መንግሥት መጪው ምርጫን እንዲታዘብ ግብዣ ያደረገለት የአውሮፓ ኅብረት፣ በአገሪቱ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ የሚገመግምና ግብዓት የሚሰበስብ ቡድን በአዲስ አበባ ጉብኝት በማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው፡፡
የአውሮፓ የውጭ ጉዳዮች አገልግሎት (European External Action Service) ፖሊሲ መኮንን ሎይክ ደፋይ፣ እንዲሁም የሕግ ባለሙያ ሬቤካ ኮክስን ያካተተው የልዑካን ቡድን፣ በአዲስ አበባ በመገኘት ከመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡
‹‹እዚህ የመጣነው የምርጫ ታዛቢነታችን የሚኖረውን አስተዋጽኦ ለመገምገም ነው፡፡ ግምገማውም በሦስት ዋነኛ ጭብጦች ላይ ያተኩራል፡፡ እነዚህም የታዛቢነታችን ጠቀሜታ፣ መታዘባችን ይመከራል ወይ፣ እንዲሁም ከትራንስፖርት፣ ከሎጂስቲክስና ከፀጥታ አንፃር አዋጭ ነው የሚሉትን ጉዳዮች ለመመልከት ነው፤›› በማለት ሎይክ ደፋይ ዓርብ ጥር 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት ለሁለት ሳምንታት በሚዘልቀው ቆይታው ከሚኒስትሮች፣ ከሲቪል ማኅበረሰቡ፣ ከመገናኛ ብዙኃን፣ ከምሁራን፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ጋር ውይይት እንደሚያደርግና ግብዓት እንደሚሰበስብ የልዑካን ቡድኑ አስታውቋል፡፡
ቡድኑ በአዲስ አበባ የሚኖረውን የግምገማ ጊዜ ሲያጠናቅቅ የሰበሰበውን ግብዓት መሠረት አድርጎ የሚያዘጋጀውን ሪፖርት ለአውሮፓ የውጭ ጉዳዮች አገልግሎት እንደሚያቀርብ የገለጸ ሲሆን፣ ሪፖርቱ የቀረበለት አካልም የመጨረሻ ውሳኔውን በየካቲት ወር ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የመጨረሻ ውሳኔውን የሚያሳውቀው አካልም ምን ያህል ታዛቢዎች እንደሚሰማሩ፣ በየትኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች ሊሰማሩ እንደሚችሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ ዝርዝር ውሳኔውን ይፋ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል፡፡
አወዛጋቢ በነበረው የ1997 ዓ.ም. ምርጫን ተከትሎ የኅብረቱና የኢትዮጵያ ግንኙነት መሻከሩ የሚታወስ ሲሆን፣ በተለይ በወቅቱ የታዛቢውን ቡድን በበላይነት ይመሩ የነበሩት ፖርቱጋላዊቷ የኅብረቱ ፓርላማ አባል አና ጎሜዝና የኢትዮጵያ መንግሥት ውዝግብ የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ከምርጫ 97 ቀጥሎ በ2002 በተካሄደው ምርጫ ኅብረቱ ታዛቢን መላኩ ይታወሳል፡፡ በወቅቱም ኔዘርላንዳዊው ቲዝ በርማን ቡድኑን መምራታቸው አይዘነጋም፡፡
የምርጫ 97 ውዝግብ ጥላውን ያጠላበት የኅብረቱና የኢትዮጵያ ግንኙነት ሻክሮ ኅብረቱ ምርጫ 2007 እንዲታዘብ አልተጋበዘም ነበር፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ወኪል ጽሕፈት ቤቱን በአዲስ አበባ የከፈተው እ.ኤ.አ. በ1975 ነው፡፡