Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ባንክ በአንድ ጊዜ ሦስት ወለድ አልባ ቅርንጫፎችን ሥራ አስጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓመቱ 20 ቅርንጫፎች እንደሚከፍት አስታውቋል

ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን ለብቻቸው በሚሰጡ ቅርንጫፎች ለማቅረብ ከሚንቀሳቀሱ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው አዋሽ ባንክ፣ በዚህ ዓመት ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎቹን 20 እንደሚያደርስ አስታወቀ፡፡ ሦስት ወለድ አልባ ቅርጫፎቹን በአንድ ጊዜ አገልግሎት አስጀምሯል፡፡

ባንኩ ወለድ አልባ አገልግሎቱን ራሳቸውን በቻሉና ለዚሁ ሥራ ብቻ በሚንቀሳቀሱ ቅርንጫፎች አማካይነት አገልግሎቶቹን ለማቅረብ በያዘው ዕቅድ መሠረት ማክሰኞ፣ ጥር 5 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ሦስት ቅርንጫፎችን በይፋ ሲያስጀምር እንዳስታወቀው፣ በሒሳብ ዓመቱ የሚከፈቱትን ወለድ አልባ ቅርንጫፎች ብዛት 20 ለማድረስ ሲያቅድ፣ በቅርቡ ይህን አሠራር ሥራ ለማስጀመር ዝግጅት አድርጓል፡፡ ሥራ ያስጀመራቸው ሦስቱ ቅርንጫፎች በቦሌ ሚካኤል፣ በሰባተኛና በበርበሬ ተራ አካባቢ የተከፈቱት ናቸው፡፡

የእነዚህ ቅርንጫፎች ሥራ መጀመርን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው፣ አዋሽ ባንክ ወለድ አልባ አገልግሎቱን ለሁሉም ተጠቃሚዎች ለማድረስ ዕቅድ እንደነበረውና በአሁኑ ወቅት በሚያስተዳድራቸው ከ430 በላይ በሆኑት ቅርንጫፎቹ በሁሉም በኩል ወለድ አልባ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ  ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ በየጊዜውም አዳዲስ አገልግሎቶችንና አሠራሮችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ሲናገሩም፣ በተለመደው የባንኮች አሠራር መሠረት በወለድ ማስቀመጥና በወለድ መበደር የማይፈልጉ ደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካት ከሁለት ዓመታት በፊት በ15 ቅርንጫፎች ብቻ ሲያቀርብ የነበረውን ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት፣ በአሁኑ ወቅት በሁሉም ቅርንጫፎቹ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

አገልግሎቱን ከእስካሁኑም በተሻለ መንገድ ለማቅረብ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎቱን ከአንድ መስኮት ይልቅ ራሱን በቻለ ቅርጫፍ ለመስጠት ሰፊ ዝግጅት በማድረግ የመጀመርያውን ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት መስጫ ቅርንጫፍ ኅዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በመክፈት ሥራ እንዳስጀመረ ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል፡፡ አሁን ደግሞ ሦስቱን ቅርንጫፎች በአንድ ላይ በመክፈት አግልግሎት እንዳስጀመረም ገልጸዋል፡፡

ይህንን አገልግሎትን በማስፋፋት በተያዘው ዓመት ውስጥ አሁን ያሉትን አራት ቅርንጫፎች ወደ 20 ለማሳደግ እየሠራ እንደሚገኝ ለሪፖርተር የገለጹት አቶ ፀሐይ፣ ከዚህ ውስጥ አሥሩ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡

ባንኩ ወለድ አልባ የባንክ ቅርንጫፎቹን ከሚከፍትባቸው ከተሞች ውስጥ ጅማ፣ ባሌ ሮቤ፣ ነቀምት፣ ደሴ፣ ድሬዳዋና ሐላባ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እንደ አቶ ፀሐይ ገለጻ፣ እስካሁን በየቅርንጫፎቹ በመስኮት ሲሰጥ በቆየው የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት አማካይነት ከ180 ሺሕ በላይ ደንበኞች ማፍራት ተችሏል፡፡

ከእነዚህ ደንበኞች ከ3.3 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ተችሏል፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ የሸሪዓ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ የሚተገበር ሲሆን፣ ለተለያዩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች የሚውል ብድር አዋሽ ባንክ እያቀረበ እንደሚገኝም ተጠቅሷል፡፡  

ከባንኩ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ እስካሁን በሸሪዓ ሕግ መሠረት በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎቱ በኩል 700 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለተለያዩ የንግድ ዘርፎች በብድር መልክ ቀርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች