Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ የኅብረት ባንክን ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመት አፀደቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቅርቡ ኃላፊነታቸውን በለቀቁት የኅብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ምትክ፣ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን እንዲሠሩ የታጩትን አቶ መላኩ ከበደን ሹመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አፀደቀ፡፡

ከባንኩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አቶ መላኩ የባንኩ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲሠሩ የኅብረት ባንክ ቦርድ ለብሔራዊ ባንክ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ተፈቅዶለታል፡፡

የኅብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ታዬ ዲበኩሉ ከኃላፊነታቸው ከለቀቁ በኋላ፣ የኅብረት ባንክ ቦርድ አቶ መላኩን ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ መሰየሙ አይዘነጋም፡፡

አቶ መላኩ ይህንን ኃላፊነት ከመረከባቸው ቀደም ብሎ የባንኩ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ (ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ) በመሆን ሲያገለግሉ ነበር፡፡ በተለይ የሲስተምና የኢባንኪንግ፣ እንዲሁም የአይቲ ዲፓርትመንት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ከ11 ዓመታት በላይ ማገልገላቸው ታውቋል፡፡

 አቶ መላኩ በቴክኖሎጂ መስክ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ አሻራቸውን ያኖሩ መሆናቸው፣ ሁሉም ባንኮች በአባልነት የያዘው ኢትስዊች ምሥረታ ላይ የጥናት የቡድን መሪ በመሆን ማገልገላቸው ተጠቁሟል፡፡

ኅብረት ባንክን ከመቀላቀላቸው ቀደም ብሎ የዘመን ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ከአራት ዓመታት በላይ እንደሠሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዚህም ተጨማሪ ከኢንሳና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር በመሆን የፋይናንስ ተቋማትን ከሳይበር ጥቃት ለመከላከል የተቋቋመው ቡድን ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው፣ በተለይ በኅብረት ባንክ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ከዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ባንኩ የሚያካሂዳቸውን የኤሌክትሮኒክስ ባንኪንግና ተመሳሳይ ሥራዎችን ከማስተባበር ጀምሮ፣ እስከ ትግበራ ድረስ ባለው ሥራ ውስጥ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ከባንኩ መረጃ መረዳት ተችሏል፡፡

የባንክ ኢንዱስትሪውን ከመቀላቀላቸው ቀደም ብሎ በአማራና በፌዴራል ኦዲተር ቢሮ ውስጥ ከዘጠኝ ዓመታት በላይ በከፍተኛ የኦዲት ባለሙያነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውም ተጠቅሷል፡፡

የቀድሞው የኅብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታዬ ባንኩን ከስድስት ዓመታት በላይ በማገልገል የተሸኙ ሲሆን፣ ላደረጉት አስተዋጽኦ ቦርዱ ቪኤይት ቶዮታ ተሽከርካሪና የ500 ሺሕ ብር ሽልማት ማበርከቱ ይታወሳል፡፡

ኅብረት ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው 2011 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 980 ሚሊዮን ብር ማትረፉን መግለጹ አይዘነጋም፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች