ሰላም! ሰላም! እናንተዬ ዝም ብላችሁ ብቻ ሕይወትን ታዘቡዋት እስኪ? አቤት የቅርጿ ብዛቱ። አንዳንዱ እኔ ነኝ ያለ ዝግ ሲዘጋ አንዳንዱ በቆመበት እያንቀላፋ ያዛጋል። አንዳንዱ ሰምሮለት በድሎት ሲሰክር ሌላው በጠራራ ፀሐይ መሀል መንገድ ላይ ወድቆ የዕርዳታ ያለህ እያለ ሲማፀን ይውላል። ስንት ዓይነት ስቃይ፣ ስንት ዓይነት ደስታ፣ ስንት ዓይነት መከፋት በሕይወት ብራና ላይ ተጽፎ ስናነብ እንውላለን መሰላችሁ? ተፈጥሮ አያልቅባት፣ የእኛም ፍላጎት አያልቅ፤ የመኖር ፍሰት ሳይስተጓጎል ይኼው አለን። በዚህ መሀል ቁጭ ብለን የምንሰማው ደግሞ ጉድ ነው። እኔ የምለው ጉድ አላልቅ ሲል ገንዘብ እያለቀብን መቸገራችን ለምን ይሆን? አንድ ቀን ምሁሩን የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ቆይ ግን የገንዘብ ኖት ከምን ይሆን የሚሠራው?›› ብዬ ጠየቅኩት። ‹‹ከላይነንና ከጥጥ ነው። ምነው በደህናህ ነው የጠየቅከኝ?›› አለኝ መልሶ። መልስ ፍለጋ ስንጠይቅ ምላሹ ጥያቄ ከሆነ አለቀልን!
አይገርማችሁም ግን፣ ‘በደህናህ ነው የጠየቅከኝ’ ማለት? ሰው እንዲህ ያለ ጥያቄ ለምን ብሎ ይጠይቃል ለማወቅ ካልሆነ? ለነገሩ አትፍረዱበት። በዚህ ጊዜ ለማወቅ ሳይሆን ለመታወቅ የሚከንፈው መብዛቱን ታዝቦ ሊሆን ይችላል። እናም ሁላችንም ታዋቂ ሆነን ማን አድናቂ ሊሆንልን እንደሆነ እንጃ። ‹‹ወይ ዘንድሮ. . .›› አለ ዘፋኙ ስል ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ያስቀኛል ገንፎ ከምሳዬ ተርፎ›› አለ የድሮ ሰው ይለኛል፡፡ መቼም ከአዛውንቱ ባሻዬ ጋር መዋል ሳላስበው የተረት ሊቅ አድርጎኝ አረፈው። ለነገሩ የሀብት እንጂ የተረት ችግርማ የለብንም፡፡ ዕድገታችንስ ‹‹ተረት. . . ተረት. . . ›› ብሎ አይደል የሚጀምረው? ዕድገት ስላችሁ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ፡፡ ዓለም በቴክኖሎጂ ዘምኖ የትና የት ተጉዞ እኛ ግን የሰውን ዘር እንደ እህል ዘር በቁና መስፈራችን ይገርመኛል፡፡ ምርጫችን ራሱ ነጠላ ጉዳይ ላይ በማተኮር የምናማትረው ከዘራችን ለማማረጥ እንጂ፣ ለሰብዕና ቅድሚያ በመስጠት ‹ከእንጨት መርጦ ለታቦት ከሰው መርጦ ለሹመት› የሚለውን ዘንግተነዋል፡፡ ወይ እኛና ዘመናችን!
የባሻዬን ልጅ ጥያቄ አልረሳሁትም፡፡ ትንሽ ትክዝ ብዬ ቆየሁና ‹‹አይመስለኝም!›› አልኩት ኮስተር ብዬ። ‹‹እውነት የዘንድሮ ረብጣ ገንዘብ ከውርጭና ከቅዝቃዜ አይደለም የሚሠራው? ብን ባለ ቁጥር ጉብታ ላይ እንደ ወጣን ኩርምት ስንል እኮ ነው የምንውለው። እኔማ አንዳንዴ (መቼም የፀሐይዋን አናት ሰርሳሪነት በየዕለቱ የማይቀምስ የለም) ርቃን በሚያስኬድ ግለት ራስ ዳሸን አናት ላይ የወጣ ቱሪስት የሆንኩ ይመስለኛል፤›› ስለው የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንበርብር ትንሽ አላካበድከውም?›› አለኝ በሹፈት መልክ። ይኼ አጉል ገለጻና ፍልስፍና የመሰለው ቢመስለኝ፣ ‹‹ከፈለግክ ከዚህ ቀጥሎ የማስቀምጠውን መሥፈርት መጠቀም ትችላለህ። ማንም ሰው ደህና ረብጣ እጁ ቆጥሮለት ኪሱ ከገባ በኋላ ተመልሶ ባዶ የሚሆነው በስንት ቀን ውስጥ ነው?›› ስለው፣ ‹‹ኧረ እባክህ ስለፈጠረህ ተወው በቃ። ልክ እንደ ተመራማሪ የሆነ ተዓምር የምትቀምር መስለህ ይኼንን የተለመደ የማወራረጃ ሥልት ትነግረኛለህ?›› አለኝ። አልገባውማ! እንዴ እሱ ራሱ እንዳጫወተኝ ከሆነ የዋጋ ግሽበት ገንዘባችንን ገለባ ወይም አረፋ አድርጎታል፡፡ ለዋጋ ግሽበቱ ምክንያት ቢደረደርም እንዴት ይውረድ በሚባለው ላይ እኔ ነኝ ያለ ምሁር ጠፍቷል፡፡ የዘንድሮ ምሁር መጨበጪያ የሌለው ወሬ ላይ ተጥዶ ቁምነገሩን የት ያውቀዋል!
በነገራችን ላይ ባሻዬ ሁሌም ቢሆን ስለትልልቅ የትምህርት ተቋማት አንስተን ስንጫወት፣ በሐዘኔታና በመቆርቆር የሚያወሩኝ ስለተማሪዎች ዕውቀት ማነስ ነው፡፡ አንዳንዴማ እየገረመኝ፣ ‹‹ባሻዬ አይተውታል እንዴ?›› እላቸዋለሁ። ብሶታቸው ‘መቼስ ምን ይደረግ?’ ብሎ ዝም ከሚለው ተማሪ ሲበረታብኝ፣ አንድ ቀን ግን ልቤ እስኪፈርስ የሚያስቅ አስተያየት ሲናገሩ ብሰማ በእጅጉ አስገረሙኝ። ምን አሉኝ መሰላችሁ? ‹‹አንበርብር ተማሪ የነገ የዚህች አገር መሪና ተረካቢ ዜጋ ነው። ያውም በዕውቀት ደርጅቶ ዝግጁ ሲሆን። እናም በአግባቡ ዕውቀት ሳይጨብጥና ሳያሰላስል የሚመረቅ ከሆነ ደግ ነው?›› አሉኝ፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹ቢያንስ ትምህርቱን የሚጨርስበትን አራት ወይም ሦስት ዓመት በሚገባ እየተኮተኮተ ቢበቃ አገሩን እንዲህ አያስቸግርም ነበር፤›› አይሉኝ መሰላችሁ? እሳቸው እንደሚሉት ጥራዝ ነጠቅ ሆኖ አገር የሚበጠብጠው ትምህርቱ የተቃወሰበት ወይም የተበደለ ነው፡፡ ‹‹አንበርብር በሚገባ የተማረ አገሩንና ሕዝቡን አይበድልም፤›› ሲሉ በበኩሌ የዓመቱ ኮከብ ንግግር ብዬ አደነቅኳቸው። ምነው ግን በየሙያው ዓመታዊ ሽልማትና የኮከብ ምርጫ ጨርሶ ጠፋ? በአንድ የመንግሥት የልማት ድርጅት ውስጥ ነው አሉ፡፡ ሠራተኞች በዳተኝነት የሚያውቁት አንድ ነፈዝ ‹ኮከብ ሠራተኛ› ተብሎ ሲሸለም ዓይናቸውን ማመን ያቃታቸው ሰዎች፣ ‹ኮከብነቱ በማንቀላፋት ነው ወይስ በሥራ?› ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ድርጊቱ ያበሳጫቸው ደግሞ፣ ‹ኮከብነቱ የዋና ሥራ አስኪያጁን ሴት ልጅ በማፍቀሩ ነው፤› ሲሉ የሠራተኞቹ ሳቅ ፓርላማ ድረስ ተሰማ አሉ፡፡ አሉ ነው ያልኩት፡፡ በዚህ ዘመን አሉ እኮ ነው አንደኛ የሚያደርገው!
በጨዋታችን መሀል ከላይ የተጠቀሰው ነገር ትዝ ብሎኝ ፈገግ ማለቴን ያየው የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንበርብር ጤናም አይደለህ?›› አለኝ መልሶ። ይኼ ሰውዬ ምን ሆኗል ብዬ፣ ‹‹የገንዘብ ኖት የሚሠራው ከምንድን ነው ብዬ ስጠይቅህ በደህና ነው የጠየቅከኝ ማለትህ እጅግ ከንክኖኛል። ተጠያቂነትና ግልጽነትን በአንፃራዊነት እኛ ለመንግሥትና ለፖለቲከኞች እንዲህ ካላስተማርን መፈክሩ ብቻ እንደማይለውጥ እያየን ያለን ይመስለኛል፤›› እያለ ሳቀብኝ፡፡ እንደ ባህር አውሎ ንፋስ የፖለቲካው ወጀብ ጠራርጎ እንዳይወስደን መላ ብንፈልግስ? ‹‹አይ አንበርብር?›› እያለ ሳቁን አልጨርስ ሲለኝ ‹‹ምንድነው የሚያስቅህ?›› ብዬ ኮስተር አልኩ። ‹‹አንተም ዕድሜህ እየጨመረ ሲሄድ ሥልጣን አማረህ መሰለኝ፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ይኼኔ የእውነቴን ኮስተር አልኩና በደንብ እንዲያብራራልኝ ጠየቅኩት። ዘንድሮ እኮ አንዳንዱን አነጋገር ካልበለታችሁትና ፍሬ ሐሳቡን ተፈራርማችሁ ካልያዛችሁት መዘዙ ብዙ እየሆነ ነው። ለምን? መዘዘኛው ብዙ ስለሆነ ነዋ! ሌላ እኮ አይደለም። ስናድግ እንኳ ትዝ ካላችሁ ‘አንተ ልጅ አርፈህ ተቀመጥ መዘዝ እንዳታመጣብኝ’ እየተባልን ነበር። እናም ጣጠኞችና መዘዘኞች በበዙበት በዚህ ዘመን ግን ጠንከር ማለት ያስፈልጋል፡፡ ያልጠነከረ ይመነጠራል ማለት ነው!
ምሁሩ የባሻዬ ልጅም፣ ‹‹እዚህ አገር የታዘብኩት ነገር ቢኖር ትንሽ እናውቃለን የሚሉ ሰዎች ታዋቂነት ሲያጠግባቸውና ሁሉንም ነገር ሲያስረሳቸው፣ ከእኛ በላይ ይህችን አገር ለመምራት የሚችል ሰው የለም ብለው ያስባሉ። አንተን እንኳ እንዲያው ለጨዋታ ያህል ነው እንዲያ ያልኩህ። ግን ታዝበህ ከሆነ ጥቃቅን የፖለቲካ ርዕሰ ጉዳይ እየመረጡ ራሳቸውን ከሰው በላይ ሲክቡ የሚውሉ እየበዙ ነው፤›› ሲለኝ ምን እንዳሰብኩ ታውቃላችሁ? ከፖለቲካ በላይ አገር የለችም ወይ? ሰውስ ስለአገሩ አስቦ ሲያበቃ ጥቃቅን ነው ብሎ የሚተወው የፖለቲካ ርዕሰ ጉዳይ ይኖራል ወይ? ወዘተ. የሚል ሐሳብ ነው። ሆኖም ነገሩ ማጠሪያ እንደሌለው ሳስብ ቋንቋው ሳያግባባን እንደቀረ ተረዳሁ። ወይ ሰውና ቋንቋው? እንዲያው ካስተዋላችሁ አብዛኞቻችን እያደርን በጉራማይሌ መኮላተፍ ዋና ተግባራችን ሆኗል። ክፍት የሥራ ቦታ ያለው እሱ ብቻ መሰለ እኮ? ለተማረውም ላልተማረውም ማለቴ ነው። ያልተማረውማ ኮብልስቶን አለለት፡፡ ተማረ የሚባለው ባይሻማው? አንድ የኪራይ ቤት ፈላጊ ሰሞኑን የኮንዶሚኒየም ቤት እንዳፈላልግለት አደራ አለኝ። አገኘሁለትና ከአከራዩ ጋር አገናኘኋቸው። ያልሰማ ይስማ! ባለ አንድ መኝታ የሚባለው እስከ 10,000 ብር እየተከራየላችሁ ነው። አቤት መጨካከን! በዚህ በጣም የተበሳጨው ተከራይ አከራዩን፣ ‹‹ምነው አልበዛም? ፈጣሪ ይወደዋል?›› ቢለው፣ አከራዩ እየተለጠጠ ‹‹ቴክ ኢት ኢዚ›› ሲለው ጎረበጠኝ፡፡ የሰው ጨጓራ እየላጡ ማላገጥ!
እና ምን ልላችሁ ነው? ስለአንዳንድ የቃላት አጠቃቀማችን ግልጽ ምልከታና ዕይታ የሚያስጨብጠንን ስያሜ መፍጠር ያቃተን መስለናል። አሁን ትዝ ያለኝ የባሻዬ ልጅ፣ ‘ጥቃቅንና አነስተኛ የፖለቲካ ጉዳዮች’ የሚለውን ቢሆንም ሁሌም የማስበው ነገር ነው። ስንቱን ጥቃቅን ሐሳብ እያልነው አይደለም እንዴ ትልቅ ችግር እየሆነ ዛሬ ዕፎይታ ያሳጣን? ተውት እሱን። ስንቶችን በሥራቸው ጥቃቅንና አነስተኛ አድርገናቸው አይደለም እንዴ ዛሬ በሚሊዮን ሲቆጥሩ የምናየው? ታዲያ ይህ ከሆነ ያውም በአገር ጉዳይ እንዴት ጥቃቅን የሚባል ነገር ይኖራል? ከልጅነቱ ጀምሮ ይታሰብበት የምንለው ነገር ሁሉ ዛሬ እየሸመገለ ሲያስቸግረን መድረሻ ጠፋን። እግረ መንገዴን ይኼ ከትንሽ ሥራ ጀምሮ ሠርቶ ለመለወጥ የማሰብ ነገር እጅጉን እየጨመረ ሲመጣ እንደታዘብኩት አጫውቻችኋለሁ? ኑሮ ባይከብደን ኖሮ ለእንዲህ ያለው ለውጥ ቆሞ መዘመር ይጠበቅብን ነበር። ኑሮና መዝሙርን ደግሞ ምን ያገናኛቸዋል? ብትሉኝ አንድ ሚስጥር ሹክ እላችኋለሁ። ሳስበው ሳስበው ወደፊት በዚህ ከቀጠለ በአገራችን ብሔራዊ መዝሙራችን የሚዘመረው ፓርላማ፣ ትምህርት ቤት፣ ስታዲየም፣ ወዘተ. ብቻ ይመስለኛል። ለምን አትሉኝም? አንድ አገር እያለን ሌላ ተጨማሪ አገር እያለምን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታችን ምን ዓይነት የአገር ፍቅር ይቀጣጠላል? አልሰማችሁም? ኢትዮጵያዊ የነበረ በዲቪ አሜሪካ ገብቶ የአሜሪካ ብሔራዊ መዝሙር ግጥም ቢያጠና አይገርምም። የሚገርመው ግጥሙ መሀል ኢትዮጵያን የሚረግም ስንኝ ሲያስገባ ነው፡፡ ወይ ዲቪና ኢትዮጵያዊ? እንሳቅ እንጂ ምን ይደረጋል!
እንዴት ነው ግን ዲቪ እየሞላችሁ ነው? አንዳንዱን ዲቪው ራሱ ሲሞላው ስታዩ ይገርማችኋል፡፡ ምን ማለት መሰላችሁ? አንዳንዱ ተገዶና ምርጫ አጥቶ ቢሳካልኝ ብሎ ነው የሚሞላው። በነገራችን ላይ ስንቱ አልፎለት የወገኑን ሕይወት እንዳላሳለፈም ታዝበናል። የማንጠግቦሽ ቡና አጣጭ የነበሩ ጎረቤቷ ለዚህ ምሳሌ ናቸው። ምን ዋጋ አለው? ልጃቸው አሜሪካ ሲገባ እሳቸው እዚሁ ቁጭ ብለው ከልጁ በላይ ራቁን። ምን ይሆን ጉዳዩ ብለን ብንጠይቅ ልጅ እናቱን አይረዳ ታመው ተኝተው ይሰቃያሉ፡፡ አብዛኞቻችን በማይረባ ነገር ወገን እየረሳን ባያልፍልን ይገርማል እላለሁ። አንዳንዱ ደግሞ እዚያ ሄዶ ወልዶ ልጁን አሜሪካዊ ለማድረግ ዲቪ ይሞላል። የእናንተን ባላውቅም እኔ ግን በፋሺስት ጣሊያን ወረራ የወደቁት ወገኖቼ አጥንት ሲወጋኝ ይሰማኛል። ለምን ያ ሁሉ መስዋትነት ተከፈለ? ለምን ያ ሁሉ ደም ፈሰሰ? ዛሬስ በዚህ አሳፋሪ ወዶ ተገዥ መንፈስ የያኔው ድል በአገር ደረጃ ለምን ይከበራል? የሚለውን ሳስብ ምኑም አይገባኝም። ጥሩ ትምህርት ለማስተማር ሲባል ከሆነ መልካም፡፡ ዜግነትን መለወጥና ኢትዮጵያዊነቱን መፋቅ ለምን ያስፈልጋል? እኔ ይቅርታ አድርጉልኝና ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ይህን ያደርጋል አልልም። አገር ተጠልታና በአሳፋሪነት ተመስላ የት ይደረሳል? በአስተሳሰብና በአኗኗር እሻላለሁ የሚለው የኅብረተሰብ ክፍል ይህን ሲያደርግ ከእሱ አነስ ለሚለው ምን እያስተማረው ነው? ጎበዝ ይኼ እኮ ራሱን የቻለ የጋራ ነቀርሳ ነው! እኔ በበኩሌ የሚሰማኝ ይኼ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በግድ የሚያገኙት፣ ተመቸ ተብሎ ደግሞ እንደ ጃኬት የሚያወልቁት አይደለም፡፡ ይልቁንስ ሌላውን ትቶ በርትቶ በመማር ለእናት አገር መድረስ፡፡ አሜሪካ የበለፀገችው በልጆቿ መስዋዕትነት እንጂ በግል ጥቅም አሯሯጮች አይደለም፡፡ አሜሪካ መሽጋችሁ አገር ለማፍረስ የምትከጅሉ ተጠንቀቁ ለማለት ነው!
በሉ እንሰነባበት። አንድ አልሸጥ ብሎ የከረመ ሚኒባስ አሻሽጬ ካገኘሁት ኮሚሽን አንድ ሁለት ማለት አማረኝና ስንዳረቅ ከዋልነው የባሻዬ ልጅ ጋር ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ሄድን። የምንፈልገውን አዘን እየጠበቅን ሳለን፣ ‹‹አንበርብር ዲቪ ትሞላለህ እንዴ?›› ብሎ ድንገት ጠየቀኝ። ‹‹የለም!›› አልኩት እንደማኩረፍ ብዬ። ‹‹ለምን?›› አለኝ። ‹‹ኧረ ተወኝ እባክህ የተከበርኩ ደላላ ነኝ። በእርግጥ የምማስነውን ያህል የማገኘው አይጠቅመኝም። ነገር ግን ከዚህ በኋላ ሰው አገር ሄጄ የማላውቀው አሠሪ አገልጋይ ከምሆን የአገሬን ሕዝብ ዝቅ ብዬ አላገለግልም?›› ስለው ዝም አለ። ኋላ የዜግነትን ጉዳይ ሳጫውተው፣ ‹‹እኔን የሚያሳስበኝ ይኼ አይደለም፤›› አለኝ፡፡ ከዜግነት በላይ ምን የገዘፈ ጉዳይ ይኖራል በማለት፣ ‹‹ምን ያሳስብሃል?›› አልኩት፡፡ ‹‹አንበርብር አሜሪካ እየኖርክ ዜግነት ማግኘት ለበርካታ ጉዳዮች ስለሚያገለግል መውሰድ ችግር የለበትም፤›› ብሎኝ፣ ‹‹እኔን የሚያሳስበኝ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር አሜሪካ ካሉ ወገኖቻችን ስንጠብቅ፣ የጥላቻና የዘረኝነት ፕሮፓጋንዳ መብዛቱ ነው፤›› ሲል አባባሉ ገባኝ፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ግንዛቤዬ ያጠበብኩትን እሱ በገዘፈ ዕውቀቱ አሰፋው፡፡ ታላቂቷ አሜሪካ ውስጥ እየኖሩ አለመማር ያበሳጫል፡፡ ወገኖቼ ከሐሜት፣ ከአሉባልታ፣ ከተራ ወሬና ከጥላቻ ተላቀው ይማሩ ዘንድ ተመኘሁ፡፡ የታላቋን አሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፉክክር ዜና ስሰማ በእጅጉ እቀናለሁ፡፡ ምናለ እንደ ኦባማ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ለዚያ ቦታ ቢደርስ እላለሁ፡፡ ከሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል ብዙዎቹ ቢማሩና ለቁምነገር ቢበቁ እኮ አሜሪካን የሚመራ አንድ ብርቱ ሰው አይጠፋም ነበር፡፡ ወገኖቼ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እያሰብን የራሳችንን መጪ ምርጫ እናሰላስል፡፡ የአሜሪካ ዓይነቱ እውነተኛ ምርጫ የሚካሄደው የሰው ልጆች ነፃነትና መብት በሚገባ በመከበሩ ነው፡፡ እኛም እርስ በርስ ተከባብረን ሰው እንምሰል፡፡ እስቲ እኛም ይመርብን፡፡ በአሜሪካ ምርጫ ያልተቀና በምን ይቀና ይሆን? መልካም ሰንበት!