Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሆቴል ተከልክለው በሜዳ ላይ የቅድመ ፓርቲ ጉባዔ ያደረጉት እነ አቶ እስክንድር ነጋ...

ሆቴል ተከልክለው በሜዳ ላይ የቅድመ ፓርቲ ጉባዔ ያደረጉት እነ አቶ እስክንድር ነጋ ፓርቲ መሠረቱ

ቀን:

አቶ እስክንድር ነጋ የፓርቲው ጊዜያዊ ሊቀመንበር ሆኖ ተመርጧል

የቅድመ ፓርቲ ጉባዔ ለማድረግና ፓርቲ ቅድመ ዕውቅና ለማግኘት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለማቅረብ የመጀመርያ ስብሰባቸውን በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል እሑድ ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ለማድረግ በሥፍራው ሲደርሱ በፀጥታ ኃይሎች ቢከለከሉም፣ በሆቴሉ ደጃፍ (ሜዳ) ላይ ጉባዔ በማድረግ ‹‹ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ›› (ባእዴ) የሚል ስያሜ ያለው ፓርቲ መመሥረታቸውን አስታወቁ፡፡

የፓርቲው ጊዜያዊ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መሆኑን የገለጸው አቶ ስንታየሁ ቸኮል ለሪፖርተር፣ ‹‹መሥራች ጉባዔያችንን በሆቴሉ በር ላይ አድርገናል፡፡ በሆቴሉ ልናደርግ የነበረውን አጀንዳ በሜዳ ላይ በውጭ ጨርሰናል፡፡ ይህንንም ለማድረግ የተገደድነው ሲቪል የለበሱ የፀጥታ ሰዎች ከበላይ በተሰጣቸው መመርያ መሠረት ስብሰባውን ማድረግ እንደማንችል ከነገሩን በኋላ ነው፤›› ሲል ገልጿል፡፡

የምርጫ ሕጉ ከሚፈቅደው 200 አባላት ፊርማ በላይ 220 አባላት ፊርማን በማሟላትና ጊዜያዊ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋን መርጠው፣ ሰኞ ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅድመ ዕውቅና እንዲሰጣቸው ማስገባታቸውን አቶ ስንታየሁ አስረድቷል፡፡

የፓርቲውን ደንብና ፕሮግራም አዘጋጅተው በአዋጁ መሠረት በሦስት ወራት ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ እየተዘጋጁ መሆኑንና በሦስት የተከፈለ ኮሚቴ እያዘጋጁ መሆኑንም አክሏል፡፡

የፖለቲካ ድርጅት (ፓርቲ) እንዲመሠርቱ የገፋፋቸው ሕዝቡ መሆኑን የገለጸው ደግሞ አዲስ የተመሠረተው ፓርቲ ጊዜያዊ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ ነው፡፡ በዕለቱ ለጋዜጠኞች በመድረኩ ላይ ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ዴሞክራሲ እንደተፈጠረና ዋናው ተግባራቸው በሥልጣን ላይ ያለውን አዲስ አመራር መደገፍ መሆኑን ገልጸው፣ ሕዝቡ አማራጭ ያስፈልገዋል ብለው ቢገፋፏቸውም ጥርጣሬ እንደነበራቸው ተናግሯል፡፡ ጥርጣሬውም እውነት መሆኑንና ኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ዴሞክራሲ ገና በእግሩ አለመቆሙን ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

የመሠረቱት ፓርቲም ይህንኑ የሚያረጋግጥ መሆኑን አክሎ፣ ሕጋዊ ነገሮችን አሟልተው የመጀመርያ ስብሰባቸውን ለማድረግ ለኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል 90,000 ብር የከፈሉ ቢሆንም፣ ሆቴሉ ሳይሆን መንግሥት እንደከለከላቸው እስክንድር ገልጿል፡፡ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ደውለው ያሳወቁ ቢሆንም፣ እሳቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ደውለው ሲጠይቁ፣ ‹‹የምናውቀው ነገር የለም›› የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ገልጿል፡፡

የኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወገኔ ማቴዎስን ለምን ክፍያ ከተፈጸመ በኋላ እነ አቶ እስክንድር እንደተከለከሉ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ክፍያው መፈጸሙን አረጋግጠው፣ ቀድመው ተመራቂ ተማሪዎች ከጎናቸው አደራሽ ይዘው ስለነበር ይረብሻቸዋል ብለው በማሰብ በሌላ ጊዜ እንዲያደርጉ እንደ ነገሯቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከፈለጉ ሰሞኑን ወይም በፈለጉት ጊዜ ማድረግ፤›› ይችላሉ ብለዋል፡፡ አቶ እስክንድር ሳይሆን፣ አቶ ስንታየሁ ለ200 ሰዎች ስብሰባ እንዳለ እንጂ የፓርቲ መሆኑን እንዳልነገራቸው አክለዋል፡፡ የከለከሏቸውም የሆቴሉ የፀጥታ ሠራተኞች እንጂ የመንግሥት አካላት እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...