የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ሊካሄድ ስድስት ወር ከስድስት ቀን ቀርቶታል፡፡ በርካታ አገሮች ዝግጅታቸውን አጧጡፈዋል፣ አትሌቶቻቸው የሚሳተፉባቸው የስፖርት መስኮች ስብጥር አዛምደው ለኦሊምፒክ ተሳትፎ ወገብ ታጥቀው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአንፃሩ በኢትዮጵያ በኩል የሚታየው ሁኔታ ከዝግጅቱ ይልቅ፣ ስፖርቱ በሚመለከታቸው አካላት መካከል የሚታየው ትርምስና ሽኩቻ ግራ የሚያጋባ ሆኗል፡፡ ከግጭቱ ጀርባ “ተዉ” ባይ ያጡ ተዋንያን፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እጅና ጓንት ሆነው በመሥራት ለአገር ክብርና ዝና ሊተጉ በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት አላስፈላጊ ንትርክ በመካከላቸው እንዲቀጣጠል ሲዳክሩ ይታያሉ፡፡
‹‹እገሌ አያገባውም፣ ከፈለግሁ ከአባልነቴ እወጣለሁ፤›› እየተባለ ለማኅበር ወይም ለዕቁብ የተሰባሰቡ ይመስል የሁለቱ ተቋማት የሥራ አመራር ቦርድ ሲገናኙ እንዳይደማመጡ የሚደረገው አካሄድ ከኦሊምፒክ በኋላ በይደር ተላልፎ አሁን ላይ ትኩረት ቅድሚያ ለሚያስፈልገው ቶኪዮ ኦሊምፒክ ማዋል ሙያዊ ብቻ ሳይሆን፣ የዜግነት ግዴታም ስለመሆኑ፣ በዚህ ወቅት አስተዳደራዊ አለመግባባቶችን እያባባሱ መካረርና መቧደን የኢትዮጵያን ኦሊምፒክ ተሳትፎ እንዳይጎዳው ሥጋት ያደረባቸው ታዛቢዎች፣ ‹‹ምነው ፀቡን ከቶኪዮ በኋላ ቢያደርጉት፤›› እንዲሉ አስገድዷቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባለፈው ቅዳሜ ጥር 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አዱላላ ሪዞርት በዝግ በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ፣ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው የሥራ አመራር ቦርድ የአገልግሎት ዘመንና ተቋሙን በዋና ጸሐፊነት መምራት ስለሚገባው የሥራ መደብ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተሳትፎዎች ሲኖሩ የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ ማግኘት ይቻል ዘንድ የውጭ አካውንት መክፈት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተነጋግሮ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ይታወሳል፡፡
ከተላለፉት ውሳኔዎች መካከል የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው የሥራ አመራር ቦርድ የቆይታ ጊዜ ከአራት ዓመት ወደ ስምንት ዓመት እንዲሻሻል ለዚህም የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 20 መሠረት ያደረገ ሆኖ ነገር ግን ውሳኔው በሒደት የሚታይ እንደሚሆን፣ የዋና ጸሐፊውን የሥራ መደብ በተመለከተ የበርካታ አገሮች ተሞክሮ በመውሰድ በተመራጭ እንዲሆን፣ ሦስተኛው አከራካሪ ሆኖ የቀረበው ደግሞ ተቋሙ የ‹‹ውጪ አካውንት ሊኖረው ይገባል›› የሚለው ነው፡፡
እንደ ሪፖርተር ምንጮች ከሆነ፣ የሥራ አመራር ቦርዱ የአገልግሎት ጊዜ በሒደት የሚታይ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አጀንዳው 61 ድጋፍና ሦስት ተቃውሞ ውሳኔ የተላለፈበት ሆኖ ተጠናቋል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጉባዔው ውሳኔ ያሳለፈባቸው ጉዳዮች ተገቢነት ላይ ‹‹አልተስማማሁም›› በሚል ተቃውሞውን በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ ይህ የፌዴሬሽኑ አቋም ሰሞነኛ መነጋገሪያ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡
አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቃውሞ ካቀረበባቸው ጉዳዮች የዋና ጸሐፊው የሥራ መደብ ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በአይኦሲ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ከመደራጀቱ በፊት ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ኦሊምፒክ ኮሚቴ›› ተብሎ ይጠራ እንደነበረ የሚናገሩ ቀደምት ሙያተኞች፣ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የአይኦሲ ቻርተርን መሠረት አድርጎ ዳግም በ1960 ዓ.ም. እንዲደራጅ ከተደረገ በኋላ አሁን ላይ ለክርክርና ለንትርክ በር የከፈተው ዋና ጸሐፊነት ከተመረጡ የሥራ አስፈጻሚ አባላት መካከል ሆኖ፣ ነገር ግን የተቋሙን የዕለት ተዕለት ሥራ የሚያከናውን ቅጥር ሙያተኛ በተመራጩ ዋና ጸሐፊ ሥር የሚሠራ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አሁን ያሉት ዋና ጸሐፊ ሙሉ ኃላፊነቱ እስከ ተሰጣቸው ድረስ ተቋሙ በተመራጭ ቋሚ ዋና ጸሐፊ ይመራ የነበረ መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡
ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው መመልከት የሚገባው በመተዳደሪያ ደንቡ ቋሚ ዋና ጸሐፊና የዋና ጸሐፊውን የሥራ መደብ በግልጽ ማስቀመጥ እንዳለበት የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ የተቀጣሪ ዋና ጸሐፊ የሥራ መደብ በሚመለከት ጉዳዩ መታየት ያለበት በሥራ አመራር ቦርዱ እንጂ፣ በጉባዔ ሊሆን እንደማይገባ ያሳስባሉ፡፡ የዋና ጸሐፊ ጉዳይን በሚመለከት ጉባዔው ድርሻ እንዳለው ተደርጎ የቀረበ መተዳደሪያ ደንብ ተቋሙ ተቀምጦ ከሆነ ጉባዔው ችግሮች ከመባባሳቸው በፊት ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና አሠራሮች መነሻ በማድረግ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ ያለበት ስለመሆኑ ጭምር ይመክራሉ፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚያነሳው መከራከሪያ በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው መተዳደሪያ ደንብ ለመሆኑ ማሳያው የዋና ጸሐፊውን ጉዳይ በሚመለከት ያቀረበው ሐሳብ፣ ‹‹ጸሐፊው የሥራ ዘመኑን ሲጨርስ መሻርም ሆነ አዲስ መሾም የሚገባው በጠቅላላ ጉባዔው ሆኖ ሳለ አሁን ያለው ዋና ጸሐፊ ጉባዔው ሾሞት በፕሬዚዳንቱ መነሳቱ (ጉዳዩ የታየው በዝግ ጠቅላላ ጉባዔ ነው) ተገቢ ያልሆነና ዋና ጸሐፊው መነሳትም ካለበት በሰየመው አካል መሆን ይገባዋል፤›› በሚል እንደሆነ ከደብዳቤው ይዘት መረዳት ይቻላል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሁለቱ መከራከሪያዎች ማለትም የሥራ አመራር ቦርዱ የአገልግሎት ዘመንና የውጭ አካውንትን በሚመለከት የቀረበው ይጠቀሳል፡፡ በተለይ የውጭ አካውንት አስመልከቶ ለጉባዔው በውይይት መልክ የቀረበው ጉዳይ፣ ከዚህ በፊት የኦሊምፒክ ተሳትፎን ጨምሮ ሌሎችም ዓለም አቀፍ መድረኮች ሲኖሩ ለተወዳዳሪዎችና ለሙያተኞች እንዲሁም ለሌሎችም ተመሳሳይ ወጪዎች ሲባል የውጭ ምንዛሪ በግለሰቦች ቦርሳና መሰል አሠራር ተይዞ ይኬድ የነበረው አሠራር ገንዘቡን ይዞት ለሚንቀሳቀሰው ግለሰብ ጭምር አደጋ የሚያስከትል በመሆኑና ከዚህ ይልቅ የብሔራዊ ባንክን ይሁንታ ጠይቆ የውጭ አካውንት መክፈት እንደሚሻል ጉባዔው አምኖበት አጀንዳው እንዲፀድቅ ተድርጓል ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይህን ውሳኔ በሚመለከት፣ ‹‹በውጭ ሀገር አካውንት ለመክፈት የቀረበው ሐሳብ ከመንግሥት የውጭ ሀገር ምንዛሪ አጠቃቀምና አሠራር ጋር የሚጋጭ በመሆኑ አግባብነት የሌለው መሆኑን እንገልጻለን፤›› በማለት ነው፡፡
በሁለቱ ተቋማት ሰሞነኛ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሙያተኞች በበኩላቸው፣ ‹‹የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የመንፈቅ ዕድሜ በቀረበት በአሁኑ ወቅት ሽኩቻውና ክርክሩ ምክንያታዊ ነው ተብሎ ቢታመን እንኳ ጊዜው አይደለም፡፡ ምክንያቱም አትሌቲክስ ማለት ለኢትዮጵያ ‹‹አንድ ዓይን ያለው በአፈር አይጫወትም፤›› በመሆኑ የስፖርቱ ዋና ባለድርሻዎች ሁለቱ ተቋማት ችግሩ እንዲባባስ ከጀርባ ሆነው ለሚያቀጣጥሉት አካላት ትኩረት ሳይሰጡ ለአንድ ዓላማ በጋራ ቆሞ መሥራት ይጠበቅባቸዋል በማለት ይመክራሉ፡፡
ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አንዳንድ አመራሮች፣ “ልዩነት ለስፖርቱ ዕድገት እስከሆነ ድረስ እንቅፋት አድርጎ መውሰድ አይገባም፤” ይሉና ብሔራዊ ፌዴሬሽናቸው ባደረገው ጉባዔ መነሳት የነበረባቸው በርካታ አጀንዳዎች ሳይቀርቡ ተሸፋፍነው የታለፉበት አጋጣሚም እንደነበር ያስታውሳሉ። “አመራሩ ይህን ጉዳይ በጋራ ለመገምገም ቀጠሮ ይዞ ባለበት ወቅት ይህ መከሰቱ ያሳዝናል፣ ይሁንና ጉዳዩ የጋራ ጉዳይ እስከሆነ ድረስ ተቀራርቦ መነጋገር ሲቻል ወደ አላስፈላጊ ነገር ወስዶ መነታረክ ተገቢ አይደለም፤” ሲሉ ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡
እንደነሱ አገላለጽ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም ሆነ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሁን ላይ የትኩረት አቅጣጫቸው ሊሆን የሚገባው፣ ዓለም በጉጉት በሚጠብቀው ታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ አገሪቱን የሚወክሉ አትሌቶች ላይ መከራከርና መነጋገር ሲገባ፣ በአንፃሩ ነገን በማያሻግር ውዝግብ መጠመድ ተገቢ አይደለም፡፡
ይልቅስ ሁለቱም ተቋማዊ አደረጃጀቶቻቸውን ፈትሸው በተለይ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያስቀመጧቸው ሙያተኞች ስፖርቱን ለማሳደግ ምን እየሠሩ ነው የሚለውን ጉዳይ በመከታተል ለየተቋሞቻቸው ሁለንተናዊ ዕድገት መትጋት እንደሚጠበቅባቸው ጭምር ይመክራሉ፡፡