Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበአወዛጋቢው የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች የሰበር ዳኝነት ሥልጣን ላይ ከፊል መፍትሔ ያካተተ...

በአወዛጋቢው የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች የሰበር ዳኝነት ሥልጣን ላይ ከፊል መፍትሔ ያካተተ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

ቀን:

የፌዴራል ሰበር ችሎት በሦስት ምክንያቶች ብቻ በክልል የተሰጠ ውሳኔን ሊመለከት ይችላል

በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ታይቶ ውሳኔ የተሰጠበት የሕግ ስህተት ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በይግባኝ እንዳይመጣ ገደብ የሚጥል ረቂቅ ሕግ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

ባለፈው ሳምንት ለምክር ቤቱ የቀረበው ይህ ሕግ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጅ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ተበታትነው የሚገኙ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የተመለከቱ አዋጆችን በአንድ አዋጅ አጠቃሎ የሚይዝና በተለያዩ ጉዳዮች ላይም አዳዲስ ማሻሻያ ድንጋጌዎችን ያካተተ ነው።

- Advertisement -

ከተካተቱት አዲስ ድንጋጌዎች መካከል ጉልህ ሥፍራ የሚይዘው በርካታ የሕገ መንግሥትና የፌዴራሊዝም ምሁራን ላለፉት በርካታ ዓመታት ክርክር ሲያደርጉበት የከረመው፣ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በክልል ጉዳይ ላይ የቀረበላቸው የሕግ ስህተት እንዲታረም የሚጠይቅ አቤቱታ ላይ የሚሰጡት የሰበር ዳኝነት የመጨረሻ ሊሆን ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው መሠረታዊ ያልሆነ ከፊል ምላሽ ይገኝበታል።

በዚሁ መሠረት በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ሰበር ችሎቶች ውሳኔ ያገኙ የሕግ ስህተት አቤቱታዎች ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሊባልባቸው የሚችለው፣ በሦስት ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር በክልል ሰበር ችሎቶች የተሰጡ ውሳኔዎች የመጨረሻ እንደሚሆኑ ረቂቅ ድንጋጌን ይዟል።

በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቶች ውሳኔ የተሰጠባቸው አቤቱታዎች ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ሊጠየቅባቸው የሚያስችሉት ሦስት ጉዳዮችም፣ በክልል ደረጃ የተሰጠው ውሳኔ የፌዴራሉን ሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች የሚቃረን ከሆነ፣ የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት አስቀድሞ የወሰናቸውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች የሚቃረን እንደሆነና የሕግ ስህተቱ ሰፋ ያለ የኅብረተሰብ ክፍልን በሚነካ መንገድ፣ አገራዊ አንድምታ የሚያስከትል ከሆነ ብቻ እንደሚሆን ረቂቁ አዋጁ ያመለክታል።

 በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 80 ሥር ስለክልል ፍርድ ቤቶችና ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተቀመጡት ድንጋጌዎች አሻሚነት በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የተሰጡ ውሳኔዎች፣ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት እንዲታረሙ ማድረግ ይቻላል ወይ የሚለውን አከራካሪ እንዳደረገው፣ ረቂቁ አዋጁን ለማብራራት አባሪ የተደረገው ሰነድ ያስረዳል።

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 80 ሥር የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በክልል ጉዳይ ላይ የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ሥልጣን እንደሚኖራቸው ሲደነግግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበትን ማንኛውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም እንደሚችል መገለጹና ከዚህ ጎንም የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበትን በክልል ጉዳይ የተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔን ለማረም፣ በሕገ መንግሥቱ ሥልጣን መሰጠቱን ማብራሪያ ሰነዱ ይገልጻል።

 ሕገ መንግሥቱ በተረቀቀበት ወቅት የተያዘው ቃለ ጉባዔ ላይ ከአርቃቂዎቹ መካከል ከአንድ አባል ከላይ በተቀመጡት ድንጋጌዎች ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በክልል ሰበር ችሎት የተሰጡ የመጨረሻ ውሳኔዎችን ማየት እንደሚችል አመላካች አስተያየት ቀርቦ ሕገ መንግሥቱ የፀደቀ ቢሆንም፣ የክልል ጉዳይን በተመለከተ በክልል ሰበር ችሎት ዳኝነት የተሰጠበት ጉዳይን የግድ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የማየት ሥልጣን አለው ማለት እንዳልሆነ ክርክር የሚነሳበት ነጥብ እንደሆነ ያመለክታል።

ነገር ግን ይህ የሰበር ውሳኔን በሰበር የማየት ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊነት ጉዳይ ዕልባት ሊያገኝ የሚችለው ሕገ መንግሥቱን በሚተረጉመው አካል በመሆኑ፣ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሚስተዋለው የአቤቱታዎች ብዛትና የዜጎች እንግልት አንፃር፣ እንዲሁም በዚህ ምክንያት በሰበር ችሎት ውሳኔ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ዳኝነት ጥራት ከግምት በማስገባት ከላይ በተገለጸው አግባብ እንዲስተካከል ረቂቅ ድንጋጌዎቹ መካተታቸውን ያስረዳል።

በሌላ በኩል የሕግ ስህተትን በተመለከተ አሁን ባለው ሕግ የተሰጡት ድንጋጌዎች በቂ ባለመሆናቸው አንድ አዲስ ድንጋጌ እንዲካተት ተደርጎ በረቂቁ ቀርቧል። አሁን ባለው አሠራር ወደ ሰበር ችሎት ከሚያስኬዱት መመዘኛዎች መካከል ወደ ሰበር የሚያስቀርበው የመጨረሻ ውሳኔው ሲሰጥ የተጠቀሰው የሕግ አንቀጽ ስህተት ያለበት በመሆኑ፣ ያላግባብ በመተርጎሙ፣ ጭብጥ ያለ አግባብ በመያዙና የመሳሰሉት ይገኙበታል።

በረቂቁ ከላይ የተገለጹትና ሌሎች እንዳሉ ሆነው በተጨማሪነት ስህተቱ በውሳኔው ላይ ፍትሕን የማዛባት ጉልህ ውጤት አስከትሏል ወይ የሚለው ተጨማሪ መመዘኛ ሆኖ በረቂቁ ተካቷል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...