Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሰኔ 15 ከፍተኛ የክልልና የፌዴራል ባለሥልጣናት ግድያ ተጠርጣሪ ተከሳሾች ክርክራቸው በፕላዝማ ሊሆን...

የሰኔ 15 ከፍተኛ የክልልና የፌዴራል ባለሥልጣናት ግድያ ተጠርጣሪ ተከሳሾች ክርክራቸው በፕላዝማ ሊሆን ነው

ቀን:

የችሎት ታዳሚዎች ቁጥር እንዲቀንስ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን አስታውቋል

የአማራ ክልል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በሦስት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና በአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምና በጓደኛቸው ግድያ ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው 13 ተጠርጣሪዎች ጉዳይ፣ በፕላዝማ እንደሚካሄድ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሽብርና በሕገ መንግሥት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት ዓርብ ጥር 8 ቀን 2012 ዓ.ም. የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ በፕላዝማ እንደሚተላለፍ ያስታወቀው፣ ተጠርጣሪዎቹ ወደ ችሎት ‹‹አንገባም›› በማለት ከማረሚያ ቤት ይዟቸው ከመጣው አውቶቡስ ላይ ‹‹አንወርድም›› በማለታቸው ነው፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ምክንያት ደግሞ ቤተሰቦቻቸውና ደጋፊዎቻቸው እንዳይገቡ በመባሉ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ በሌሉበት በመሰየም የጄኔራል ሰዓረ መኮንን ልዩ ጠባቂ የነበረውና ከተከሳሾቹ አንዱ የሆነው አሥር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ክስ መሻሻሉን ጠይቆ እንደተሻሻለ ከተረዳና የተሻሻለውን ክስ ከተቀበለ በኋላ፣ ቀደም ባለው ችሎት የሰጣቸውን ትዕዛዞች ስለመፈጸማቸው ጠይቋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦቻቸውንና ጠያቂዎቻቸውን በተመለከተ ባቀረቡት አቤቱታ፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ተወካይ ረዳት ኦፊሰር ድሪባ ሰንበታ ቀርበው አስረድተዋል፡፡ ኦፊሰሩ ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡት አቤቱታ ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል፡፡ ጠያቂዎቻቸው እንደ ማንኛውም እስረኛ ቤተሰብ ወይም ጠያቂ እየጠየቋቸው መሆኑን፣ ጠያቂዎች ከእነ ሙሉ አድራሻቸው ስለሚመዘገቡ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን አስቀርቦ መመልከት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳልተፈጸመም አክለዋል፡፡

ረዳት ኦፊሰር ድሪባ ጨምረው እንዳስረዱት፣ ለተጠርጣሪዎች ዘርንና ሃይማኖትን ከፍ ዝቅ ከሚያደርጉ መጻሕፍት በስተቀር ሌሎች መጻሕፍት እየገቡላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎች ከአንድ ዞን ወደ ሌላኛው ዞን ሲዘዋወሩ እንደ ማንኛውም ተጠርጣሪ ከመፈተሽ በስተቀር፣ ምንም ዓይነት ሳንሱር እንደማይደረግባቸውም አክለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በኤግዚቢት ያስያዙትን የሞባይል ስልክና ሌሎች ማስረጃዎችን በሚመለከትም፣ የፌዴራል ፖሊስ ምላሹን በጽሑፍ አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ምላሽ ከሰማ በኋላ፣ የተጠርጣሪዎች ቤተሰብ ወይም ችሎት ታዳሚ እንዲቀንስ ያደረገው ራሱ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ጉዳዩ መታየት ያለበት በግልጽ ችሎት ቢሆንም፣ ባለፈው የችሎት ውሎ ፍርድ ቤቱ ውስጥ ረብሻ መፈጠሩን አስታውሷል፡፡ እንዲያውም ከዚህ በኋላ ክርክሩ በፕላዝማ እንደሚሆን ሲያስታውቅ የተጠርጣሪዎች ጠበቆች አቤቱታ እንዳላቸው ቢናገሩም፣ ሳይቀበል ትዕዛዝ በመስጠት በማረሚያ ቤትና በፌዴራል ፖሊስ በቀረበው ምላሽ ላይ ብይን ለመስጠትና የ12 ተጠርጣሪዎችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ለየካቲት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በችሎት የተገኙ ጋዜጠኞች ከየትኛው የመገናኛ ብዙኃን እንደመጡ ከተመዘገቡ በኋላ፣ የችሎቱን ትክክለኛ መጠርያ አስተካክለው እንዲጽፉና ቀደም ባለው ዘገባቸው ላይ ሲዘግቡ ስህተት የፈጸሙ ቢሆንም መታለፋቸውን፣ ነገር ግን ወደፊት አስተካክለው እንዲዘግቡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...