Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያ ክልል በተነሳ የወሰን ጥያቄ ምክንያት ዘጠኝ ሺሕ ቤቶች ለነዋሪዎች ማስተላለፍ አለመቻሉ...

በኦሮሚያ ክልል በተነሳ የወሰን ጥያቄ ምክንያት ዘጠኝ ሺሕ ቤቶች ለነዋሪዎች ማስተላለፍ አለመቻሉ ተገለጸ

ቀን:

በ40/60 የግንባታ ሽርክና የቤት ችግርን ከባለሀብቶች ጋር ለመቅረፍ ፕሮጀክት መታቀዱ ተነገረ

 የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመጀመርያ ጊዜ ያቀረቡት የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ለነዋሪዎች በዕጣ እንዲተላለፉ ካደረጓቸው 51 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል፣ ዘጠኝ ሺሕ የሚሆኑት ቤቶች ከኦሮሚያ ክልል በተነሳ የወሰን ጥያቄ ምክንያት ነዋሪዎች እንዲረከቧቸው ማድረግ አለመቻሉን ገለጹ።

ምክትል ከንቲባው ይህንን የተናገሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ አልፎ አልፎ የሚያደርገውን ክትትልና ግምገማ ለማድረግ፣ ሰኞ ታኅሳስ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. የአስተዳደሩን ምክትል ከንቲባና ካቤኔ በመጥራት ባከናወነው ግምገማ ነው።

በአፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ሰብሳቢነትና የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አመራሮች በተሳተፉበት በዚህ መድረክ፣ የቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎች ከሕዝብ የሰበሰቧቸውን ቅሬታዎች፣ እንዲሁም በቋሚ ኮሚቴ ደረጃ ባከናወኗቸው የመስክ ምልከታዎች ለይተናቸዋል ያሏቸውን ችግሮች አንስተው ማብራሪያ ጠይቀዋል።

የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎቹ ካነሷቸው ዓበይት ጉዳዮች መካከል የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መዘግየት፣ የመሬት ወረራ መንሰራፋትና የሰነድ አልባ ይዞታዎች ችግር ዕልባት ያላገኙና ነዋሪዎችን እያማረሩ የሚገኙ መሆናቸውን በመጥቀስ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ምክትል ከንቲባው በሰጡት ምላሽ፣ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል ግንባታቸው ከሞላ ጎደል ተጠናቆ ለነዋሪዎች ሳይተላለፉ ለረዥም ጊዜ የቆዩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በፍጥነት ተጠናቀው እንዲተላለፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ጥረት በጥቅሉ ወደ 51 ሺሕ የሚጠጉ ቤቶች በዕጣ ወደ ነዋሪዎች እንዲተላለፉ መደረጋቸውን የተናገሩት ምክትል ከንቲባው፣ በዚህ መንገድ ከተላለፉት ቤቶች መካከል ዘጠኝ ሺሕ የሚሆኑት የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ወሰን ውስጥ ናቸው በማለቱ ዕጣ የወጣላቸው ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሊሆኑ እንዳልቻሉ አስረድተዋል።

ምክትል ከንቲባው ዕጣ ወጥቶባቸው ለተጠቃሚዎች እንዲተላለፉ ከዓመት በፊት ከተወሰነባቸው 51 ሺሕ ቤቶች መካከል በተለይ አሥር ሺሕ የሚሆኑት ኮዬ ፈጬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ቤቶች ውስጥ አንድ ሺሕ የሚሆኑት ለቤቶቹ ግንባታ ሲባል ይዞታቸውን እንዲለቁ ተደርገው ተገቢው ካሳ ላልተከፈላቸው አርሶ አደሮች እንዲተላለፉ የከተማ አሰተዳደሩ ካቢኔ በወቅቱ መወሰኑን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለአርሶ አደሮቹ እንዲተላለፉ የተባሉት ቤቶች በውሳኔው መሠረት ቢተላለፉም፣ በተቀሩት የኮዬ ፈጬ አካባቢ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና ክልሉን በወቅቱ ያስተዳድር የነበረው ኦዴፓ ቤቶቹ የክልሉ አስተዳደር ወሰን ክልል ውስጥ ናቸው የሚል ጥያቄ አንስቶባቸዋል።

በመሆኑም በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰን ተለይቶ ሕጋዊ ውሳኔ ሳያገኝ ቤቶቹ ለተጠቃሚዎች እንዳይተላለፉ አቋም መያዛቸውን በወቅቱ አስታውቀው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ለተነሳው ጥያቄ መፍትሔ ለመስጠት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በእሳቸው የሚመራ ዘጠኝ አባላትን የያዘ ኮሚቴ ማቋቋማቸውን ይፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ኮሚቴ የወሰን ጥያቄውን ለመመለስ ያደረገው እንቅስቃሴ ስለመኖሩ እስካሁን በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።

ከላይ ከተገለጸው ችግር በተጨማሪ 130 ሺሕ ቤቶች ተገንብተው በወቅቱ ለባለዕድለኞች ባለመተላለፋቸው፣ እንዲሁም በተላለፉ ቤቶች ውስጥ ግለሰቦች ባለመግባታቸው የተነሳ ክፍያ አለመጀመራቸውን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ለምክር ቤቱ ያስረዱ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያትም አስተዳደሩ 50 ቢሊዮን ብር የባንክ ዕዳ መሸከሙን ገልጸዋል።

ይህንን የዕዳ ሸክም ለማቃለልም የተወሰነ ዕዳ ስረዛ የሚደረግበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ድርድር ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። ከቤቶች ልማት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት አስተዳደሩ ያለቁትን የማስተላለፍና የተጀመሩትን በፍጥነት የመጨረስ ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝና ግንባታቸው የተጠናቀቁ 38 ሺሕ ቤቶችም በቅርቡ ለነዋሪዎች እንደሚተላለፉ ገልጸዋል።

የቤት ችግርን ለማቃለል እስካሁን የነበረውን የግንባታ ሥልት በመቀየር ባለሀብቶችን በማሳተፍ ፈጣን የቤት ግንባታ ሒደት መከተል እንደተጀመረ፣ በዚህም መሠረት 500 ሺሕ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ ትግበራ መጀመሩን አስረድተዋል።

በአዲሱ የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት የከተማ አስተዳደሩ ለባለሀብቶች መሬት በማቅረብና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ በራሳቸው ወጪ የቤት ግንባታ ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረግ መጀመሩን የተናገሩት ምክትል ከንቲባው፣ ባለሀብቶቹ 60 በመቶ ድርሻ እንደሚኖራቸውና አስተዳደሩ ደግሞ ቀሪውን 40 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል።

በዚህ ሥልትም የግል ባለሀብቱን በማሳተፍ ለገበያ የሚቀርቡና ከአስተዳደሩ ደግሞ በሚኖረው ድርሻ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች እንደሚያስተላልፍ ገልጸዋል።

በዚህ መንገድም የከተማዋ የመኖሪያ መንደሮች በሀብት ደረጃ ልዩነት የማያስተናግዱ፣ ሀብታሙንም ደሃውንም በጋራ ማኖር የሚችሉ ሆነው ለነዋሪዎች እንዲተላለፉ ያስችላል ብለዋል።

በከተማ ውስጥ የሚታየውን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍም በሁሉም የአዲስ አበባ መግቢያ በሮች ምግብ ነክ ሸቀጦችን ከአርሶ አደሩ ተቀብሎ በቀጥታ ለሸማቹ ለማቅረብ የሚያስችል አሠራር፣ በቅርቡ ተግባራዊ የሚያደርግ ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀን 80 ሺሕ ዳቦ የማምረት አቅም ያለው የዳቦ ፋብሪካ ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑንና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥም ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ አስረድተዋል። በተመሳሳይም የዘይት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ባለሀብቶችን በማስተባበር ግንባታ መጀመሩን ገልጸዋል።

ሕገወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ያስረዱት ምክትል ከንቲባው ከፌዴራል ፖሊስ፣ አዲስ አበባና ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመተባበር በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዚህም ጥረት ከ2004 ዓ.ም. ወዲህ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ መሬቶችን የማስለቀቅና ሕግ የማስከበር ተግባር እንደሚፈጸም አስረድተዋል። ፓርላማው ይኼንን የመሰለ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በአዲስ አበባ አስተዳደር ላይ ሲያደርግ የመጀመርያው አይደለም።

አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም አቶ ድሪባ ኩማ ከንቲባ ሆነው ከተማዋን ባስተዳደሩባቸው ወቅቶች ቁጥጥር አድርጎ እንደሚያውቅ፣ በከንቲባ ድሪባ ኩማ የአስተዳደር ዘመን በአዲስ አበባ የቤት ግንባታ ፕሮጀክት ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ጥልቅ ኦዲት እንዲያከናውን በወቅቱ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ በነበሩት አቶ አባ ዱላ ገመዳ ታዞ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይሁን እንጂ ፓርላማው ይኼንን ክትትልና ግምገማ የሚያከናውንበት ግልጽ አሠራርም ሆነ ሕጋዊ ሥልጣን በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ አልሠፈረም።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...