዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር በጋራ የፋይናንስ ስምምነት (80 በመቶው በብድርና 20 በመቶው በዕርዳታ) የሚቀርብ ነው፡፡ የተቀረው 11 ሚሊዮን ዶላር ከተጠቃሚዎች እንደሚዋጣ በብድርና በዕርዳታ ስምምነቱ ሰነድ መካተቱን አይፋድ ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

እንደ አይፋድ ማብራሪያ ፕሮጀክቱ በዋናነት የተቀረጸው ከተመድ የዘላቂ ልማት ግቦች የመጀመሪያውና ሁለተኛውን፣ ማለትም ድህነትንና ረሃብን ማስወገድ የተሰኙትን ግቦች ማዕከል በማድረግ አነስተኛ የመስኖ እርሻዎችን ለማስፋፋት የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን በማስረጽ በዝናብ ላይ የተመሠረተውን የአገሪቱን የግብርና ዘርፍ በመጠኑም ለማገዝና የዝናብ ላይ ጥገኝነትን ለመቀነስ ያለመ ነው፡፡ በተለይ የዝናብ ሥርጭትና መጠን በየጊዜው እየተዛባና የዝናብ ወቅትም እየተቀያየረ በመምጣቱ፣ የመስኖ እርሻ የግድ እንደሚል ተመልክቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አነስተኛ አርሶ አደሮችን የሚደግፉ የጥናትና የምርምር ሥራዎችን በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖና መላመድ ላይ ያተኮሩ ሥራዎችም ይካተታሉ፡፡

የመስኖ ሥራዎችን የሚደግፈው ይህ ፕሮጀክት ለግጦሽ መሬቶችና ለተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር እንዲሁም መሠረታዊ የማኅበራዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ላይ በመሥራት በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ ድርቅና ሌሎች የአየር ንብረት አደጋዎችን ለመቀነስና የገበሬውና የአርብቶ አደሩ ሀብትም እንዳይጠፋ ለመከላከል እንደሚያግዝ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በውኃ፣ በመሬትና በግጦሽ ዕጦት በአርብቶ አደሩና በከፊል አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ አካባቢ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቀረት የሚያስችል ሥነ ምኅዳር እንዲኖር ለማስቻል የሚጫወተው ሚናም ታሳቢ ተደርጓል፡፡

በፕሮጀክቱ ከ500 ሺሕ ያላነሱ ተጠቃሚዎች እንደሚካተቱ፣ ግማሽ በግማሽም ሴቶች እንደሚሆኑ፣ በዚህም መሠረት ፕሮጀክቱ በአፋር፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በሶማሌ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል በሚገኙ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎችን እንደሚያካትት ታውቋል፡፡

ይህን ፕሮጀክት ለመተግበር ፋይናንስ ያቀረበው አይፋድ፣ እ.ኤ.አ. ከ1980 ጀምሮ በኢትዮጵያ የገጠር ልማት ላይ ላተኮሩና እስከ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው 20 ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች እንዲተገበሩ ከ795.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ማድረጉን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች 12 ሚሊዮን የገጠሩን ሕዝብ በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ታስበው ድጋፍ የተደረገባቸው ናቸው፡፡

አይፋይድ በሮም ከሚገኙ የተመድ ኤጀንሲዎች አንዱ ሲሆን፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት አብረውት በተመድ ሥር በሮም የሚወከሉ ተቋማት ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች