Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፕሪሚየም ስዊች ትርፉ ከአሥር ሚሊዮን ብር ወደ ግማሽ ሚሊዮን ብር አሽቆለቆለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ስድስት የግል ባንኮችን በአባልነት ያካተተውና ዘመናዊ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎትን ለመስጠት የተቋቋመው ፕሪሚየር ስዊች ሶሉሽንስ (ፒኤስኤስ)፣ ባለፈው ዓመት ካስመዘገበው የአሥር ሚሊዮን ብር አሽቆልቁሎ 498 ሺሕ ብር መድረሱ ታወቀ፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንቱም የአገልግሎት ዋጋ ቅናሽ ማድረጉ መሆኑ ታውቋል፡፡ ኩባንያው በ2011 ዓ.ም. አጠቃላይ ገቢው 44 ሚሊዮን ብር የነበረ ቢሆንም፣ በ2010 ዓ.ም. ካስመዘገበው አኳያ በ9.2 ሚሊዮን ብር ያነሰ ገቢ ሆኖበታል፡፡

 ተቋሙ ባለፉት ሰባት ዓመታት በጠቅላላው ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ክፍያዎችን ሲያስተናግድ፣ በኤቲኤም አማካይነት ብዛታቸው 29.4 ሚሊዮን ክፍያዎችን ስለማከናወኑም አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ዓመታዊ ትርፉ ግን ቀንሷል፡፡ ኩባንያው የ2011 ዓ.ም. ክንውኑን ይፋ ባደረገበት ወቅት እንደተመለከተው፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ያስተናገደው የክፍያ አገልግሎት ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በጠቅላላው ካስተናገዳቸው ግብይቶች አንፃር የ27 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡

የዲጂታል ክፍያ አገልግሎቶችን በቀላሉ በማቅረብ ባንኮችንና ደንበኞቻቸውን ለማዘመን እንዲችል ታስቦ የተቋቋመው ፕሪሚየር ስዊች ሶሉሽንስ፣ ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ዕድገት እንዳስመዝገበ ያስታወቁት የድርጅቱ ቦርድ ሰብሳቢና የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው ናቸው፡፡ ድርጅቱ ሥራ ከጀመረ ዘንድሮ ሰባተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ አቶ ፀሐይ እንዳሉት፣ ፕሪሚየር ስዊች የተጋረጡበትን ፈተናዎች በማለፍ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት በኢትዮጵያ እንዲሳለጥ የድርሻውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

ፕሪሚየም ስዊች 409,316 የክፍያ ካርዶችን በማሳተም ለአባል ባንኮች ማሠራጨቱን የጠቀሱት አቶ ፀሐይ፣ ይህ ቁጥር ኩባንያው ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለገበያ ያቀረባቸውን ካርዶች ብዛት ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ለማድረስ አስችሎታል ብለዋል፡፡ ከካቻምና ክንዋኔው አኳያ፣ የሰባት በመቶ ዕድገት ያስመዘገበበት ውጤት ላይ እንደደረሰም  የቦርድ ሰብሳቢው ያቀረቡት ሪፖርት ያትታል፡፡ በ2011 ዓ.ም. በጠቅላላው 8.8 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡና ብዛታቸው 10.75 ሚሊዮን የገንዘብ ክፍያ ግብይቶችን በኢቲኤም አማካይነት አስተናዷል፡፡ በኤቲኤም አማካይነት ክፍያ የተፈጸመባቸው ግብይቶች ከካቻምና አንፃር ሲታዩ የ34 በመቶ ዕድገት ተመዝግቦባቸዋል፡፡ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውና ብዛታቸው 1.2 ሚሊዮን ግብይቶች የተፈጸሙትም በፒኤስኤስ አባል ባንኮች መካከል እንደሆነ ጠቅሷል፡፡  

በሞባይል ስልኮች አማካይነት በሚሰጡ ትዕዛዞችን ለመፈጸም፣ ገንዘብ የማውጣትና የካርድ አልባ ግብይቶች እንቅስቃሴ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ በተያዘው ሒሳብ ዓመት ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው 10,455 ግብይቶች ተከናውነዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም. የሽያጭ መዳረሻ የክፍያ ማሽኖችን በመጠቀም በአባል ባንኮችና በዓለም አቀፍ የክፍያ ካርዶች አማካይነት 406 ሚሊዮን ብር ያስመዘገቡ የ93,794 ግብይቶችን ፒኤስኤስ አስተናግዷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 87 በመቶው ዓለም አቀፍ ካርዶችን በመጠቀም የተከናወኑ ሲሆኑ፣ በእነዚህ ክፍያዎች የተመዘገበው ውጤት ከ2010 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ108 በመቶ ዕድገት እንደታየበት ድርጅቱ ይፋ አድርጓል፡፡

በአገሪቱ የክፍያ መቀበያ ማሽኖችን በመጠቀም የሚደረጉ ግብይቶች በዝቅተኛ ደረጃ ቢገኙም፣ ሁሉም አባል ባንኮች የፖስ ማሽኖችን በመጠቀም የሚከናውኗቸውን ክፍያዎች ለማሻሻል የሚያስችል ሥራ መሥራት እንደሚገባ የቦርድ ሊቀመንበሩ አሳስበዋል፡፡   

የክፍያ መቀበያ ማሽኖችን በመጠቀም 257 ሚሊዮን ብር ያስዘመገቡና 69,562 ያህል የገንዘብ ማውጣት አገልግሎቶች ለደንበኞች መቅረባቸው በ2011 ዓ.ም. ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል የቀረበው ክንውን ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ94 በመቶ በላይ የሚሆኑት የፕሪሚየም ስዊች ካርዶችን በመጠቀም እንደተከናወኑ ተጠቅሷል፡፡ የክፍያ መቀበያ ማሽን በመጠቀም የተከናወኑ የገንዘብ ማውጣት ክንውኖች ከካቻምናው ጋር ሲነፃፀሩ ትልቅ የሚባል ዕድገት ታይቶባቸዋል፡፡  

ከዚህ ባሻገር በ2011 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ የክፍያ ካርዶች አማካይነት በኤቲኤምና በክፍያ መቀበያ ማሽን በኩል የተስተናገዱ ግብይቶች ብዛት ከ195,000 በላይ የደረሱ ሲሆን፣ ዋጋቸውም ከ21 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡  

ፕሪሚየም ስዊች በጥሪ ማዕከሉ አማካይነት በ2011 ዓ.ም. 113,790 ጥሪዎችን በማስተናገድ በአባል ባንኮች በኩል ለቀረቡና ከዲጂታል ክፍያዎች ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎችና ችግሮች መፍትሔ መስጠቱንም አስታውቋል፡፡ የጥሪ ማዕከሉ ሳምንቱን በሙሉ በዕለቱ ለ24 ሰዓታት አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ ሁሉም አባል ባንኮችና ደንበኞች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉን ድርጅቱ ገልጿል፡፡  

የዓለም አቀፍ ክፍያ ካርዶች ማኅበራት ያስቀመጡትን ግዴታዎች ለመወጣት የዓለም አቀፍ የክፍያ ምክር ቤት ባስቀመጠው መሥፈርት መሠረት ፕሪሚየም ስዊች የሚጠበቅበትን ዓለም አቀፍ የኦዲት ግዴታና ሥርዓት ውጤታማ በማድረግና በስኬት በማጠናቀቅ ለአምስተኛ ጊዜ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘቱንም አስታውቋል፡፡ ይህም በድርጅቱ የክፍያ መረብ በኩል የሚተላለፉና በማጠራቀሚያ ቋቱ የሚከማቹ የካርድ መረጃዎች በማንኛውም መንገድ ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ፣ በደንበኞቹም ዘንድ መተማመንን እንደፈጠረለት የቦርድ ሰብሳቢው አስታውቀዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም. ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ትግበራ አኳያ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውም በሪፖርት ቀርቧል፡፡ ከእነዚህ መካከል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን የማስፋት፣ የማጠናከርና የማዘመን ሥራዎች ስለመከናወናቸው ተጠቅሷል፡፡  

ዓምና በተደረገ እንቅስቃሴ 109 ተጨማሪ ኤቲኤም ማሽኖች፣ 334 የሽያጭ መዳረሻ የክፍያ ማሽኖች ከድርጅቱ የመረጃ ሥርዓት ጋር እንዲገናኙና አገልግሎት እንዲሰጡ በመደረጋቸው፣ በአጠቃላይ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የኤቲኤም ማሽኖች ብዛት 712፣ የክፍያ መቀበያ ማሽኖች ብዛት 1,304 እንደደረሰ ተጠቅሷል፡፡ በ2011 ዓ.ም. ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል የማስተር ካርድ ኩባንያን ማስተናገድ የሚችሉ የኤቲኤምና የክፍያ መቀበያ ማሽኖችን የሚያስተናግዱ ባንኮች ብዛት ወደ አራት ከፍ ማደረጋቸውም ተመልክቷል፡፡

ካቻምና ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የሚጠቀሰው ሌላው አፈጻጸም፣  የፕሪሚየም ስዊች አባል ባንኮች ተወዳዳሪ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለደንበኞቻቸው እንዲሰጡ ለማስቻል ሲባል የአገልግሎት ክፍያ በሁሉም የአገልግሎት ዘርፎች ከ30 እስከ 40 በመቶ ቅናሽ መደረጉ ነው፡፡

ፕሪሚየም ስዊች ሶሉሽንስ አዋሽ ባንክ፣ ንብ ባንክ፣ ኅብረት ባንክ፣ ብርሃን ባንክ፣ አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክና የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የመሠረቱት ተቋመ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉ 150 ሚሊዮን ብር ገደማ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች