Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለድህነት መድኃኒቱ ሥራ ብቻ!

‹‹ኢትዮጵያ ድሃ ነች›› የሚለው መገለጫ እንደ ኢትዮጵያዊ ለሚያስብ ይጎረብጠዋል፡፡ ያሳምመዋል፡፡ የቱንም ያህል ቢያመን እውነታው ግን ድሆች መሆናችን ነው፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያን ድሃ ያሰኟትና አበክረን ልንዘረዝራቸው የሚችሉ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ባለን የተፈጥሮ ሀብትና ባሉን መልካም ዕድሎች አለመጠቀማችን ለድህነታችን መንስዔ በመሆን ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

የፖለቲካ አለመረጋጋትና ሽኩቻዎቻችን፣ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የእርስ በርስ ግጭቶችና ጦርነቶች፣ የተረጋጉና ዘመን ተሻጋሪ ተቋማትን ለመፍጠር አለማስቻላቸው ተደማምረው ወደኋላ አስቀርተውናል፡፡ እንዲህ ያሉት የዘመናት ችግሮቻችን እንደተጠበቁ ሆነው፣ የኢትዮጵያችን ድህነት ሲታሰብ በዋና መንስዔነት ልናስቀምጠው የምንችለው ሌላው ነጥብ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት በአግባቡ ልትጠቀምበት አለመቻሏ ነው፡፡ ሀብቷን በአግባቡ ማስተዳደር አለመቻሏም ተጠቃሽ ችግር ነው፡፡ ብስለት ያለው ፖሊሲና ትግበራ ማጣታችን ሳያንስ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ዜጎች ስንፍና የተጠናወተን፣ የደከመ የሥራ ባህል ያለንና የሥራ ዲስፕሊናችን እጅግ የተበላሸ መሆኑ ለድህነታችን ምክንያት መሆኑ አይሸሸግም፡፡  

የማዕድን ሀብት፣ ለግብርና ምቹና ተስማሚ መልከዓ ምድር፣ ዓለም ተንሰፍስፎ ሊጎበኛቸው የሚችሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችና ሀብቶች፣ በጣዕሙ የተለየ የቡና ምርት፣ የቁም እንስሳት ሀብት የታደልን ስለመሆናችን መጥቀሱ፣ መናገሩ አይጠፋንም፡፡ በዓለም ቀዳሚ ከመባሉ አገሮች በመጀመርያዎቹ ረድፎች የሚያስቀምጡ አንጡራ ሀብቶች ያሏት አገር አለችን፡፡  

ይሁንና የአገራችንን ገፀ በረከቶች በሚፈለገው ደረጃ ተጠቅመን በአግባቡ አደራጅተን፣ በየፈርጁ አሰናድተንና አምርተን ወደ ገንዘብ መቀየር ባለመቻላችን ድሃ ብቻም ሳይሆን የሌሎች ተመጽዋች ብሎም ለማኝ ሆነን ለዘመናት ዘልቀናል፡፡

ከድህነት ሊያስወጡ በሚችሉ ሥራዎች ላይ አተኩሮና አምርሮ የመሥራት ልምድና ሞራል የሌለን መሆናችን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባሉን ሀብቶች ሌላው ቢቀር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያለብን ስንፍና አገራችንን ወደኋላ እየጎተታት ነው፡፡ እሴት ተጨምሮበት ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የአገር ሀብት ስንት ገንዘብ ሊያስገኝልን ሲችል በጥሬው መላክም ፍዳ እየሆነብን መጥቷል፡፡ የአገሪቱ ወጪ ንግድ ምርቶች ይባሱኑ  የሕገወጦች መፈንጫ ሆነዋል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ በቀደሙ ዓመታት የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ያስገኙ የነበሩ ምርቶች ቁልቁል መሄዳቸው ነው፡፡ እነዚህ ምርቶች በሕገወጥ ንግድ እየተጠለፉ ነው፡፡

በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ በኮንትሮባንድ ከአገር ማስወጣት  ተለምዷል፡፡ የአገር ሀብት በጓሮ ሲሸሽና ሕጋዊ ንግዱ እየተጎዳ ሲመጣም የአገራችንን የድህነት መውጫ ዕድሜ እንዲራዘም በማድረግ መጉዳቱ አይቀሬ ነው፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፍ ለማጋበስ የሚሯሯጥ ባለሀብት በበዛበት አገር ውስጥ ዘላቂና የጋራ ጥቅም በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ የሚተጉን በባትሪ ብንፈልግ ለማግኘት አዳጋች ነው፡፡ ብዙዎችን ሊጠቅም አገርንም ከድህነት ሊያወጣ በሚችል ሥራ ላይ  ጨክኖ የሚጋፈጠውን የሚያደሙ አሠራሮችም ችግራችንን አባብሰውታል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም የምትታወቅበትን የእንስሳት ሀብትና የቆዳ ምርት ምን ያህል ለድህነት የተመቸን ሕዝቦች መሆናችንን ከሚያመላክቱ የስንፍና መገለጫዎቻችን መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ ዘርፍ ብቻ የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ገቢ ማሳደግማ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቷን ማሟላት በተቻለ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዘርፍ ከማደግ ይልቅ ማሽቆልቆል ውስጥ ሲዋልል እናያለን፡፡ ሥጋ ባህሉ የሆነው የአገራችን ሕዝብ በየዕለቱ ከሚያርደው እንስሳ የሚገኘውን ቆዳና ሌጦ እንደ ሀብት ሳይሆን እንደ አልባሌ የማየቱ ሳንካ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ መጥቶ ጥሬ ቆዳ ከውጭ ማስገባት ጀማምሮን ነበር፡፡

በአንድ ወቅት ቆዳ ፋብሪካዎች በየበዓላቱ ወቅት የፍየልና የከብት ቆዳ በሽሚያ ሲገዙ እንዳልነበር፣ ዛሬ ዋጋ እያጣ የመምጣቱ ምክንያት ምንድን ነው የሚል አካል በመጥፋቱ ቆዳ እየተጣለ ቆየ፡፡ ይህንን ሀብት በአግባቡ ተጠቅሞ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ሲገባ፣ ጭራሹኑ በየቦታው መጣሉ ‹‹ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል›› ከሚሉትም በላይ አላዋቂነት ነው፡፡

ከቆዳና ከቆዳ ውጤት የሚዘጋጁ ምርቶችን ለማምረት ስንትና ስንት ኢንቨስትመንት የሚፈስበት ቆዳ ሆኖ ሳለ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ከውጭ እየገዛን ማስገባታችን በእርግጥ ይህች አገር ድሃ መባል ያንሳታል ያሰኛል፡፡ ዛሬ በገፍ ከውጭ የምናስገባቸው ምርቶች ዋነኛ ጥሬ ዕቃዎቻቸው እዚሁ ጉያችን እያሉ ከውጭ ማስገባታችንን በመግታት የተሳሳተ አካሄዳችንን የሚያስተካክል አሠራር እንዴት እናጣለን?

ዛሬም በየበዓላቱ ከዕርድ የሚሰበሰበውን ቆዳ ከቁርበትና ከአጎዛ አልፎ እሴት ጨምሮ ጥሩ ዋጋ ሊያወጣ የሚችል ምርት ማድረግ ያልቻልንበት ምክንያት ምንድነው? ስለዚህ ድህነታችን የስንፍናችን ውጤት፣ ያለንን ሀብት በአግባቡ ያለመጠቀም ችግር መሆኑን መናገር ስህተት አይሆንም፡፡

ከአፍሪካ አንደኛ የቀንድ ከብት በብዛት ያላት አገር፣ ይህንን ሀብቷን ከእነ ነፍሱ አሊያም ሥጋውን በልቶ መሸጥ ሲቻል፣ ቆዳና ሌጦውንም ወደ ገንዘብ መቀየር ሲገባ በባዶ ሜዳ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አሥረኛ እያሉ መተረክ ድህነትን አያሸንፈውም፡፡

በመሆኑም ከሰሞኑ በከፊል የተዘጋጀ ቆዳን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ይከለከል የነበረውን የ150 በመቶ ታክስና ቀረጥ መንግሥት ማንሳቱ መልካም ቢሆንም፣ ይህ ብቻውን መፍትሔ እንደማሆን ግን ማሰብ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ሥራ ለተሰማሩት ተጨማሪ ድጋፍ መስጠት፣ ወደ ውጭም ሆነ ለአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ተገቢውን ምርት ማቅረብ ሲችሉ ማበረታታትና ማገዝ የመንግሥት ሚና መሆን አለበት፡፡

   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት