Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበታሪካዊ ሥፍራ ጭቃ ማቡካት

በታሪካዊ ሥፍራ ጭቃ ማቡካት

ቀን:

በሔለን ተስፋዬ

የብዙ ሰዎች ትውስታ (ትዝታ) እንደሆነ ከተሰበሰቡት ሰዎች ዓይናቸው ላይ ይነበባል፡፡ በተዘጋጀላቸው ንጣፍ በመቀመጫቸው ዘርፈጥ ብለው ልባቸው የፈለገውን መሥራቱን ተያይዘውታል፡፡

በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት በሸክላ ጭቃ ገሚሱ፣ ጀበና፣ ድስትና ሳህን ለመሥራት ማቡኳኳቱን ቀጥለዋል፡፡ በዕድሜ ትልቅ ነኝ ብሎ ያፈገፈገ አንድም ሰው የለም፡፡ ይልቅ ቦታ ሳይሞላ ጠደፍ ጠደፍ እያሉ ወደ ተዘጋጀው የሸክላ መሥሪያ ቦታ ብዙዎች ይጎርፋሉ፡፡

አዋቂው ትዝታውን ከውስጥ ፈንቅሎ ያወጣለት ቦታ እንደሆነለት ከሳቃቸውና ከደስታቸው ማወቅ ያስችላል፡፡ ‹‹እማዬ ድስት፣ የሻይ ብርጭቆ ሥራ እኔ ደግሞ እንደዚህ እሠራለሁ፤›› የሚሉም ሕፃናት ፓርኩ ይቁጠራቸው፡፡ በሕፃናቱ ላይ ያለው ደስታ ግን ወደር እንደሌለው በገጻቸው ላይ ፍንትው ብሏል፡፡ አብዛኛው ሕፃናት ለመጀመርያ ጊዜ በጭቃ የሚሠሩት በመሆኑ የሚሠሩትን ለማየት ቀረብ አልኩ፡፡ አንዷ ሕፃን የምትሠራው ግራ ቢገባኝ ቀረብ ብዬ፣ ‹‹ሚጣ ምን እየሠራሽ ነው?›› ስላት፡፡ ቀና ብላ አየት አርጋኝ፣ ‹‹በርገር እየሠራሁ ነው፤›› አለችኝ፡፡ እርሷ ምታውቀው ምግብ የሚሠራበትን ሊጥ እንጂ ጭቃ ማን ቦታው ላይ አስደርሷት ልታውቅ ትችላለች፡፡

ለነገሩ ጭቃ ሊጫወቱበት ቀርቶ የሚቦርቁበት ቦታ በሌለበት አብዛኛው መንደሮች ውስጥ ለሕፃናት ተብሎ የሚተው ቦታ ባለመኖሩ በመሞከር እልኻቸውን የሚወጡ ነው የሚመስሉ ሕፃናት አሸን ናቸው፡፡ ምናልባት የመዲናዪቱ በቀደምት ዘመናት ጭቃውን አቡክተው፣ ጀበና፣ ስኒ፣ ድስትና የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች ሠርተው ካሳለፉት ውጭ በአሁኑ ዘመን ላሉ የማይታሰብ ነውና፡፡

ምናልባት በተለያዩ የክልል ከተሞች የሚኖሩ ሕፃናትና ታዳጊዎች ዕድሉን ሊያገኙ ይችሉ ይሆናል እንጂ በሸገር ይህንን ለማድረግ የታደሉ ሕፃናት አሉ ለማለት አያስደፍርም፡፡ በጭቃ የራሳቸውን መጫወቻ ለመሥራት ንፁህ አፈርን፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ ለማግኘት አዳጋች ከሆነ ሰንበት ብሏል፡፡ የሕፃናት መጫወቻ ቦታዎች ቢኖሩም እንኳን፣ ለሕፃናቱ ባህላቸውን የሚያሳይ ወይም ቀደምት አባቶች የራሳቸውን መጫወቻ እንዴት እንደሚያበጁ የሚያሳይ ነገር በመዲናዪቱ ታይቶ አይታወቅም፡፡

የአሁን ትውልድ ጭቃ አቡክተው፣ የራሳቸውን ቅርፃ ቅርፅ ሠርተውና ቀደምቱ እንዴት የልጅነት ጊዜያቸውን እንዳሳለፉ ይታወስ ዘንድ ‹‹ኑ ጭቃ እናቡካ›› መርሐ ግበር መሰናዳት ከጀመረ ጊዜያት ተቆጥረዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ራስን የመምራት አቅምና ጥበብ ከልጅነታቸው እንዲማሩ ይህ ባህል ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሎ በመታመኑ የተሰናዳ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡

ይህንን ታሳቢ በማድረግ ጥር 2 ቀን 2012 ‹‹ኑ ጭቃ እናቡካ›› መርሐ ግብር በታላቁ ቤተ መንግሥት በሚገኘው በአንድነት ፓርክ ተካሂዷል፡፡

በፓርኩ በተለያዩ ስያሜ ተከፋፍሎና እንደየ አካባቢ እንቅስቃሴ አራት ኪሎ፣ ሸማ ተራ፣ ቡሄ፣ ምን አለሽ ተራ፣ ፖስታ ቤትና አራዳ በሚል ተከፋፍሎ ከሕፃን እስከ አዋቂ ሲያሳልፍ ቆይቷል፡፡

ሸማ ተራ እናቶች ያልተፈተለ ጥጥ የሚፈትሉ፣ ተፈትሎ ያለቀለት ጥጥ ይዘው እንዝርት የሚያሾሩ፣ እናቶቹን በመመልከት እነርሱም የእንዝርት አያያዝና ጥጥ አፈታተል ሙያ ለመቅሰም ሕፃናቱ ሰብሰብ ብለዋል፡፡ በሸማ ተራ በተሰየመው ቦታ የሚገኙ ሰዎች መፍተል፣ እንዝርት ማሾርን ሳይሞክሩ አላለፉም ማለት ይቻላል፡፡ በብዙዎች የፊት ገጽ ላይ የናፈቁት ባህልና ማንነትን እጅግ የተጠሙ መሆናቸውን ቁጭ ብለው ከእናቶች ትምህርት ለመቅሰም መጓጓታቸውን ያሳብቅባቸዋል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ‹‹ኧረ ይኼማ አያቅተኝም፤›› ብለው ሲዳክሩና ለመልመድ የሚደርጉት ሙከራ ቢሳካም ባይሳካም መፍጨርጨራቸውን ቀጥለዋል፡፡

በአራት ኪሎ ስያሜ የተከፈተው ቦታ ሕፃናቱ የራሳቸው ሐሳብ በሥዕል እንዲያስቀምጡ የተደረገ ሲሆን፣ በጃንሜዳ ስያሜ ደግሞ የቴዘር ኳስ እንዲጫወቱ፣ በፖስታ ቤት ስያሜ ከተለያዩ የወረቀቶችና ፕላስቲኮች በመጠቀም የእጅ ጌጣጌጦች፣ በወደቁ ፕላስቲክ ማንኪያዎች ላይ ሥዕል እየሣሉ፣ ያላቸውን ተሰጥዖ በፈለጉት መንገድ የሚገልጹበት መድረክ ተመቻችቶላቸዋል፡፡

የሸክላ ሥራ ለመሥራት እጅግ አድካሚና ትዕግሥት የሚጠይቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሙያው በጥቂት ሰዎች እጅ ብቻ ስለሚገኝ፣ ሕፃናቱ ዝንባሌያቸው እንዲያሳድጉና የባህል ሥራ እንዲያውቁ የሚያግዝ መርሐ ግብር ነው፡፡

በሰባት ዓመታት በሸክላ ሥራ የተሰማራችው ወጣት ሰላም፣ በኑ ጭቃ እናቡካ መርሐ ግብር ሙያዋን ለማካፈል ከተገኙት መካከል ትገኝበታለች፡፡ ሰላም በትዕግሥት ለሕፃናቱና ለወላጆቻቸው እንዴት ሸክላ ሥራ እንደሚሠራ በማሳየት ጊዜዋን አሳልፋለች፡፡  

በኑ ጭቃ እናቡካ ተሳታፊ የነበሩ ወጣቶች በተለይም ገጽ ቅብ ወይም የፊት ቅብ (ፌስ ፔንቲንግ) የውጭ አገሮች ባህል (መጤ) የሚመስላቸው ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ በደቡብ ኦሞና አካባቢዋ ላይ ያሉ ማኅበረሰብ ግን ባህላቸውና የማንነታቸው መገለጫ እንደሆነ ለማሳየት መቅረባቸውን ወጣቶቹ ነግረውናል፡፡

 ብዙ ሕፃናትና ወላጆች የተሳተፉበት ኑ ጭቃ እናቡካ መርሐ ግብር በአንድነት ፓርክ መሆኑ ይበልጥ ሳቢና ሕፃናቱ የአገራቸውን ታሪክና ትውፊት እንዲያውቁ እንደሚያግዛቸው በዕለቱ ተካፋይ የነበሩ ወላጆች ነግረውናል፡፡

ከሦስት ቁጥር ማዞሪያ የመጣችው ወላጅ እንደተናገረችው፣ የአሁኑ ትውልድ የሸክላ ሥራን ጨምሮ የተለያዩ አገራዊና መገልገያ ነገሮችን አይቶ ስለማያውቅ ፕሮግራሙ ለማሳየት ያግዛል ብላለች፡፡ የኑ ጭቃ እናቡካ መርሐ ግብር ፓርኩ ላይ መሆኑ አገራዊ ታሪኮችን ከእነትውፊታቸውና ቀደምት ወላጆች መጫወቻዎች እንዴት እንደሚሠሩ ለሕፃናት ለማሳየት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ያነጋገርናቸው ወላጆች ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ለመጀመርያ ጊዜ እየተሳተፍኩኝ ነው የሚሉት አንድ ወላጅ፣ አይደለም ለልጆቹ ለእኔም ደስታ፣ አለፍ ብሎም ትዝታዬንና ያሳለፍኩትን የልጅነት ጊዜ እንድቃኝ ረድቶኛል ይላሉ፡፡

ጥጥ መፍተል እየሞከረች ያገኛት ወጣት ለመጀመርያ ጊዜ እንደተሳተፈች እንዲሁም የአገራችን ባህል፣ የባህል አልባሳት የሚሠራበት ጥሬ ዕቃ፣ አባቶቻችን እንዴት እንደተጫወቱ መልሰን ወደ ራሳችን እንድንመለከት ያግዘናል ብላለች፡፡

በዚህ መርሐ ግብር ልጆች ማንነታቸውን ከማወቅ ባሻገር፣ የፈጠራ ክህሎቶቻቸውን እንዲያውቁ ይረዳቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ‹‹በአንድነት ፓርክ ከልጆቻችን ጋር መጥተው ጥንት የነበረውን ታሪክ ማየታቸው አለፍ ሲልም በዚህ ታሪካዊ ቦታ እንደፈለጉ እንዲቦርቁና ታሪካቸውን እንዲያውቁ መደረጉ ለልጆች የማያልፍ ትዝታ እንዲኖራቸው ያደርጋል፤›› የሚል አስተያየት ከተለያዩ ወላጆች ተደምጧል፡፡

ለሦስተኛ ጊዜ የተሰናዳውና ሕፃናትን ማዕከል ያደረገው የ‹‹ኑ ጭቃ እናቡካ›› መርሐ ግብር ልጆች ባህላቸውንና ትውፊታቸው አውቀው እንዲያድጉ ትልቅ አሻራ ይጥላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሠዓሊት ሐመረ ሙሉጌታ አዘጋጅነት የሚካሄደው ‹‹ኑ ጭቃ እናቡካ›› ዝግጅት በቀጣይ ልጆች ማንነታቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ባህላቸውን እንዲያውቁ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የሕፃናቱ ወላጆች ሳይነግሩን አላለፉም፡፡  

መርሐ ግብሩ በሌላ ጊዜና ቦታ ከዚህ በተሻለ አቀራረብ ብሎም አገራዊ ባህልን የሚያሳውቅ ነገሮችን ታክሎበት በአራተኛ ዙር እንደሚቀርብ ተነግሯል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...