Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግንባታቸው የተቋረጠ 15 ሺሕ ያህል የግል ሕንፃዎች በአንድ ወር መፍትሔ እንደሚያገኙ ቃል ተገባ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሀብቶች ከብድር ዕጦት እስከ መንግሥት ባለሥልጣናት ምሬት ያሉባቸውን ችግሮች ተናገሩ

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በአዲስ አበባ በግለሰብ አልሚዎች ተጀምረው በተለያዩ ችግሮች ግንባታቸው የተቋረጡ ከአሥር ሺሕ እስከ 15 ሺሕ ያህል ሕንፃዎች እንዲጠናቀቁ፣ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥም ለችግሮቻቸው ዕልባት እንደሚሰጣቸው ቃል ገቡ፡፡

ምክትል ከንቲባው በከተማው ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የግንባታ ተዋንያንኑን ባነጋገሩበት ወቅት እንዳሉት፣ አስተዳደራቸው ቅድሚያ በሰጣቸውና ከፍተኛ ችግር ታይቶባቸዋል ባላቸው በቦሌ፣ በቂርቆስና በአራዳ ክፍላተ ከተሞች ውስጥ የተጓተቱ ግንባታዎችን በአካል በመጎብኘት ችግራቸውን እዚያው የግንባታው ቦታ ላይ በመገኘት ይፈታላቸዋል፡፡  

ከንቲባው ይህንን ያስታወቁት፣ በግንባታው መስክ የሚታዩ ችግሮች ላይ ለመነሻ ጥናት ተደርጎ የአብዛኛው ግለሰብ ገንቢዎችና አልሚዎች ችግሮች ላይ መፍትሔ ለመስጠት በተጠራው ስብሰባ ወቅት ነበር፡፡ እሑድ ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው ስብሰባ በርካቶች የገጠሟቸውን ችግሮች አሰምተው ነበር፡፡

የውጭ ምንዛሪ ዕጦት፣ የግብዓት ጥራት ችግርና የዋጋ ንረት፣ የሊዝ አሠራርና የመሬት አሰጣጥ ችግሮች፣ ለግንባታ የተቀመጠው ጊዜ በእጅጉ ማጠርና መሰል ችግሮች ተነስተዋል፡፡ ‹‹ባንኮች አላበድር እያሉ ነው፤›› ያሉ አንድ ባለሀብት፣ ወሎ ሠፈር አካባቢ ባለ 19 ፎቅ ሕንፃ በመገንባት 95 በመቶ አጠናቀው፣ በባንክም ከ75 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ እያላቸው ብድር ማጣታቸውን፣ ይባስ ብሎም 200 ሺሕ ብር ማውጣት እንዳልቻሉ ጭምር ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ27 በመቶ አስገዳጅ የቦንድ ግዥ መመርያን ከባንኮች ላይ ቢያነሳም፣ ባንኮች ግን የገንዘብ አቅርቦት እንዳለባቸው መግለጻቸውም ተወስቷል፡፡

ይህ ብቻም ሳይሆን ባንኮች የወለድ ቅናሽ አለማድረጋቸውም ትዝብት ላይ እንደሚጥላቸው አስተያየት ሰጪዎቹ ሳይጠቁሙ አላላፉም፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት ጀምሮ የኤልሲ ጥያቄ አቅርበው ሊስተናገዱ እንዳልቻሉ የገለጹ አስተያየት ሰጪ፣ ከሁሉ በላይ ግን ባንኮች ብድር አልሰጥ ማለታቸው በእጅጉ ከንክኗቸዋል፡፡ ‹‹ዶላሩስ እሺ የለም ይባል፡፡ ብሩ የት ሄዶ ነው ብድር የለም የሚሉን?›› በማለት ጥያቄ ያቀረቡት ባለሀብቱ በአንድ በኩል ገንዘብ የለም እየተባሉ፣ በሌላ በኩል ግን ግንባታ በጊዜ አላጠናቀቃችሁም እየተባሉ ለቅጣትና ለማስጠንቀቂያ መዳረጋቸውን በምሬት አውስተዋል፡፡

በሊዝ የተገዛ መሬት ላይ በየጊዜው ማሻሻያ ስለተደረገ ክፈሉ የሚል ማስታወቂያ በግንባታ ቦታ እየተለጠፈባቸው መቸገራቸውን የተናገሩት እኚህ ባለሀብት፣ በከተማው አብዛኛው የሕንፃ ግንባታ እየቆመ ያለው በተለይ በባንክ ብድር ዕጦት፣ በመንግሥት ቢሮክራሲና የአሠራር ችግር ሳቢያ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ሌሎችም በተመሳሳይ አስረድተዋል፡፡

ከባንኮች ጋር በተያያዘ ለተነሱ ቅሬታዎች ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ባንኮች ፕሬዚዳንትና የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ፣ የውጭ ምንዛሪ ዕጦት የአገር ችግር ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት ከዚህ ቀደም በተለየ ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፕሮጀክቶች ላይ መከተል በጀመረው ጥብቅ የቁጥጥር ፖሊሲ ሳቢያ ገንዘብ ከመልቀቅ መቆጠቡን፣ ከፍተኛ ግብር እየሰበሰበ በሚገኝበት ወቅት እንኳ ገንዘቡ መልሶ ወደ ገበያ እንዳይገባ ማድረጉ የፈጠረው የአጭር ጊዜ የገንዘብ እጥረት በመኖሩ እንጂ፣ ባንኮች ማበደር ሳይፈልጉ ቀርተው እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ንግድ ባንኮች ከሚያመነጩት የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶውን ቀንሶ እንደሚይዘው የገለጹት አቶ አቤ፣ አሁን ወደ አገሪቱ እየገባ ካለው የውጭ ምንዛሪ አኳያ ቢያንስ ይህ የ30 በመቶ ተቀናሽ አሠራር እንዲነሳ ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እየገባ ካለው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ባንኮችም እንዲደርሳቸው እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

የባንኮች የብድር ማስከፈያ ወለድ በቅርቡ እየተሻሻለ እንደሚሄድ የጠቀሱት አቶ አቤ፣ ባንኮች ካበደሩት ገንዘብ ውስጥ 25 በመቶው በብሔራዊ ባንክ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ፣ እጅ ስላጠራቸው እንጂ ማበደር ዋናው ሥራቸው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ባለሀብቶችም ቢሆኑ የገነቡትን ሕንፃ ለማከራየት የሚያስከፍሉት ገንዘብ የባንኮችን ወጪ እያናረው ይህን ለማካካስ ወለድ እንደሚጨምሩ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡  

አብዛኞቹ የውይይቱ ተሳታፊዎች በየፊናቸው ስለገጠሟቸው ነባርና አዳዲስ ችግሮች አቤቱታ አሰምተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ለአቤቱታ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በመሄድ መፍትሔ ለማግኘት ቢጣጣሩም፣ ከንቲባውን ማግኘት ‹‹የሰማይ ቤት›› ያህል እንደ ራቃቸው ለምክትል ከንቲባው ገልጸውላቸዋል፡፡ እሳቸውም ለእያንዳንዱ አቤቱታ ምላሽ መስጠት እንደሚቸግራቸው፣ ከተማዋ ለድሆችም መኖሪያነቷን ለማረጋገጥ ችግር ላይ የወደቁ፣ ዞር ብሎ የሚያያቸው ያጡ ትምህርት ቤቶችንና አቅመ ደካሞችን በመደገፍና በመንከባከብ ሥራ ላይ ማተኮሩን፣ ቢሮ ተቀምጦ እያንዳንዱን ባለሀብት ለማነጋገር የሚበቃ ጊዜ አለመኖሩንና ጊዜውም ቢኖር እንኳ ሁሉንም ጥያቄ ከንቲባ እንደማይፈታው ለጠያቂዎቹ ገልጸውላቸዋል፡፡

የተንዛዛው ቢሮክራሲ ያሰለቻቸው ጠያቂዎች ላነሱት ቅሬታ ምክትል ከንቲባው ምላሽ ተጠይቀው ነበር፡፡ ‹‹ጆተኒ ታውቃላችሁ?›› በማለት ምላሽ መስጠት የጀመሩት ምክትል ከንቲባ ታከለ፣ ‹‹ጆተኒ ሳንቲም ካልገባበት ኳሷን አይሰጥም፡፡ እናተን ገንዘብ ባትሰጡ የመንግሥት ኃላፊዎችም አያስቸግሩም ነበር፤›› በማለት ባለሀብቱና ባለሥልጣናቱ በንፅህና ከመሥራት ይልቅ በአገም ጠቀም መያያዛቸው ችግር እንደፈጠረ አስታውቀዋል፡፡

‹‹የባለሥልጣናት ኔትወርክ ከባድና አደጋ ነበር፡፡ ይህንን መበጣጠስ ከባድ ነበር፤›› ያሉት ምክትል ከንቲባው፣ በዚህ መነሻነት አስተዳደራቸው እጅ እግሩ የማይለይ የተወሳሰቡ ሥራዎችን መረከቡን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ሁሉ ችግር እያቃለለ እንደሚገኝ፣ በአሁኑ ወቅት በግለሰቦች የተጀመሩ ሕንፃዎችን መንግሥት እየያዘ በጋራ ችግሮችን እየተከታተለ መፍትሔ የሚሰጥ አካል መዋቀሩን አስታውቀዋል፡፡ መንግሥትና ባለሀብቱን በማሳተፍ የሚንቀሳቀስ ትልቅ ተቋም አስተዳደራቸው ማደራጀቱን፣ ይህ ተቋም ማን እንደሆነ በስም ባይገልጹትም፣ በሥራው ግን የግንባታ ጥንስስ ከሚጀመርበት ጀምሮ እስከሚያበቃበት ደረጃ ድረስ የሚመራና የሚከታተል ተቋም ስለመሆኑ ለማብራራት ሞክረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በአራዳ፣ በቂርቆስና በቦሌ ክፍላተ ከተሞችን የሕንፃ ግንባታ ችግሮች የሚፈታ ቡድን ተዋቅሮ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በመንቀሳቀስ በየግንባታ ቦታዎች እየተዘዋወረ የአልሚዎቹን ችግር እንደሚፈታ ቃል በመግባት ስብሰባውን ቋጭተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች