የኢትዮጵያ ህልውና አስተማማኝ የሚሆነው ብሔራዊ ጥቅሟና ደኅንነቷ ሲከበር ነው፡፡ ይሁንና ከዚህ እውነታ በተቃራኒ በርካታ ጉዳቶች እያጋጠሙ ነው፡፡ ሰሞኑን ከመላ የአገሪቱ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ግጭቶችን በመሸሽ፣ ከ35 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለሳቸው ተሰምቷል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አስደንጋጭ ዜና እየሰሙ መዝናናት አይቻልም፡፡ ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ሲፈናቀሉ፣ በጦር መሣሪያ የተደገፈ ዕገታ በተማሪዎች ላይ ሲፈጸም፣ ሕፃናት ታግተው ሲገደሉ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ የጦር መሣሪያ ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ ሲፈጸም፣ መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ አደንዛዥ ዕፆች ሲዘዋወሩ፣ በቀላሉ መፈታት የሚችሉ አለመግባባቶች ወደ ግጭት እያመሩ ንፁኃን ሲገደሉ፣ በቀን በአማካይ 13 ሰዎች የሚሞቱባቸው የተሽከርካሪ አደጋዎች ከቁጥጥር ውጪ እየሆኑ ሲያስቸግሩና በርካታ ለአገር የማይጠቅሙ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እያየን ነው፡፡ ከእነዚህ አሳሳቢ ችግሮች በተጨማሪ በጠራራ ፀሐይ ተሽከርካሪዎችን የሚዘርፉ፣ በጦር መሣሪያ ጭምር የተደራጀ ዝርፊያ የሚፈጽሙና የሕዝቡን ደኅንነት ለአደጋ የሚያጋልጡ እየበዙ ነው፡፡ ችግሮችን ታቅፎ ምንም ያላጋጠመ ከማስመሰል ለመፍትሔ ፍለጋ የበኩልን አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባል፡፡ እነዚህ የተጠራቀሙ ችግሮች በፍጥነት ካልተወገዱ፣ በአገር ጥቅምና ደኅንነት ላይ የሚያደርሱት አደጋ ከሚታሰበው በላይ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ ከፊቷ ምርጫ እየጠበቃት ነው፡፡ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ መረጋጋት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትገነባ የሚፈልግ ማንኛውም ወገን ዴሞክራሲን መንከባከብ አለበት፡፡ ኢትዮጵያን በ‹‹ኖህ መርከብ›› ብንመስላት፣ የተለያዩ ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች ያሉዋቸው ወገኖች ተሳፍረውባታል፡፡ የመርከቧን ደኅነነት የመጠበቅ ኃላፊነት በመርከቧ ውስጥ የተጠለሉ ሰዎች በሙሉ መሆን አለበት፡፡ መርከቧ ውስጥ ተሁኖ በገጀራ መፈላለግ ወይም በጠመንጃ መታኮስ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም መርከቧ እንድትሰምጥ በማድረግ ተያይዞ መጥፋት ይከተላልና፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚቻለው የመርከቧን ደኅንነት በመጠበቅ፣ ጤናማ ፉክክር ለማድረግ የሚያስችል መደላድል በመፍጠር ብቻ ነው፡፡ የመናገርና ሐሳብን በማንኛውም መንገድ የመግለጽ ነፃነትን አሽሞኑሙኖ የሚሰጠው ዴሞክራሲ ነው፡፡ ዴሞክራሲን የመጠበቅ ኃላፊነትም የሁሉም ነው፡፡ ሚዲያውም ሆነ ሌሎች አካላት ዴሞክራሲን መጠበቅ ካልቻሉ ባይኖሩ ይመረጣል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መሽገው ውጥረት የሚፈጥሩም ሆነ ግጭት የሚቀሰቅሱ፣ ለዴሞክራሲ ጀርባቸውን የሰጡ ናቸው፡፡ ሃያ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ሥራቸውን እንዲያስተጓጉሉ በማድረግ አገርን ሰላም እየነሱ ነው፡፡ የአገር ሰላም ሲቃወስ ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ለአደጋ ተጋልጠው፣ ሊወጡበት ከማይችሉት አዘቅት ውስጥ ይገባል፡፡
ለአገር ሰላም፣ ብልፅግና፣ ፍትሐዊነት፣ እኩልነትና ነፃነት አስተዋጽኦ ማበርከት የሚገባቸው ፖለቲከኞች ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የብሔርና የሃይማኖት ግጭት እንዲቀሰቀስና የንፁኃን ሕይወት እንዲቀጠፍ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች የተለየ ዓላማ ከሌላቸው በስተቀር አገርን ችግር ውስጥ የሚከት ድርጊት ውስጥ አይገኙም ነበር፡፡ ነገር ግን አገርን በማተራመስና የሕዝብን ደኅንነት ለአደጋ በማጋለጥ፣ ድብቅ ዓላማቸውን ለማሳካት የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ነው፡፡ ፍላጎታቸው አንድም ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳትኖር መበታተን፣ ካልሆነም የእነሱን ፍላጎት የሚያሳካ አምባገነናዊ ሥርዓት መትከል ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለም ዴሞክራሲን በአፋቸው ያንበለብሉታል እንጂ፣ በተግባር ዕውን እንዲሆን አይፈልጉም፡፡ በኢትዮጵያ ምድር እውነተኛ ምርጫ ተካሂዶ ሕዝቡ በድምፁ የመወሰን ነፃነቱ ከተረጋገጠ፣ ሊገኝ የሚችለው ውጤት ስለሚያስፈራቸው ሒደቱን ማበላሸት ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም ፍላጎታቸው ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን፣ ቤተ እምነቶችንና የተለያዩ መሰባሰቢያዎችን የግጭት አውድማ ለማድረግ ይባዝናሉ፡፡ ለዚህ የጥፋት ድርጊታቸው ወደኋላ በመሄድ የአገሪቱን ታሪክ እያመሰቃቀሉ መርዝ ይነሰንሳሉ፡፡ በተፈጸሙ መልካም ተግባራትም ሆነ ክፉ ድርጊቶች የጋራ ተሳትፎ የሌለ ይመስል መልካሙን ለአንዱ ወገን፣ ክፉውን ለሌላው በማደል ትውልዱን ያባሉታል፡፡ ካለፉት መልካምና ክፉ ነገሮች በመማር በዚህ ዘመን አርዓያነት ያለው ተግባር ማሳየት እየተቻለ፣ የአገርን ህልውና የሚፈታተኑ አሳፋሪ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡ ኢትዮጵያም ሕዝቧም የታከታቸው እንዲህ ዓይነቱ አክሳሪ ፖለቲካ ነው፡፡
ለምርጫ እንፎካከራለን የምትሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ፈቃደኛ ከሆናችሁ፣ ግጭት የሚጠነስሱትንና የሚያስፈጽሙትን በጋራ ስትታገሉ አሳዩ፡፡ ምርጫው በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ ሒደት እንዲታጀብ ቁርጠኛ ከሆናችሁ፣ ፉክክራችሁ በሠለጠነ መንገድ እንዲከናወን ዕገዛ አድርጉ፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ሆናችሁ የጦር መሣሪያ ፍልሚያን በድብቅ አትቀስቅሱ፡፡ ለሕዝብ ይጠቅመዋል የምትሉትን ፖሊሲ በግልጽ ይዛችሁ ቀርባችሁ ለመወዳደር ተዘጋጁ እንጂ፣ በስም አጥፊነትና በጠላትነት ስሜት ውስጥ ሆናችሁ አታሲሩ፡፡ የሕዝብን የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤትነት የምታምኑና በተግባር የምታረጋግጡ መሆናችሁን ሕዝብ በማክበር አረጋግጡ፡፡ በሕዝብ ስም እየነገዳችሁ የሕዝብን ልጆች በብሔርና በሃይማኖት እየከፋፈላችሁ አታጋድሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከችጋርና ከመከራ ውስጥ እንዴት መውጣት እንደሚችል ፍኖተ ካርታችሁን አቅርቡ፡፡ ኢትዮጵያ ከልመና ለመውጣት እንዴት የተፈጥሮ ሀብቶቿን እንደምትጠቀምና ባለፀጋ እንደምትሆን አመላክቱ፡፡ የዘመናት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዴት መወገድ እንደሚችሉ መፍትሔ ጠቁሙ፡፡ ሌላው በሠራው ላይ አቃቂር ከማውጣት እንዴት አስበልጦ መሥራት እንደሚቻል አሳምኑ፡፡ ደሃ አገር ጀርባ ላይ በአንቀልባ ታዝላችሁ ሥልጣን በአቋራጭ እንዴት እንደሚገኝ ከማለም፣ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዕውን መሆን ታገሉ፡፡ በአገር ህልውና መቀለድ አቁሙ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ጉዳይ ሲወሳ በርካታ የመነጋገሪያ ጉዳዮች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ በተለይ የአገርን ጥቅም ለማንም አሳልፎ ለመስጠት አለመደራደር፣ ብሔራዊ ደኅንነትን ሊጎዱ የሚችሉ ማናቸውንም ሚስጥሮች መጠበቅ፣ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው እኩል መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ ብልሹ አሠራሮችን ከሥር መሠረታቸው መናድ፣ አድልኦና መገለልን ማስወገድ፣ የሕግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር፣ በኢትዮጵያዊያን መካከል ጥላቻና ግጭት የሚቀሰቅሱ ማናቸውንም ድርጊቶች ማምከን፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን መጠበቅ፣ የሕዝብ ደኅንነትንና ጤና የሚጎዱ ማናቸውም ዓይነት ምርቶች ላይ ዕርምጃ መውሰድ፣ ወዘተ አፅንኦት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት አገር መሆን የምትችለው ለህልውናዋ ቅድሚያ ሲሰጥና ሰላም ሲሰፍን ነው፡፡ ሕዝቡ በነፃነት ሲነጋገር፣ ሲከራከርና ሐሳቦች በተሟላ መንገድ ሲንሸራሸሩ ዴሞክራሲ ባህል ይሆናል፡፡ ሐሰተኛ መረጃዎች በቀላሉ እየተሠራጩ ጉዳት የማድረስ አቅማቸው ይመናመናል፡፡ አገርን ለማተራመስ የሚፈልጉ ኃይሎች ይጋለጣሉ፡፡ ማን ለሕዝብ የሚጠቅም አጀንዳ እንደሰነቀ፣ ማን ደግሞ አውዳሚ ዓላማ እንደያዘ በግልጽ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችም እንደፈለጋቸው የሚፈነጩበት መስክ ያጣሉ፡፡ መጪው ምርጫም መካሄድ ያለበት እንዲህ ያሉ ነገሮችን በማጥራት ነው፡፡ ‹‹ሲፋጅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ›› እያሉ አገርን ማተራመስ ማብቃት አለበት፡፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ የሞራል ከፍታን ያሳዩት የጋሞ አባቶች፣ ሰሞኑን ደግሞ ከወጣቶቻቸው ጋር በጉልበታቸው በመንበርከክ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሰላም በአንድነት እንዲቆሙ በእንባቸው ተማፅነዋል፡፡ ይህንን የታላቅነት ተግባር በተደጋጋሚ ሲያሳዩን እኛ ምን እያደረግን ነው ብለን ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ በዚህ የሞራል ከፍታ ላይ በመሆን ብሔራዊ ጥቅምንና ደኅንነትን ከሚጎዱ ድርጊቶች መታቀብ ይገባል!