ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ኤርትራ መዲና አስመራ አቅንተው በተጀመረው የኢትዮ ኤርትራ ዕርቅ የሳዑዲ ዓረቢያ እጅ እንዳለበት፣ የሳዑዲ ዓረቢያ የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር አሻርቅ አል አውሳት ለተባለ ለአገራቸው ሚዲያ ቢናገሩም፣ ኤርትራ ግን አስተባበለች፡፡
ምክትል ሚኒስትሩ አህመድ ካታን አዲስ የተመሠረተውን በቀይ ባህር ዙሪያ የሚገኙ የዓረብና የአፍሪካ አገሮች ምክር ቤት በተመለከተ በሰጡት ዘለግ ያለ ቃለ ምልልስ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ በአፍሪካና በባህረ ሰላጤው ያላት ተፅዕኖ እያደገ መጥቷል ብለዋል፡፡ የዚህ አንዱ ማሳያም በአፍሪካውያን መካከል የተፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ናቸው ሲሉ አክለዋል፡፡
‹‹የሳዑዲ ዓረቢያ ጥረቶች በአፍሪካ ወንድማማቾች መካከል ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታት አግዟል፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ሳዑዲ ግጭቱን በመፍታት ረገድ ቀዳሚ ኢስላማዊ ሚናዋን በመጠቀም የመጀመርያው የጥረቷ ፍሬ የሆነው የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ስምምነት ነው ብለዋል፡፡
ይሁንና ይኼንን ገላጸ ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር በድረ ገጹ ሻባይት ዶት ኮም ባወጣው መግለጫ፣ የምክትል ሚኒስትሩን አገላለጽ በመጠቆም አገላለጹ እጅግ የተሳሳተ ነው ብሏል፡፡
የኤርትራ መንግሥት ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ይኼ አገላለጽ ከታሪካዊው ስምምነት ጥንስስና እውነታዎች በእጅጉ የተራራቀ ነው፡፡ ለዓለም አቀፍ አገሮችም መልካም ፈቃድ ዕውቅና የምንሰጥ ቢሆንም፣ አፍሪካንና ስኬቶቿን የሚያሳንሱና የራስን የበላይነት የሚያጎሉ ትርክቶች አግባብ ካለመሆንም አልፈው የአገሪቱን (ሳዑዲን) መልካም ገጽታ የሚያቀጭጩ ናቸው፤›› በማለት ድርጊቱ ገልጾታል፡፡
በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኖቤል ሽልማት ማግኘታቸውን በማመልከት፣ ሽልማቱ ግን ለእሳቸው ይገባ እንደነበር ጠቁመው ሰፊ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. ለ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ‹‹ስለኖቤል ሽልማቱ ልንገራችሁ፤›› ሲሉ ትችታቸው ለተሰበሰቡ ታዳሚዎች ሰንዝረዋል፡፡
‹‹ስምምነት አድርጌ እንዲት አገርን አተረፍኩ፡፡ አሁን ደግሞ የዚያች አገር መሪ አገሪቱን አድኗታል በሚል የኖቤል የሰላም ሽልማት እንደተሰጣቸው ሰማሁ፡፡ እኔ ያደረግኩት ነገር ነበር? አዎን፡፡ ነገር ግን ታውቃላችሁ? እንዲህ ነው የሚሠራው፡፡ እስከምናውቀው ድረስ አስፈላጊው ነገር ያ ነው፡፡ ታላቅ ጦርነት ነው ያስቀረሁት፣ ሁለት አገሮችን አድኛለሁ፤›› በማለትም አሜሪካ የተጫወተችውን ሚና አስረድተዋል፡፡
የፕሬዚዳንት ትራምፕን ንግግር በሚመለከት በደቡብ አፍሪካ ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የኖቤል ኮሚቴው እንዴት የተሸላሚ ምርጫ እንደሚያደርግ እንደማያውቁ በመግለጽ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሽልማቱ ላይ ቅሬታ ካላቸው ወደ ኦስሎ ነው እንጂ መሄድ ያለባቸው ወደ ኢትዮጵያ አይደለም ብለዋል፡፡