Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየኢራን በስህተት የመታችው አውሮፕላን መዘዝ

የኢራን በስህተት የመታችው አውሮፕላን መዘዝ

ቀን:

በዩክሬን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ የሚተዳደረው ቦይንግ 737 አውሮፕላን የቴህራን ዓለም አቀፍ ኤርፖርትን ለቆ በተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከዕይታ (ከራዳር) ጠፋ፡፡ ወደ ዩክሬን በማቅናት ላይ የነበረው ይህ አውሮፕላን ከአፍታ በኋላ 176 መንገደኞችና የአየር መንገዱን ሠራተኞች ይዞ የመከስከሱ ዜና ተሰማ፡፡

በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡት 82 ኢራናውያን፣ 63 ካናዳውያን፣ 11 ዩክሬናውያን፣ 10 ስዊዲናውያን፣ አራት አፍጋን፣ ሦስት የጀርመን፣ ሦስት የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው 167 መንገደኞች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ዘጠኝ ተጎጂዎች የአየር መንገዱ ሠራተኞች ናቸው፡፡ በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች በሰማይ ላይ እሳትና የተቃጠሉ የአውሮፕላኑን ክፍሎች ማየታቸውን፣ መስክ ላይ እንዴት እንደተበታተነም መመልከታቸውን ቃል ሰጥተዋል፡፡

አውሮፕላኑ ረቡዕ ታኅሣስ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ፓራንድና ሻህራር በተባሉ የኢራን ከተሞች መካከል መከስከሱ ሲገለጽ የአደጋው ምክንያት ገና አልታወቀም ነበር፡፡ የአደጋው መንስዔ ይሆናሉ የተባሉ የተለያዩ መላምቶች ሲወጡ ነበር፡፡

ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተል የነበረው የኢራን ሚዲያ አደጋው የደረሰው በአውሮፕላኑ የቴክኒክ ችግር ሊሆን እንደሚችል ሲገልጽ፣ በዩክሬን በኩል ደግሞ አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በሮኬት ጥቃት እንደሚሆን አስተያየት ይሰጥ ጀመር፡፡ የአደጋው ምክንያት በትክክል ሳይረጋገጥ ግምታቸውን ከመስጠት የተቆጠቡ የሁለቱ አገሮች ባለሥልጣናት ግን የምርመራ ውጤቱ ይፋ እስኪሆን መጠበቅን መረጡ፡፡

የአውሮፕላኑ የመከስከስ ዜና የተሰማው ኢራን በኢራቅ በሚገኙ የአሜሪካ የወታደሮች ካምፕ ላይ የሮኬት ጥቃት በፈጸመች በሰዓታት ልዩነት ውስጥ መሆኑ አጋጣሚ ተብሎ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም የሚሉም የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ነበር፡፡

የኢራን በስህተት የመታችው አውሮፕላን መዘዝ

 

የአውሮፕላኑ አብራሪ ካፕቴን ቮሎድሚሪ ጋፓኔንኮ ቦይንግ 737 አውሮፕላንን ለ11,600 ሰዓታት ያበረረ ልምድ ያለው መሆኑን፣ ኢንስትራክተር ፓይለቱ አሌክሲ ናውምኪንም እንዲሁ 12,000 ሰዓታት የበረራ ልምድ ያካበተ መሆኑን በመግለጽ፣ አደጋው ከሙያ ብቃት ጋር እንደማይያያዝ የሚገልጹ መረጃዎች ሲለቀቁም ነበር፡፡ የዩክሬን ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ፕሬዚዳንት ዩቬኒ ዳይከንም፣ ‹‹ከበረራ ሠራተኞቹ በኩል ምንም ዓይነት ስህተት ሊኖር አይችልም፤›› ብለው ነበር፡፡ በዩክሬን ከተማ ኬይቭ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም የቴህራን ኤርፖርት፣ ‹‹ቀላል ኤርፖርት አይደለም፡፡ ፓይለቶቹም የዓመታት ልምድ ያካበቱ ናቸው፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዲ 138ቱ ከዩክሬን ወደ ካናዳ ይሄዱ የነበሩ የትራንዚት መንገደኞች እንደነበሩ፣ እነዚህን መንገደኞች ያጓጉዝ የነበረው አውሮፕላን ቶሮንቶ ሲደርስ አብዛኛው ወንበሮቹ ክፍት እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

የዓለምን ትኩረት ስቦ የሰነበተው ይህ አደጋ በአሜሪካና በኢራን መካከል የነበረውን ውጥረት መልኩን እንዲቀይር አድርጓል፡፡ ዓርብ ታኅሣሥ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢራን ብሔራዊ ጀግና የሚባሉት የኢራን ሌተና ጄኔራል ቃሲም ሱሌማኒ በአሜሪካ በመገደላቸው የተቆጡ ኢራናውያን ብቻ ሳይሆኑ አውሮፓውያንም ጭምር ናቸው፡፡ በአሜሪካ ጎን እንደምትሠለፍ እርግጥ የሆነችው ኢራቅ እንኳ የአሜሪካን ዕርምጃ በግልጽ ተቃውማለች፡፡

የአንድን አገር ሉዓላዊነት መግፈፍ የተባለው የቃሲም ሱሌማኒ ግድያ አብዛኞቹ የተደሰቱበት አልነበረም፡፡ ጄኔራሉ ለአሜሪካ ተኝተው የማያድሩ ነበሩ የሚሏቸው እንኳ ዕርምጃው የባሰ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል በመግለጽ አግባብነት እንደሌለው ሲገልጹ ነበር፡፡ ለሦስተኛው የዓለም ጦርነት መነሻ ሊሆን እንደሚችል የሠጉም በየሚዲያው አስተያየት ሲሰጡ ነበር፡፡

አሜሪካን ለማጥቃት በዝግጅት ላይ ሳሉ ነው የቀደምናቸው የሚሉት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ኢራን የአፀፋ ዕርምጃ የምትወስድ ከሆነ ዋጋ እንደምትከፍል ሲያስፈራሩ፣ ታሪካዊ የኢራን ቦታዎችን ጨምሮ በ52 የተመረጡ ሥፍራዎች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ሲያስፈራሩ ደግሞ ቁጣው ጠንክሮ ነበር፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ዓለም ለኢራን እንዲያደላ ባደረገበት በዚህ ወሳኝ ወቅት 176 መንገደኞችን የያዘው የዩክሬን አውሮፕላን ኢራን ላይ መከስከሱ አገሪቱን ጥያቄ ውስጥ ከቶ ነበር የሰነበተው፡፡

ሁለቱን አደጋዎች የሚያያዝ አንድም ነገር መኖሩ ከመጣራቱ በፊት አንዳች የፖለቲካ ቁማር ስለመኖሩ ሲወራ ነበር፡፡ በአውሮፕላኑ ስለደረሰው አደጋ ወሳኝ መረጃ የሚገኝበት ‹‹ብላክ ቦክስ› እንደተገኘ፣ የኢራን ባለሥልጣናት በምንም ዓይነት ለቦይንግ ኩባንያ አሳልፈን አንሰጥም አሉ፡፡ ጥቂት ካንገራገሩ በኋላ የኢራን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አባስ ሙሳቪ በትዊተር ገጻቸው የአውሮፕላኑ አምራች ቦይንግ የምርመራ ቡድኑን እንዲቀላቀል መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተወከሉበት የምርመራ ቡድኑ ውጤት ግን የኢራን ቅዠት ነበር፡፡

ኢራን ቦይንግ 737-800 አውሮፕላንን በስህተት መምጣቷን አመነች፡፡ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ በተፈጠረው አደጋ መፀፀታቸውንና ማዘናቸውን ገልጸው፣ በአደጋው ወላጆቻቸውን ላጡ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተው፣ ይቅርታም ጠይቀዋል፡፡

የኢራን በስህተት የመታችው አውሮፕላን መዘዝ

 

ይህንን ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን በንፁኃን ላይ የደረሰውን አደጋ በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል፡፡ የ176 ሰዎችን ሕይወት ለቀጠፈው የአውሮፕላን አደጋ ባለሥልጣናቱን አውግዘዋል፡፡ ‹‹ጠላታችን እናንተ ናችሁ!›› እያሉ የኢራን መሪዎች ከሥልጣን እንዲወርዱ ጠይቀዋል፡፡ ጄኔራል ቃሲም ሱሌማኒ በተገደሉ ማግሥት የነበረው የኢራናውያን ቁጣ ወደ መሪዎቻቸው መቀልበሱንም ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው፡፡

‹‹ጠላታችን አሜሪካ ነች እያሉ እየዋሹን ነው፡፡ ጠላቶቻችን እዚሁ ናቸው ያሉት፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ቅዳሜ ጥር 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በተቀሰቀሰው የሕዝብ ተቃውሞ፣ ‹‹ሞት ለአምባገነን!›› እያሉ የኢራን ታላቁ የእስልምና መሪ አያቶላህ ዓሊ አክመኒን ስም ሲጠሩ ነበር፡፡ እንዲህ በሚሉበት ጊዜም በአስለቃሽ ጭስ መመታታቸው ተሰምቷል፡፡ በርካታ ፖሊሶችና ወታደሮች ተቃውሞ በተስፋፋባቸው በዋና ከተማዋ ቴህራን ተሠራጭተዋል፡፡ ተቃዋሚዎቹ በተለየ በቫሊ ኢአሥር አደባባይና በዩኒቨርሲቲ ካምፓሶች በመሰባሰብ ቁጣቸውን እየገለጹ ነው፡፡  

176 መንገደኞችን ይዞ በቴህራን የተከሰከሰው ቦይንግ 737 – 800 አውሮፕላን ከራዳር ከመጥፋቱ በፊት 8,000 ጫማ ከፍታ ላይ ወጥቶ ነበር፡፡ አውሮፕላኑ መብረር በጀመረ በሦስት ደቂቃዎች ውስጥ መከስከሱ እየተነገረ ነው፡፡ አውሮፕላኑ ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...