ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ ባደረጉት ጉብኝት ከኢትዮጵያውያን ጋር በነበራቸው ውይይት ካደረጉት ንግግር የተወሰደ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያውያኑ ባደረጉት ንግግር በርካታ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ሁሌም በሕይወታችን ከሚገጥሙን ጭቆናዎች ራሳችንን ነፃ ስናወጣ ከውስጣችን የጭቆናውን ሐሳብ አራግፈን መጣል ይገባናል። ከአስከፊ ሥርዓት ስንላቀቅ አስከፊውን ሥርዓት ከውስጣችን ጠራርገን ማፅዳት አለብን። ጥላቻን ከዙሪያችን ገለል ከማድረግ ባለፈ ከልባችን ፍቀን መጣል ይኖርብናል። ከክፉ ነገር ውስጥ ለመውጣት የምናደርገውን ትግል ያህል ክፉውን ነገር ከውስጣችን ለማውጣት ትግል ካላደረግን አሸናፊነታችን ትርጉም አይኖረውም። የማንዴላ የማሸነፍ ሚስጥርም ይኼው ነው። ልክ እንደ ማንዴላ ሁሉ በውጭ ያለውን ጠላት ከማሸነፋችን በፊት፣ በውስጣችን ያለውን ጥላቻና ቂም ማሸነፍ ይቀድማል። አለበለዚያ ጠላታችንን ያሸነፍን ቢመስለን እንኳን፣ የጥላቻ ሐሳቡን በውስጣችን እስከ ተሸከምነው ድረስ ተሸናፊዎች እኛ ነን፤›› ብለዋል።