በጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
“ሰበብህን ቆጥበው፡፡ ጊዜ የማግኘት ጉዳይ ሳይሆን ጊዜ የመስጠት ጉዳይ ነው፡፡ ላንተ በጣም አስፈላጊ ከሆነ ጊዜ ስጥ፤” ያልታወቀ ሰው ከተናገረው የተወሰደ፡፡
በአገራችን የፖለቲካ ጉዳይ በተለይም ኢሕአዴግ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ፣ ምርጫ አወዛጋቢ ያልሆነበት ጊዜ የለም፡፡ ኢሕአዴግ በጉልበቱ የሽግግር መንግሥት አቋቁሞ ራሱን ያፀደቀውን ቻርተር ጥሶ ጊዜውን ካራዘመ በኋላ፣ አገራችን ውስጥ “ቋሚ የሆነ መንግሥት” ይመሠረት ዘንድ በግንቦት 1987 ዓ.ም. ነበር የመጀመርያው “አገራዊ ምርጫ” የተካሄደው፡፡ ይህ ምርጫ ከመደረጉም በፊት ሆነ ከተደረገ በኋላ ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሳ ከመሆኑም በላይ፣ በተቃዋሚ ጎራ የተሠለፈው ኃይል ሜዳውን ሙሉ ለሙሉ ለገዥው ፓርቲ ትቶ ገዥው ፓርቲ ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው መንግሥት ተቋቋመ፡፡
ከሌሎች የምርጫ ጊዜዎች የ1987 ዓ.ም. ምርጫ የተለየ የሚያደርገው ለዚህ ምርጫ ምዕራባውያን ትኩረት ሰጥተው ተቃዋሚዎች በምርጫ ሊሳተፉ የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት ነበር፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት፣ በየካቲት 1987 ዓ.ም. የፕሬዚዳንቱ የፀጥታ ጉዳዮች አማካሪ የነበሩት አንቶኒ ሌክ የመሩት ቡድን፣ ከገዥው ፓርቲና ከተለያዩ የተቃዋሚ ኃይሎች ጋር በኋይት ሃውስ ያደረጉቧቸው በርካታ ውይይቶች የጥረቱ ምሳሌ ሆኖ ይጠቀሳል። ለዚህ የኢትዮጵያ ምርጫ ምዕራብውያኑ ትኩረት ሰጥተው በገዥው ፓርቲ ላይ ያደረጉት ግፊት አንዳንድ ተቃዋሚ ጎራ ውስጥ የነበሩ “የፖለቲካ ልሂቃን” የተሳሳተ የፖለቲካ ሥሌት በማድረግ፣ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ በመድረሳቸውም ምዕራብውያኑ ከሚገባው በላይ በገዥው ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ጫና አድርገው ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ምኅዳሩን ይበረግዳል ብለው ገመቱ። በዚህም የተነሳ በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) ይመሩት ከነበረው የፖለቲካ ድርጅት በስተቀር፣ ሁሉም በሚባል ሁኔታ ገዥው ፓርቲ የምርጫ ጊዜውን ካላራዘመና የምርጫ ቦርዱን ካልቀየረ በስተቀር በምርጫው አንገባም ሲሉ ደመደሙ። ፕሮፌሰር በየነም በተቃዋሚው ጎራ በተደረገባቸው ከፍተኛ ጫና ወደ ምርጫው ለመግባት ውሳያቸውን በመከለስ፣ በግንቦት 1987 ዓ.ም. ምርጫ እንደማይሳተፉ ገለጹ።
ይህ በተቃዋሚው ጎራ የተወሰደው የተሳሳተ ውሳኔ የፖለቲካ ምኅዳሩን ከማስፋት ይልቅ በማጥበቡ አገራችንን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል። ይህ ጸሐፊ በወቅቱ በዋሽንግተን ዲሲ ይተላለፍ የነበረው የኅብረት ሬዲዮ አዘጋጅና አቅራቢ ከነበሩት አንዱ ነበር። የዚህ ሬዲዮ ዝግጅት የፈጠረለትን አጋጣሚም ተጠቅሞ በተቃዋሚ ጎራ የነበረው የፖለቲካ ኃይል ወደ ምርጫው እንዲገባ ከፍተኛ ግፊት አድርጓል። ለኦነግ፣ ለኢዲኃቅ ለመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት፣ ለአማራጭ ኃይሎች፣ እንዲሁም በወቅቱ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር በአሜሪካ ለነበሩት ለአምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ቃለ መጠይቅ በማድረግ መንግሥትና ተቃዋሚዎች ስምምነት ፈጥረው ምርጫው ሁሉን አሳታፊ እንዲያደርግም በቃለ መጠይቆቹ ሞግቷል። ሆኖም በተቃዋሚዎች እምቢተኝነትና ያለ ምንም ስትራቴጂ በተወሰደ ዕርምጃ ተቃዋሚዎች በዓለም መድረክ ላይ የነበራቸውን ተደማጭነት አጡ። ምዕራብውያኑም ተቃዋሚዎች ሰበብ ፈላጊ እንጂ የተፈጠረላቸውን አጋጣሚ ተጠቅመው በትግሉ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ተግቶ ለመታገል የቆረጡ አይደሉም ሲሉ ደመደሙ።
ምንም እንኳን የተቃዋሚው ኃይል ሕዝቡ በ1987 ዓ.ም. ምርጫ ባለመሳተፍ ገዥው ፓርቲ፣ መንግሥት የመሆን “ሕጋዊነት” (Legitimacy) እንዳይኖረው በምርጫው ላይ ማዕቀብ እንዲደረግ ቢሞክርም፣ ሕዝቡ በምርጫው ተሳተፈ፡፡ ከዚያም በላይ በርካታ ግለሰቦች “በግል ተወዳዳሪነት” ገዥውን ፓርቲ ተቃውመው በምርጫው በመሳተፍ፣ ገዥው ፓርቲ ብቻውን መንግሥትን እንዲቆጣጠርና መንግሥትም ምርጫው “ፍትሐዊና ነፃ” ነው እንዲል አደረጉት። የሚያሳዝነው የተቃዋሚው ኃይል፣ በደመነፍስ የሚንቀሳቀስ ሁኔታዎችን ለመምራት፣ የረጅምና የአጭር ጊዜ ዓላማና ግቡን ነድፎ የማይንቀሳቀስ፣ ለሚፈጠሩ ነገሮች ምላሽ በመስጠት የተጠመደ በመሆኑ፣ ትግሉን በቅጡ ሊመራ አልቻለም። ይህ ጸሐፊ ኢሕአፓ በሳንዲያጎ አዘጋጅቶት ለነበረው ስብሰባ “Lack of Strategic Planning, the Deficiency in the Ethiopian Opposition Camp” የሚል ሰፊ ሃተታ ያለው ጽሑፍ በማቅረብ ገና ከጅምሩ፣ ተቃዋሚው የአጭርና የረጅም ጊዜ ዓላማና ግብ፣ እንዲሁም የሚጓዝበትን መንገድ እንዲነድፍ የምክር ሐሳብ አቅርቦ ነበር። ሆኖም እስከ መጨረሻው ያየነው ነገር ተቃዋሚው በደመነፍስ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ነው። በዚህም ምክንያት ነው “አንጋፋ የነበሩት” እንደ ኢዲኃቅ ዓይነትና መድኅን የተባሉት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ሊከስሙ የቻሉት።
በዚህ ጸሐፊ እምነት የተቃዋሚው ጎራ ትልቁ ችግር ከስህተቱ ለመማር ፈቃደኛ አለመሆኑ ነው። ከ1987 ዓ.ም. ምርጫ ምንም ዓይነት ትምህርት ያልወሰደው የተቃዋሚ ኃይል፣ ለግንቦት 1992 ዓ.ም. ምርጫም የማይሳተፍ መሆኑን በአደባባይ አወጀ፡፡ በምርጫ ለመሳተፍ ያንገራግሩ የነበሩ በአገር ውስጥ የነበሩ ድርጅቶች ላይ የወከባ ዘመቻ ተጀመረ፡፡ ምርጫ ውስጥ መሳተፍ እንደ ክህደትም ተቆጠረ፡፡ አንዳንዶቻችን የምርጫው ሜዳ ለገዥው ፓርቲ መተው የለበትም ብለን በማመናችን፣ በተለይም በግል እንወዳደራለን ብለው ዝግጅት ያደርጉ የነበሩ ሰዎችን በአንድ አጀንዳ ሥር በማስተባበር በየምርጫ ጣቢያው የሚኖረው ውድድር፣ አንድ የኢሕአዴግ ተወዳዳሪ ከአንድ ተቃዋሚ ጋር ሊወዳደር የሚችልበትን መድረክ ለማዘጋጀት፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አንጋፋ ሚና ካላቸው ሰዎችም ጋር ውይይት ተደረገ። ይህ ሁኔታ በውይይትና በጥናት ደረጃ ላይ በነበረበት ጊዜም፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት በመጀመሩ ለተጀመረው ንድፈ ሐሳብ እንቅፋት ሆነ። በዚህ ውስብስብ ጊዜም ነበር የኢትዮጵያውያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢዴፓ) የተባለ በአቶ ልደቱ አያሌው የተመራ ድርጅት ገና ብቅ ከማለቱ፣ በግንቦት 1992 ዓ.ም. ምርጫ እንደሚሳተፍ ያበሰረው፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ጥሩ ዜና ነበር፡፡ ኢዴፓን ተከትሎ ሌሎች በአገር ውስጥ የነበሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች በምርጫው ተሳተፉ በምርጫ 1992 ተቃዋሚው ጎራ ገዥውን ፓርቲ ምጥ አስያዘው፡፡
በምርጫ 1992 ተቃዋሚው ባደረገው የምርጫ ተሳትፎ ምክንያት፣ በፌዴራል ምክር ቤትም ውስጥ ሆነ በአንዳንድ የከተማና ክልል ምክር ቤቶች መቀመጫ ለማሸነፍ በመቻሉ፣ በየምክር ቤቶቹ ስብሰባዎች ገዥውን ፓርቲ በመሞገትና የፖሊሲዎቹን ድክመትና አደገኛነት በማጋለጥ፣ ለፖለቲካው ሒደት ያበረከቱት አስተዋጽኦ የሚናቅ አልነበረም። ተቃዋሚው ይህንን ያገኘውን ድል በማስፋት የኅብረተሰቡን ልብ በማሸነፍ ገዥውን ፓርቲ በራሱ የፖለቲካ ቁማር ከጨዋታ ውጪ ከማድረግ ይልቅ፣ እርስ በርሱ በመጠላለፍና አንዱ ሌላውን በመተንኮስ ጊዜና ኃይል ማባከኑን ቀጠለ። “ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ” የሚለው የሕዝብ ግፊት በማየሉም ነው በነሐሴ 1995 ዓ.ም. በአሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት ውስጥ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት (ኅብረት) የተባለው ድርጅት የተመሠረተው፡፡ ኅብረት ግን ወደ ታሰበለት ግብ ሳይደርስ፣ ገና ከጅምሩ በውስጡ የነበሩት ድርጅቶች መንጠባጠብ ስለጀመሩ ጉልበት አጣ፡፡ ያው ፖለቲካው በለመደው መጠላለፍ ቀጠለ፡፡ የዚህ መጠላለፍ ምክንያት ነው በኅዳር 1997 ዓ.ም. ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት) የተባለውን ድርጅት የፈጠረው፡፡
ቅንጅት ትግሉ ከኢሕአዴግ ጋር ከኅብረት ጋር ነበር፡፡ በሁለቱ መካከል የነበረው ሹክቻ ቀርቶ ትግላቸውን በኢሕአዴግ ላይ እንዲያነጣጥሩ ብዙ ግፊት፣ በሚያዚያ 1997 ዓ.ም. ምርጫው አንድ ወር ብቻ ሲቀረው በቅንጅትና በኅብረት መካከል ትብብር ተፈጠረ፡፡ ይህ የሚያሳየው ተቃዋሚው በደመነፍስ የሚንቀሳቀስና አገራዊ ራዕዩ የደከመ እንደነበር ነው፡፡ የግንቦት 2002 ዓ.ም. ሆነ የግንቦት 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የተደረጉት ምርጫዎች የሚያሳዩት፣ በተቃዋሚው ጎራ መካከል ኢሕአዴግን በጠላትነት ከመፈረጅ ባለፈ፣ ምንም ዓይነት የአጭርና የረጅም ጊዜ የጋራ አጀንዳ ነድፎ የማይንቀሳቀስ መሆኑን ነው። ምንም እንኳን መድረክ የተባለ ስብስብ ቢኖርም፣ በመድረክ ውስጥ ያሉ ብሔር ተኮር ድርጅቶች የየብሔራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ከመቆም በቀር ምንም ዓይነት ብሔራዊ የጋራ አጀንዳ ነድፈው የማይንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው በኅዳር 2007 ዓ.ም. የተነሳው አመፅ ያለ ምንም ፖለቲካ ድርጅት መሪነት በወጣቱ ግብታዊ ስሜት ሊቀሰቀስ የቻለው፡፡
ይህ ግብታዊ አመፅ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ለውስጥ ለለውጥ ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ ኃይሎች ጉልበት በመፍጠሩ፣ ገዥው ፓርቲ ከውስጡ ተገዝግዞ ዛሬ ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ዛሬ ደግሞ ለውጡን የሚመራው ኃይል በአገራችን የዴሞክራሲያዊ ሥልተ ሥርዓት እንዲገነባ ሕዝቡ ወዶና ፈቅዶ የመረጠው የፖለቲካ ኃይል የመንግሥትን ኃይል እንዲቆጣጠር ተግቶ በሚሠራበት ወቅት፣ የዚህ ሒደት እንቅፋት በመሆን ላይ ያሉት በተቃዋሚ ጎራ ውስጥ የተሠልፉ ኃይሎች መሆናቸው አስገራሚ ነው። ሌላው ቀርቶ ለመጀመርያ ጊዜ በታሪካችን ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች በምርጫ ፖለቲካ ውስጥ እንዲሳተፉ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ድፍረት የሰጠው ኢዴፓ እንኳን፣ “የምርጫው ጊዜ ይራዘም” ሲል መስማቱ አስገራሚ ነው። ሌላው አስገራሚ ነገር በተቃዋሚ ጎራ የተሠለፈው ኃይል አቅሙን ሰብሰብ አድርጎ ለአገር ይጠቅማል የሚለውን የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ኑሮ ዕቅድ ነድፎ ለግንቦት ለመጪው 2012 ምርጫ ራሱን ለማዘጋጀት ከመትጋት ይልቅ፣ ምርጫው ውስጥ ላለመሳተፍ “ሰበብ” መደርደሩ ነው፡፡ በአገራችን ውስጥ ከ130 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች መኖር ራሱ በተቃዋሚ ጎራ የተሠለፈው ኃይል መሪ ያጣ የፖለቲካ ኃይል ለመሆኑ ምስክር ነው፡፡ በመቶ የሚቆጠሩ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን አስተባብሮ ቁጥራቸውን መቀነስ ያልቻለ የፖለቲካ ኃይል፣ ስንት የተወሳሰበ ችግር ያለባትን አገር በመሪነት ተረክቦ ሊያስተዳድር ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል ወይ?
የምርጫ ቦርድ በተወካዮች ምክር ቤት ያስፀደቀውን የምርጫ ሕግ ተከትሎ ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የምንሰማው አቤቱታ ሰበብ እንጂ፣ ምርጫ ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚያግድ አይደለም። ጊዜ ሰጥቶ ተግቶ በመሥራት ፖሊሲ ነድፎ አሥር ሺሕ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ማሳመን የማይችል የፖለቲካ ድርጅት፣ እንዴት ነው በሚሊዮን የሚቆጠር መራጭ ሊያሳምን የሚችለው? ይህንን ተከትሎ የምንሰማቸው አቤቱታዎች ትናንትና ላይ ቆመው የወደፊቱን ማየት በማይፈልጉ የፖለቲካ ኃይሎች ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም.ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ ምርጫ እንደሚካሄድ ለማንም ሚስጥር አይደለም፡፡ ይህ ከአምስት ዓመታት በፊት ጀምሮ ይታወቅ ነበር፡፡ በአገር ውስጥም ያሉ ይሁኑ ከአገር ውጪ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች በአሁኑ የለውጥ የፖለቲካ ሒደት ውስጥ ለመሳተፍ የወሰኑት፣ በ1987 ዓ.ም. የፀደቀውን ሕገ መንግሥት ተቀብለው ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱም በየአምስት ዓመቱ ብሔራዊ ምርጫ እንደሚኖር ደንግጓል፡፡ ከዛም አልፎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ምርጫው እንደሚካሄድና ተቃዋሚ/ተፎካካሪ ድርጅቶች መርሐ ግብራቸውን በመንደፍ ለሥልጣን እንዲወዳደሩ፣ ሥልጣን መያዝ የሚቻለውም በሕዝብ ምርጫ ብቻ መሆኑን ደግመው ደጋግመው መክረዋል፡፡ የዘንድሮ ምርጫ መካሄድ ለማንም አዲስ ዜና ሊሆን አይገባውም፡፡
አሳዛኙ ነገር በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ የምርጫ ሒደት ውስጥ የታዘብነው ለምርጫ ውድድር ከመዘጋጀት ይልቅ በሙሾ ፖለቲካ ጊዜ ማባከንን፣ የሕዝብን ተስፋ ማጨለምና የራስን ድክመት ለመሸፈን ስበብ በማብዛት የተገኙ ዕድሎችን ማበላሸት ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ዓይነት የፖለቲካ ኃይሎች አሉ፡፡ አንደኛው ኃይል ትናንት ላይ ቆሞ የወደፊቱን ለማየት ያልፈቀደና በሙሾ ፖለቲካ፣ የፖለቲካ ሕይወቱን ማርዘም የሚችል የሚመስለው፣ እንዲሁም በአቤቱታ ሊፈጠር በሚችል ትርምስ ሥልጣን በአቋራጭ ይዛለሁ ብሎ በቅዠት ውስጥ ያለ ነው፡፡ ሌላው የፖለቲካ ኃይል ደግሞ ካለፈው ተምሮ ዛሬን ተጠቅሞ ነገ ሕዝቡ የተሻለ ሕይወት እንዲኖረው አገራችን ነገ የተሻለች አገር እንድትሆን ተግቶ የሚሠራ ነው፡፡ ብዙዎቹ የብሔር ድርጅቶች መሪዎቻቸው ትናንት ላይ ቆመው የሚያላዝኑ በመሆናቸው በምርጫው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችላል። ይህን አሉታዊ ተፅዕኖ ግን አቅጣጫ ሊያስቀየር የሚችለው በተለይ የድርጅቱ አባላት በአጠቃላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትናንት ላይ ቆመው በቀሩትና በወደፊት መፃኢ ዕድሉ ላይ ባተኮሩ ድርጅቶች መካከል ያለውን ልዩነት በመረዳት፣ የወደፊት ዕድሉን ብሩህ የሚያደርጉ የፖለቲካ ድርጅቶችን በመምረጥና የፖለቲካ ነጋዴዎችን አጨበርባሪነት እምቢ በማለት ነው።
ስለትናንትና እያጋነኑ በማውራት በሕዝቡ ውስጥ ጥላቻን በመዝራት ጊዜና ኃይል የሚያባክኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ለሕዝብ የሚጠቅም ምንም ዓይነት መርሐ ግብር የላቸውም፡፡ ሕዝቡም ይህንን በቅጡ ሊረዳ ይችላል። ዛሬ ላይ ሆነን እንደ ኦፌኮ መሪዎች የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ ከጥቁር አሜሪካውያን ታሪክ ጋር በሚያነፃፅር የሐሰት ትርክት ሕዝብ በመቀስቀስና ስለኢሕአዴግ ኢፍትሐዊነት በማውራት፣ ምርጫ ላይ ተሳትፎ ማሸነፍ የሚቻል አይመስለኝም። ጥያቄው እነዚህና መሰል ድርጅቶች የኢኮኖሚ የማኅበራዊ መርሐ ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፍልስፍናቸው ምንድነው የሚል ነው። እንደ ጃዋር መሐመድ ያሉ ጽንፈኞች በምርጫ ከተሸነፉ ሁከት ለመፍጠር እየተዘጋጁ መሆናቸው ምልክቶቹ እየታዩ ነው። ጃዋር ለኒውዮርክ ታይምስ በሰጠው ቃለ ምልልስ ምርጫው ፍትሐዊና ነፃ መሆኑን የሚመዝነው በእሱ መመረጥና አለመመረጥ መሆኑን መግለጹ አስቂኝ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ እንጭጭ መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳየበት ነው። ይኸው ግለሰብ በቅርቡ የምርጫ ቦርድን የሚያምነው 50 በመቶ መሆኑን ሰምተናል፡፡ የምርጫ ቦርድን ተዓማኒነትም ሆነ ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ መሆኑን የሚመዘንበትን መሥፈርቱን የሚነግሩን እንደ ጃዋር ዓይነት ሰዎች ዓላማቸው አንድ ነው፡፡ ይህም እኛ ካላሸነፍን ምርጫው ነፃ አልነበረም ለማለት ነው። እነዚህ ኃይሎች ግን ቀጣዩን ምርጫ ሊያሸንፉ የሚችሉበት መርሐ ግብራቸውና አማራጭ ሐሳባቸው ምን እንደሆነ እንኳን አይነግሩንም።
በዚህ ጸሐፊ እምነት እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ሙሾ ከማውረድ ባለፈ አቅም የላቸውም። ኦፌኮም ሆነ በመድረክ ሥር የተሰባሰቡት የፖለቲካ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ንድፈ ሐሳብ አቅርበው የሚያውቁት መቼ ነው? እስከ ዛሬ የነበረው “ፖለቲካ” “ኢሕአዴግን በመኮነን” ላይ ብቻ ያተኮረ ነው፡፡ ዛሬ ትናንት አይደለም፡፡ ኢሕአዴግን በመኮነን ብቻ መፅደቅ አይቻልም፡፡ “የራስን የፅድቅ” ሠርቶ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ በሚቀጥለው ምርጫ ኢሕአዴግ የሚባል የፖለቲካ ድርጅት አይኖርም፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ አሳሪ ነው፡፡ ገራፊ ነው ገዳይ ነው የሚል አጀንዳ ቦታ አይኖረውም፡፡ በዚህ ጸሐፊ ግምት ዛሬ ላይ ሆነው የነገን ተስፋ በመሰነቅ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ እጅግ የሚደነቅ ተግባር እያከናወነ ያለው ኢዜማ የተባለው የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ በኢዜማ ውስጥ የተሰባሰቡ የፖለቲካ ኃይሎች ብቃታቸውንና የድርጅት ሥርዓታቸውን (ዲሲፕሊን) በተግባር አሳይተዋል፡፡
ምርጫው አይቀሬ መሆኑን በመረዳት ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች አሰባስቦ አንድ ድርጅት ያዋቀረው ይህ ድርጅት፣ ስለትናንትና ስሞታ በማቅረብ ጊዜውን ሲያባክንም ሆነ በትናንትና ታሪክ ላይ “የፖለቲካ ልፍያ” ውስጥ ሲንቦጫረቅ አናየውም፡፡ ይህ ጸሐፍ ኢዜማ ውስጥ ካሉ ከማናቸውም ጋር ግላዊ ግንኙነት የለውም። በአንድ ወቅት ብቻ ከብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) እና ሳሙኤል ዮሐንስ (ዶ/ር) ጋር በአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ላይ ለውይይት ከመቅረብና የተወሰነ ውይይት በግል ከማድረግ ውጪ፣ ምንም ዓይነት የጠበቀ ግንኙነት የለውም። ይህ ጽሑፍም ዓላማው ኢዜማንም ሆነ ሌላውን የፖለቲካ ድርጅት ምረጡ ወይም አትምረጡ ለማለት የተዘጋጀ አይደለም። የጽሑፉ ዓላማ አገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚፈጥሩትን ሰበብ አቁመው፣ ጊዜያቸውን ተጠቅመው ለሕዝብ አማራጭ እንዲያቀርቡ ለማሳሰብ ነው።
ከኢዜማ አካሄድ ብዙ መማር ይቻላል፡፡ ኢዜማ ለበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ዕጩዎቹን አዘጋጅቷል፡፡ ለአይቀሬው ምርጫ መርሐ ግብሩን ነድፎ አባላቶቹ እንዲወያዩበት አድርጓል፡፡ “የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” ዓይነት ሰበብ ከኢዜማ አይሰማም። ኢዜማ ዛሬ ላይ ሆኖ ለነገ ለአገር ያለውን ራዕይ በወረቀት አስፍሮ የምርጫ ዘመቻ በማድረግ ላይ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ነው። አገራችን ዛሬ የምትፈልገው እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ኃይል ነው። ለኢዜማ ተመጣጣኝ ተፎካካሪ የሚሆነው በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መሪነት የተመሠረተው የብልጽግና ፓርቲ ነው። የብልጽግና ፓርቲ ከኢሕአዴግ የወረሳቸው ድርጅታዊ መዋቅሮችና ሀብት ስላለው፣ በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በክልሎች ደረጃ የመወዳደር ብቃት አለው። በዚህ ጸሐፊ ግምት ብልጽግና ፓርቲ እንደ ኢዜማ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ጉዳይ በእውቀት የተካኑ ሰዎች የሉትም። ብዙዎች ብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ያሉ የአመራር አካላት አቅማቸው ውስን ነው።
ሆኖም እንደ ዶ/ር ዓብይ ያሉ ብቃት ያላቸው መሪዎች ሌሎች ብቃት ያላቸውን ልሂቃን ወደ ብልጽግና ፓርቲ ሊጎትቱ ይችላሉ። ትልቁ ነገር ብልጽግና ፓርቲ በትናንትና ላይ ቆሞ ሙሾ እያወረደ አይደለም፡፡ ለሕዝብ የነገ ራዕዩን እያቀረበ ያለና ለሕዝብ ተስፋ የሰጠ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ቀጣዩ ምርጫ ስለፍትሕ፣ ዴሞክራሲ፣ የፕረስ ነፃነት፣ ወዘተ ዓይነት አጀንዳዎች ብዙውን የክርክር ቦታ የሚወስዱ ሳይሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚደረግው የሥራ ፈጠራ፣ የቤት ዕጦት፣ የሕክምና ተቋማት ማስፋፍያ፣ የትምህርት ፍኖተ ካርታና ትምህርት ቤቶችን ማሻሻያ፣ በአገሪቱ ውስጥ የብሔራዊ ከበርቴውን ሊያሳድግ የሚችል የቀረጥ ሕግ፣ ሕፃናትና አዛውንት ተኮር መርሐ ግብር፣ የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ፣ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን መሠረታዊ ልማቶችን ማሻሻያ፣ ተገቢ የሆነ የሞኒተሪና የፊስካል ፖሊሲውን ቀርፆና የምርት አቅርቦት አሻሽሎ የኑሮ ውድነትን መቀነስ፣ በተለይም ደግሞ የሕዝብ ቁጥርን ጭማሪ ፍጥነት የሚገድብ ዕቅድን የተመለከቱ ክርክሮች ትኩረት የሚያገኙበት ይሆናሉ የሚል ግምትም አለ። ከምንም በላይ ቀጣዩ ምርጫ ትናንት ላይ ቆመው ሙሾ በሚያወርዱና ዛሬ ላይ ሆነው ስለወደፊቱ የአገራችን ዕድገት ራዕይ ባላቸው ኃይሎች እንደሚሆን በርካታ ምልክቶች እየታዩ ነው። ስለዚህ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ጎራዴያቸውን ሳይሆን አዕምሮአቸውን በመሳል ለውድድር ይዘጋጁ እላለሁ።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡