Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ የተቆጠሩ 29 ምስክሮች...

በእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ የተቆጠሩ 29 ምስክሮች ጉዳይ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ተባለ

ቀን:

የዓቃቤ ሕግ ጥያቄ ሕገ መንግሥቱን የጣሰ መሆኑ ተመላክቷል

በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን (በሌሉበት) ጨምሮ 26 ተከሳሾች ላይ፣ ዓቃቤ ሕግ አካላቸው ሳይታይ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ምስክርነት እንዲሰጡለት የቆጠራቸው 29 ምስክሮች ጉዳይ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የሚጥስ በመሆኑ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ተባለ፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 4 (1ሸ እና በ) መሠረት ስማቸውን ሳይጠቅስ የቆጠራቸው 29 ምስክሮች፣ ማንነታቸው እንዳይገለጽና ምስክርነት ሲሰጡም በአካል ሳይታዩ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ የአዋጁን አንቀጽ 23 (1፣ 2ሀ እና ለ)ን ጠቅሶ ፍርድ ቤቱን መጠየቁ ይታወሳል፡፡

ተከሳሾቹ ባቀረቡት መቃወሚያ ደግሞ የዓቃቤ ሕግ ጥያቄ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(1) ማለትም፣ ‹‹የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመሰማት መብት አላቸው፡፡ የተከራካሪዎቹን የግል ሕይወት፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታና የአገሪቱን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ክርክሩ በዝግ ችሎት ሊሰማ ይችላል፤›› የሚለውን ድንጋጌ ይቃረናል ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡

ፍርድ ቤቱም ዓቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 4 መሠረት የቆጠራቸው 29 ምስክሮች በአካል ሳይታዩ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ወይም ማንነታቸውን በመሸፈን ምስክርነት እንዲሰጡ ማድረግ መቻል አለመቻሉን፣ ከላይ የተጠቀሰውን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(1) ድንጋጌንና ኢትዮጵያ ፈርማ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቃል ኪዳን ሰነድ (UDHR) አንቀጽ 11(1)፣ ‹‹በወንጀል የተከሰሰ ማንኛውም ሰው ጥፋተኛ ሆኖ እስከሚረጋገጥ ድረስ ንፁህ ሆኖ የመገመት መብት እንዳለውና ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) አንቀጽ 14(1) የተከሰሱ ሰዎች ነፃና ገለልተኛ በሆነ ፍርድ ቤትና ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመዳኘት መብት ያላቸው መሆኑ የሚገልጹ ድንጋጌዎችን መሠረት አድርጎ መዝገቡን መርምሯል፡፡

በተጨማሪም ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት፣ እንዲሁም ባለሥልጣናት ሕገ መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር፣ ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(2) ላይ መደንገጉንም ፍርድ ቤቱ በምርመራው ጠቁሟል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(1) እንደተገለጸው፣ ኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች የተከሰሱ ሰዎች የተጎናፀፉት በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት፣ በልዩ ልዩ ሁኔታዎች በሚለው ውስጥ የ‹‹ምስክሮች ጥበቃ›› አለመካተቱን ፍርድ ቤቱ በብይኑ ጠቁሟል፡፡ በአንቀጽ 20(4) ላይም ‹‹የተከሰሱ ሰዎች የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት መብት እንዳላቸውና የሰው ምስክሮችንም የሚያካትት መሆኑንም ከማስረጃ ሕግ ፍልስፍና መገንዘብ እንደሚቻል አክሏል፡፡ ከሕገ መንግሥት አተረጓጎም መርሆዎች አንፃር ተቀባይነት ያለውና በተለይ በሕገ መንግሥቱ ‹‹ማናቸውንም ማስረጃ›› የሚለውን ሐረግ መጠቀሙ፣ የተከሰሱ ሰዎች በምስክርነት የተቆጠሩባቸውን ሰዎች የማየትና የማወቅ መብትን ለማጎናፀፍ ጭምር መሆኑንም ፍርድ ቤቱ በአንክሮ ጠቅሷል፡፡

ምስክሮችን የመመልከት መብት በችሎት አካላቸውን የማየት ብቻ ነው ተብሎ በፍፁም መደምደሚያ ላይ ሊደረስ እንደማይቻል፣ ይልቁንም ሕገ መንግሥቱ ከሰጠው መብት ጀርባ በማስረጃ ሕግ ተቀባይነት ያላቸው ልዩ ልዩ የሕግ ፍልስፍናዎች ያሉ ሲሆን፣ ‹‹የቀረበው ምስክር ለምስክርነት ብቁ ነው? አይደለም?›› የሚለውን ማረጋገጥ የሚቻለው የምስክሩ ማንነት ሲታወቅ መሆኑንም ፍርድ ቤቱ አብራርቷል፡፡ በመሆኑም አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 4 (1በ እና ሸ) መሠረት ዓቃቤ ሕግ 29 ምስክሮች ስማቸው ሳይገለጽና በአካል ሳይታዩ በመጋረጃ ጀርባ እንዲመሰክሩለት መጠየቁ፣ የሕገ መንግሥት ጥያቄ እንደሚያስነሳ ፍርድ ቤቱ በብይኑ ገልጿል፡፡ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔን ለማጠናከር፣ ሥልጣኑንና ተግባሩን ለመዘርዘር የወጣው አዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ 3(1)፣ አንቀጽ 4(1እና3) ድንጋጌ መሠረት ፍርድ ቤቱ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮችን ለጉባዔው ማቅረብ እንደሚችልም አክሏል፡፡ በእርግጥ ተከራካሪዎቹ የዓቃቤ ሕግ ጥያቄ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ እንደሚጥስ ከመግለጽ በስተቀር ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ እንዲቀርብ ባይጠይቁም፣ ፍርድ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ 4(1) መሠረት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ማቅረብ ስለሚችል፣ ዓቃቤ ሕግ በእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ የቆጠራቸው 29 ምስክሮችን በሚመለከት ያቀረበው ጥያቄ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን በመሆኑ ትርጉም እንዲሰጥበት፣ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በተመሳሳይ የክስ መዝገብ ላይ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዞችን ሰጥቷል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ እንዳላገኛቸው ለፍርድ ቤት ያሳወቀውን የ34 የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በሚመለከት ‹‹ራሱ ዓቃቤ ሕግ አቀርባለሁ›› በማለቱ፣ ፍርድ ቤቱ ሰፋ ያለ ትንታኔ ከሰጠ በኋላ ለምስክሮቹ መጥሪያውን እንዲያደርስና ማድረሱን የሚያሳይ መተማመኛ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ባያቀርብ ግን የሚያልፈው መሆኑንም አክሏል፡፡ መጥሪያ ደርሷቸው ያልቀረቡ 36 ምስክሮችን ፌዴራል ፖሊስ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 125 ድንጋጌ መሠረት አስሮ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ በአድራሻቸው ‹‹አላገኘኋቸውም›› ያላቸውን ምስክሮች በአድራሻቸው ‹‹አቀርባለሁ›› በማለት ለዓቃቤ ሕግ ከገለጸ በኋላ መሆኑን የጠቆመው ፍርድ ቤቱ፣ በሁለቱ ተቋማት መካከል በምስክሮች አቀራረብ ረገድ ያለውን ልዩነት እንደሚያመላክት ጠቁሞ፣ ቀሪ 26 ምስክሮችን ሁለቱም ተቀናጅተው የፍርድ ቤቱን መጥሪያ እንዲያደርሱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...